አይኤምኤፍ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የተደረገው ውይይት አዎንታዊ ሂደት የታየበት ነው አለ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን፣ አይኤምኤፍ ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚሰጠውን ድጋፍ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የተደረገው ውይይት አዎንታዊ ሂደት የታየበት መሆኑን አስታወቀ።

ከመጋቢት 18፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የቴክኒክ ጥናቶችን ለማድረግ ለአስር ቀናት በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረገው የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ቡድን ጉብኝቱን ካጠናቀቀ በኋላ በትናንትናው ዕለት መጋቢት 29/2015 ዓ.ም በድረገጹ ባወጣው መግለጫ ነው ይህንን የገለጸው።

“የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በአገር በቀል ማሻሻያው ድጋፍ ላይ ስለሚኖረው ሽፋንም ባደረግነው ውይይት ረገድ አዎንታዊ ሂደቶችን አይተናል” ሲሉም የአይኤምኤፍ ልዑክ ቡድኑን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ መናገራቸው ተጠቅሷል።

ውይይቶቹ በቀጣይ ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ በሚደረጉ የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ስብሰባዎች እንዲሁም ከዚያ በኋላም እንደሚቀጥልም መግለጫው አክሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቁልፍ የሚባሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ምጣኔ ኃብት ችግር ለመፍታት እንዲሁም የአገሪቱን ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት አቅምም ለመጠቀም በሚል ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሁለተኛ ምዕራፍ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም መርሃ ግብር በበጎ እንደሚያዩትም አይኤምኤፍ አስታውቋል።

በመጋቢት ወር ላይ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አገሪቷ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ወደነበረበት ለመመለስ የፈረመችው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምነት እንዲሁም በትግራይ ክልል ተቋርጠው የነበሩ የሰብዓዊ እርዳዎችና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበረበት ለመመለስ እየተሰራ ያለውን ስራም በበጎ እንደሚቀበለውም መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።

ተቋሙ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የድጋፍ ፕሮግራም እንዲሁም አገሪቷ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ስረዛና የአከፋፈል ሽግሽግ እንዲደረግላት ያቀረበችው ጥያቄ የዘገየው ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ነበር።

በመቶሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና በቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ ውድመትን ያስከተለው የርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ተቋማት እና አገራት ታገኝ በነበረው ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ጫናን አስከትሎ ነበር።

ብሉምበርግ እንዳለው ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እና የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመሸፈን አስፈላጊ ለሆኑ የገቢ ምርቶች ክፍያ ለመፈጸም ድጋፍ ያስፈልጋታል።

ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር በአፍሪካ ካሉ የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን እና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተነሳ ከዓለም ባንክ አንዲሁም ከአይኤምኤፍ የምታገኘውን ድጋፍ ገትቶት መቆየቱን ብሉምበርግ ዘግቧል።

በጦርነቱ እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር የገጠማት ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ከመመዝገቡ በላይ እጥረትም ተከስቷል።

ጥቅምት መጨረሻ በፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመውን ዘላቂ ግጭትን የማቆም ስምምነት አፈሙዝ ጸጥ ከማሰኘት ባለፈ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችንም ህይወት ወደ መደበኛው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።

በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ ተናግረዋል።