ኢራን ሂጃብ ያላደረጉ ሴቶችን ለመከታተል ካሜራዎችን ገጠመች

የኢራን ባለስልጣናት ሂጃብ ያልለበሱ ሴቶችን ለመለየት ህዝብ በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ካሜራዎችን መትከል መጀመራቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ጸጉራቸውን የማይሸፍኑ ሴቶች "የማስጠንቀቂያ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ይደርሳቸዋል" ብሏል ፖሊስ።

ይህም "በሂጃብ ሕግ ላይ የሚደርሰውን ተቃውሞ ለመከላከል ይረዳል" ብሏል።

ባለፈው ዓመት ማህሳ አሚኒ የተባለች ወጣት ኩርዳዊት የሂጃብ ሕግን ጥሳለች በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ሕይወቷ በማለፉ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።

አሚኒ ሕይወቷ ካለፈ በኋላ የመታሰረ ዕድል ቢኖራቸውም በተለይም በትልልቅ ከተሞች መሸፈኛቸውን የማያደርጉ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በመንግሥት ስር የሚተዳደረው ኢስላሚክ ሪፐብሊክ የዜና አገልግሎት ይዞት በወጣው የፖሊስ መግለጫ ቴክኖሎጂው “ስማርት” ካሜራዎችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን በመጠቀም “የሂጃብ ሕግን የሚጥሱትን በመለየት የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን” ይልካል ብሏል።

ከእአአ 1979 የእስልምና አብዮት በኋላ ጥብቅ የኃይማኖት ሕግን እየተተገበረ ሲሆን ሴቶች ፀጉራቸውን በሂጃብ እንዲሸፍኑ በሕግ ይገደዳሉ። ሕጉን የጣሱ ሴቶችም ቅጣት ወይም እስራት ይጠብቃቸዋል።

ፖሊስ የቅዳሜ ባጋራው መግለጫ ሂጃብን “ከኢራን ሕዝብ የሥልጣኔ መሠረት አንዱ ነው” በማለት የገለፀው ሲሆን የንግድ ቤት ባለቤቶች ሕጉን “በትጋት” እንዲያስከብሩ አሳስቧል።

በኢራን ጸጉራቸውን ባልሸፈኑ ሴቶች ላይ በይፋ የሚደረጉ ጥቃቶች በብዛት የተለመዱ ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ግለሰብ ሂጃብ ባለደረጉ ሁለት ሴቶች ላይ እርጎ ሲደፋ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል። በኋላም ሴቶቹ የሂጃብ ሕግን በመጣስ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ግለሰቡም ሁከት በመፍጠር በቁጥጥር ስር ውሏል።

ከታህሳስ ወር ጀምሮ ኢራን ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ሲታሰሩ አራቱ ተገድለዋል። የሕጉ ደጋፊዎች ሕጉን ለማስከበር የበለጠ መሠራት እንዳለበት አጥብቀው መከራከር ቀጥለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ "ለሃይማኖት አስፈላጊ በመሆኑ” የሃገራቸው ሴቶች ሂጃብ መልበስ አለባቸው ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

የኢራን የፍትህ ሃላፊ ጎላምሆሴን ሞህሴኒ ኢጄይ ሴቶች ሕጎቹን እንዲከተሉ ለማበረታታት የተሻለው መንገድ ማስገደድ ላይሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

"ባህላዊ ችግሮች በባህላዊ መንገድ መፍታት አለባቸው... መሰል ችግሮችን በማሰር እና በመቅጣት ለመፍታት ከፈለግን ችግሩ እየጨመረ ስለሚሄድ የሚፈለገውን ያህል ውጤት አናገኝም" ብለዋል።