የሩሲያን ሐሰተኛ ዜና ለሚሊዮኖች ያሰራጫል የተባለው የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያ

ሐሰተኛ መረጃን የሚያጣራው የቢቢሲ ቡድን የሩሲያን መንግሥት የተሳሳተ መረጃ አረብኛ ቋንቋ ለሚናገሩ ሚሊዮኖች እያሰራጨ ስላለው ኩባንያ መረጃዎችን አጠናቅሯል።

የሚዲያ ኩባንያው በዩናይት ኪንግደም የተመዘገበ ነው።

ይህ ኩባንያ “ያላ ኒውስ” የሚሰኝ ሲሆን፣ ዜናዎችን ገለልተኛ በሆነ መልኩ እንደሚያቀርብ ይናገራል።

በተቃራኒው የቢቢሲ ትንታኔ እንደሚያሳየው ሚዲያው የሚያሰራጫቸው መረጃዎች ይዘት በሩሲያ መንግሥት ከሚደገፉ እና መቀመጫቸው ሶሪያ ከሆኑ ድረገጾች ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆኑን ያሳያል።

የያላ ኒውስ እናት ኩባንያ ያላ ግሩፕ ጠንካራ የሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ አለው። 20 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የፌስቡክ ገጾቹ ማራኪ እንዲሁም በባለሙያ የተሰሩ ናቸው።

የሦስት ሚሊዮን አረብኛ ተናጋሪ ተከታዮቹ ትኩረትን ሊስቡ በሚችሉ ታሪኮች ላይም ያነጣጠሩ በየሁለት ሰዓቱ የሚለጠፉ ቪዲዮዎችም ታዋቂ አድርገውታል።

ከእነዚህም ውስጥ የታዋቂ ሰዎች ቃለ ምልልስ፣ አስቂኝ ቀልዶች፣ የዓለም ፖለቲካ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።

ያላ ገለልተኛ፣ ነጻ እና ተአማኒ ዜናዎችን እንደሚያቀርብ ግምገማዎች አሉ። ነገር ግን በቅርበት ለተከታተለው ለሩሲያ ጭፍን ድጋፍ የሚያሳዩ ታሪኮች፣ እንዲሁም በሩሲያ የመንግሥት ሚዲያ ላይ ከታዩት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ መረጃዎች ይቀርባሉ።

በተለይም ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ሚዲያው ከፍተኛ ዕውቅናን አትርፏል።

ለምሳሌ መጋቢት 1/ 2014 ዓ.ም. የሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዥን አሜሪካ ወፎችን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማ ገዳይ በሽታዎችን ለማሸከም እና ወደ ሩሲያ ለማሰራጨት እየሞከረች እንደሆነ የሚጠቅስ አስገራሚ እና ፍጹም ልብወለድ የሆነ ታሪክ አቀረበ።

በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ ታሪኩ ተተርጉሞ በሩሲያ መንግሥት በሚደገፉት ስፑትኒክ አረብኛ እና በአረብኛው “ሩሲያ ቱደይ” ድረገጾች ላይ ታተመ።

ከሁለት ሰዓታት በኋላ ይኸው ታሪክ በያላ ኒውስ የፌስቡክ ገጽ ላይ በቪዲዮ መልክ ተለጠፈ። ቃላቶቹ ሳይቀር ተመሳሳይ ነበሩ።

የጦር መሳሪያዎቹ ወፎች ታሪክ ከብዙ አንድ ነው።

ቢቢሲ ለአንድ ዓመት ያህል ሐሰተኛ መረጃን ከሚያጣሩ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በያላ ኒውስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የታዩ ቪዲዮዎችን መርምሯል።

በዚህም ሁሉም በሚባል ሁኔታ በክሬምሊን ባለቤትነት የሚተዳደሩ ወይም በክሬምሊን ከሚደግፋቸው የዜና ጣቢያዎች ጋር የተገናኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ አረጋግጧል።

ከእነዚህ መካከልም ዩክሬን ውስጥ ቡቻ በተባለው ስፍራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የተቀነባበረ ስለመሆኑ የሚናገር ሐሰተኛ ዜና፣ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሰክረው ለዩክሬን ሕዝብ መግለጫ መስጠታቸውን የሚጠቅስ፣ እንዲሁም የዩክሬን ወታደሮች ከጦር ግንባር እሸሹ ነው የሚሉ ይገኙበታል።

የእነዚህ ሁሉ የዜና ምንጮች የሩሲያ መንግሥታዊ ሚዲያ ሲሆን፣ ከጥቂት ሰዓታት በኋላም በያላ ኒውስ ላይ ተመሳሳይ ታሪኮች በቪዲዮዎች ወጥተዋል።

“የመረጃ ዝውውር”

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የመረጃ ተቋቋሚነት ማዕከል ውስጥ የሩሲያ ተጽእኖዎችን የሚያጠኑት ቤለን ካርራስኮ ሮድሪጌዝ፣ ስለ ያላ ኒውስ ሲናገሩ በመካከለኛው ምሥራቅ የክሬምሊን ድምጽን ለማስተጋባት እንደ ማጉያ እያገለገለ ነው ብለዋል።

ዜናዎቹ በተመመሳይ ቀን እና ሰዓት መውጣታቸው እንዲሁም ተመሳሳይ ይዘት መኖሩ ያላ ኒውስ ለሩሲያ “በመረጃ አዘዋዋሪነት” እየሰራ ስለመሆኑ የሚጠቁም እንደሆነም ይናገራሉ።

ፕሮፓጋንዳው ከክሬምሊን ቀጥታ የወጣ እንዳልሆነ በማስመሰል በሦስተኛ ወገን እንዲወጣ ከማድረግ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ከዚህ ቀደምም ሩሲያ እንዲህ አይነት ድርጊቶች በመፈጸም ትታወቃለች።

“ያላ ኒውስ በአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ተወዳጅነት ስላለው ከክሬምሊን ጋር ግንኙነት ያላቸው የዜና ምንጮች መረጃዎችን ለማሰራጨት ሊጠቀሙበት ይችላሉ” በማለት ያስረዳሉ።

ዓለም አቀፉ የሳይበር ደኅንነት እና ጥበቃ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሩሪግ ቶርንተን በበኩላቸው ሰዎች የሩሲያ መንግሥት ሚዲያዎችን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ የመረጃ ዝውውር እየተለመደ መጥቷል ይላሉ።

“ሃሳቡ ትክክለኛ ያልሆኑ ትርክቶችን ወደ ትልልቅ ሚዲያዎች በማምጣት እውነት እንዲመስሉ ማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነት ይዘቶችንም ለማዘጋጀት በዲጂታል ማርኬቲንግ የተሰማሩ ድርጅቶችን በመቅጠር ከሩሲያ ጋር ሙሉ በሙሉ ግንኙነት የሌለው እንዲመስል ማድረግ ነው። ከዚያም ዜናዎቹ በራሳቸው እንዲፈሱ ማስቻል ነው” ይላሉ።

ሐሰተኛ ግምገማዎች

ያላ ኒውስ የያላ ግሩፕ አካል ሲሆን፣ ሚዲያውም ራሱን የሚገልጸው “በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ በቪዡዋል መስኮች” የተሰማራ እንደሆነ ነው። ሆኖም የድርጅቱ ተግባር እንደ ማኅበራዊ ገጾቹ የረቀቀ አይመስልም።

የያላ ግሩፕ ድረገጽ በአብዛኛው በዘፈቀደ ጽሑፎች እና በአክሲዮን ፎቶዎች የተሞላ ነው። አብዛኞቹ በፌስቡክ ላይ የሚያቀርቧቸውም የታዳሚ ግምገማዎች አምስት ኮከብ የተሰጣቸው ሲሆን ሐሰተኛም ይመስላሉ።

ለዚህም ማሳያው በተመሳሳይ ቀኖች የተጻፉ እና ከደቡብ ምሥራቅ እስያ በተገኙ አንድ ዓይነት አካውንቶች ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ለፌስቡክ ጥሩ ግምገማ ክፍያ መቀበል ትልቅ ንግድ እንደሆነም ይታወቃል።

ሁለት በተደጋጋሚ የተሰጡ ግምገማዎች የያላ ኒውስ “ገለልተኛ፣ ሙያዊ እና ተጨባጭ መረጃ የሚሰጥ” የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ “አስደናቂ፣ ታማኝ፣ ግልጽ እና አላማ ያለው የዜና መድረክ” በማለት ገልጸውታል።

ስትራቴጂካዊ ዲያሎግ የተሰኘው ተቋም ሠራተኛ ሙስጠፋ አያድ በዚህ ግምገማ አይስማሙም “በደንብ ተቀናጅቶ እየተሰራ ስለ መሆኑ አመልካች ነው” ይላሉ።

ያላ ኒውስ በየዕለቱ በርካታ፣ በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጁ እና ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ቪዲዮዎችን ለማዘጋጀት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሊያስወጣው እንደሚችል ያምናሉ።

የያላ ግሩፕ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተመዝግቧል፤ ዕውቅናም አለው።

የተመዘገበ አድራሻውም በመካከለኛው ለንደን በሚገኘው ብሉምስበሪ ሲሆን፣ ከ65 ሺህ በላይ ኩባንያዎችም በዚህ አድራሻ ተመዝግበዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 12 ሺህ ያህሉ የነቃ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው። ያላ ግሩፕ በዚህ አድራሻው ጽህፈት ቤት ቢኖረውም ሠራተኛ ግን የለውም።

ሆኖም ያላ ቢሮው በእርስ በርስ ግጭት በምትታመሰው እና ፕሬዝዳንቷ ባሻር አል አሳድ የሩሲያ የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው ሶሪያ እንደሆነ ይጠረጠራል።

ሩሲያ በ12 ዓመታቱ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ፕሬዝዳንት አሳድን በመደገፍ የጦር መሳሪያ ሰጥታለች።

የያላ ኒውስ ሠራተኞች እና ቢሮዎችን የሚያሳዩ የፌስቡክ ፎቶዎችን በጥልቀት በመመርመር ቢቢሲ የአካባቢውን ሁኔታ በመገምገም እና የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ቢሮው አረንጓዴዋ ደማስቆ ልትሆን እንደምትችልም ነው የጠቆመው።

የአብዛኞቹ ሠራተኞች የማኅበራዊ ሚዲያ መገለጫዎቻቸው በሶሪያ ዋና ከተማ ውስጥ እንዳለ ይናገራል። አንድ የቀድሞ ሠራተኛም ይህንኑ አረጋግጧል።

የያላ ደንበኞች የሶሪያ መሪ ደጋፊ የሆኑ ታዋቂ ሰዎችን እና ጋዜጠኞችን ያካትታል። በአንድ ፎቶ ላይም የያላ ደንበኛ የሆነው የሶሪያ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሻዲ ሃልዊ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሶሪያውያኑ ነጋዴዎች የካተርጂስ ወንድማማቾች ጋር ታይቷል። ሃልዊ በካተርጂስ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት የሬድዮ ጣቢያ አለው።

ሌላኛው የያላ ደንበኛ የሩሲያ መንግሥት የሬድዮ ኔትወርክ አካል በሆነው በስፑትኒክ አረብኛ የተሰሩ ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፈው እና የሶሪያ መንግሥት ደጋፊው የሻም ኤፍኤም የሬድዮ ጣቢያ ነው።

የቢቢሲ ሞኒተሪንግ የሶሪያ ሚዲያ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ የግል ሚዲያዎች “አብዛኛውን ጊዜ ከፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተቋማት ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላቸው የንግድ ሰዎች በባለቤትነት የሚተዳደሩ ናቸው” ይላሉ።

ያላ ኩባንያውን በዩናይትድ ኪንግደም ያስመዘገበው መቀመጫው ማዕቀብ በተጣለባት አገር ውስጥ መሆኑ እንዳይታወቅ እና እንደ ሜታ ካሉ ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክና ለመፍጠር እንዲያስችለው እንደሆነ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

ከያላ የፌስቡክ ገጾች አንዱ ከሜታ ጋር “የንግድ አጋር” ስለመሆናቸው የሚያሳይ ጽሑፍ የለጠፈ ሲሆን፣ ይህም ማለት በፌስቡክ ከፍተኛ ስፍራ ከተሰጣቸው አንዱ መሆኑንም የሚጠቁም ነው።

ቢቢሲ ይህንን በተመለከተ ሜታን ቢጠይቅም ተቋሙ አስተባብሏል።

ከያላ ኒውስ ጀርባ ያለው ማነው?

የያላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነዋሪነቱን በዱባይ ያደረገው ሶሪያዊው ነጋዴ አህመድ ሞኤምናን ቢቢሲ ጠይቆታል።

“ያላ ግሩፕ መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ ኩባንያ ነው” ሲል አህመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ከ500 በላይ ደንበኞች ያሉን ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ታዋቂ ሰዎች እና አርቲስቶች ይገኙበታል። ለንደን ውስጥ እስካሁን ሠራተኞች የለንም በቅርቡ ግን ቢሮ እናቋቁማለን” ብሏል።

በያላ ኒውስ ላይ የሩሲያን ወረራ የሚደግፉ ቪዲዮዎችን በተመለከተ ያለውን አስተያየት አህመድ ተጠይቆ፣ “ያላ ኒውስ ለየትኛውም ወገን አያዳላም። ሶሪያም ሆነ ሩሲያ ወይም ሌላ አገር ገለልተኝነትን እናከብራለን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ከሩሲያ ወይም ከሶሪያ መንግሥታት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለት እንደሆነ ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ “ያያላ መሥራችም ሆነ የገንዘቡ ምንጭ እኔ ነኝ። ማንም ተጽዕኖ ሊያሳድርብኝ አይችልም” ብሏል።