የኢራን የሂጃብ ተቆጣጣሪ ፖሊስ አንዲት ታዳጊን ራሷን እስክትስት በመደብደብ ተከሰሰ

የኢራን የመብት ተሟጋቾች የግብረ ገብ ፖሊስ አንዲት ታዳጊን ሂጃብ አልለበሽም በሚል የከፋ ድብደባ አድርሶባታል ሲሉ ከሰሱ።

ተሟጋቾቹ ወጣቷ ራሷን ስታ የሚያሳይ ምስልም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተዋል።

የ16 ዓመቷ አርሚታ ገራቫንድ እሑድ ዕለት በቴህራን ሜትሮ ባቡር ላይ ከተሳፈረች በኋላ ራሷን ስታለች።

ባለሥልጣናትም ታዳጊዋ ራሷን ከሳተች በኋላ ከባቡሩ ሲያስወጧት የሚያሳይ በደኅንነት ካሜራ የተቀረፀ ቪዲዮ ለቀዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ ሄንጋው ግን በግብር ገብ ፖሊሶች “የከፋ አካላዊ ጥቃት ተፈፅሞባታል” ሲል ከሷል።

ታዳጊዋ አርሚታ በቴህራን ፋጂር ሆስፒታል በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ሆና ሕክምና እየተደረገላት ሲሆን የሁሉም ቤተሰቦቿ ስልክ መወሰዱንም ተሟጋች ቡድኑ ገልጿል።

ሰኞ ዕለት ባለሥልጣናት ጉዳዩን ለመዘገብ ወደ ሆስፒታል አምርታ የነበረችውን የሻርቅ ጋዜጣ ዘጋቢን አስረዋል።

በኢራን በቁጥር አነስተኛ በሆኑት ኩርዶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሄንጋው፣ ማክሰኞ ዕለት ከሰዓት አርሚታ በቴህራን እንደምትኖር፣ ነገር ግን በአብዛኛው ኩርዶች ከሚኖሩበት ምዕራብ ግዛት ከርማንሻሽ የመጣች እንደሆነ ገልጿል።

“አርሚታ ሂጃብ አልበሽም በሚል በሾሃዳን የባቡር ጣቢያ ባለሥልጣናት አካላዊ ጥቃት ተፈፅሞባታል” ያለው ተሟጋች ቡድኑ፣ ከባድ ጉዳት ደርሶባት ወደ ሆስፒታል መወሰዷንም ጨምሮ ገልጿል።

ሁለት ታዋቂ የመብት ተሟጋቾች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ጥብቅ የሆነውን የአለባበስ ሥርዓት ለማስፈፀም ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ነበር።

ተቀማጭነቱን በአምስተርዳም ያደረገው ራዲዮ ዛማነህም፣ ታዳጊዋ የፀጉር መሸፈኛ ሳታደርግ ወደ ባቡር ውስጥ ከገባች በኋላ በሂጃብ ተቆጣጣሪዎቹ እንደተገፈተረች እና ከብረት ምሰሶ ጋር እንደተጋጨች ስማቸው ያልተገለጸ ምንጭን ጠቅሶ ዘግቧል።

ማክሰኞ ምሽት ላይም ሄንጋው በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አርሚታ ሆስፒታል ውስጥ ራሷን ስታ የሚያሳይ ፎቶ አጋርቷል።

በቢቢሲ ያልተረጋገጠው ይህ ምስል አጭር ፀጉር ያላት ታዳጊ ጭንቅላቷ በፋሻ ተጠቅልሎ በጀርባዋ ተኝታ፣ የመተንፈሻ ቱቦ ተገጥሞላት ያሳያል።

የመብት ተሟጋች ቡድኑ በሆስፒታሉ ውስጥ ከፍተኛ የጸጥታ መኮንኖች ባሉበት የአርሚታ ቤተሰቦች በመንግሥት የዜና ወኪል ኢርና ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው መረጃ ደርሶኛል ብሏል።

ኢርና፣ የአርሚታን እናት በደኅንነት ካሜራው የተቀረፀውን ቪዲዮ እንደተመለከቱ እና እሑድ እለት የተከሰተው ‘ድንገተኛ አደጋ’ እንደነበር መናገራቸውን ዘግቧል።

በአርትኦት በተቆራረጠው እና በኢርና በተላለፈው ቪዲዮ ላይ“ እንደማስበው የልጄ የደም ግፊት ወርዶ ነበር። በጣም እርግጠኛ ግን አይደለሁም። የደም ግፊቷ ወርዶ ነበር ብለዋል።” ሲሉ ተደምጠዋል።

የቴህራን ባቡር ጣቢያ ማኔጂንግ ዳሬክተር መስኡድ ዶሮስቲም በበኩላቸው፣ በአርሚታ እና በመንገደኞች ወይም በባቡር ሰራተኞቹ መካከል ምንም ዓይነት የቃላትም ሆነ የአካል ግጭቶች አልነበረም ብለዋል።

በደኅነንት ካሜራው የተቀረጸው ቪዲዮ አርሚታ ፀጉሯ ሳይሸፈን ከሁለት ታዳጊዎች ጋር ሆና ወደ ባቡሩ ስትገባ ያሳያል። ወዲያውኑም አንደኛዋ ታዳጊ ወረደች። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ራሷን የሳተችው አርሚታ ከባቡሩ በሰዎች ሸክም ስትወጣና መሬት ላይ ሲያስተኟት አሳይቷል።

የኢራን ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በባለሥልጣናቱ የወጣው ቪዲዮ ከባቡሩ ውጭ ያለውን እንጂ ውስጥ የተፈጠረውን አያሳይም ሲሉ ተችተውታል።

ባለፈው ዓመት የ22 ዓመቷ ኩርድሽ ማህሳ አሚኒ ሂጃብ በአግባቡ አለበሽም ተብላ በቴህራን ግብረ ገብ ፖሊስ ከተያዘች በኋላ በደረሰባት ድብደባ በቁጥጥር ሥር ሳለች ሕይወቷ ማለፉ ይታወሳል።

የዓይን ምስክሮች በፖሊስ መኮንኖች ተደብድባለች ያሉ ሲሆን ባለሥልጣናት ግን ቀድሞውኑ በነበረባት የጤና ችግር ነው ሕይወቷ ያለፈው ብለው ነበር።

አሚኒ በእስር ቤቱ ውስጥ ስትወድቅና ሆስፒታል ውስጥ ሆና የሚያሳዩ በደኅንነት ካሜራ የተቀረጹ ቪዲዮዎች በርካታ ኢራናውያንን አስቆጥቷል። አሚኒ ለሦስት ቀናት ራሷን ስታ ከቆየች በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ የፀረ መንግሥት ተቃውሞው በበመላ አገሪቷ ተቀታጥሎ ነበር .

ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በነበረው ግጭትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል።

ማህሳ አሚኒ ከሞተች ከአንድ ዓመት በኋላ ተቃውሞው የበረደ ሲሆን አሁንም ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ሰልፎች ይካሄዳሉ። በርካታ ታዳጊዎችና ሴቶችም የአለባበስ ሕግን በመጣስ ፀጉራቸውን መሸፈን አቁመዋል።