ጸጉራችሁን አልሸፈናችሁም የተባሉ ኢራናውያን ሴቶች እርጎ ከተደፋባቸው በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ሁለት ኢራናውያን ሴቶች በአደባባይ ሆናችሁ ጸጉራችሁን አልሸፈናችሁም በሚል በአንድ ግለሰብ እርጎ ከተደፋባቸው በኋላ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በማሕበራዊ ሚዲያ በስፋት የተጋራ ተንቀሳቃሽ ምስል አንድ ወንድ መደብር ውስጥ ቆመው ወደ ነበሩት ሴቶች በመጠጋት ካነጋገራቸው በኋላ በንዴት ከመደብር መደርደሪያ ላይ እርጎ አንስቶ ጭንቅላታቸው ላይ ሲደፋ አሳይቷል።

የኢራን ባለስልጣናት ማንነቱ ባልተገለጸው ወንድ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጸጉራቸውን ባለመሸፈናቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።

ግለሰቡም ሁከት በመፍጠር በሚል በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ሁለቱ ሴቶች አገልግሎት ፍለጋ በመደብር ውስጥ ቆመው ሲጠባበቁ ያሳያል።

ወደ ሁለቱ ሴቶች የቀረበው ግለሰብ ካነጋገራቸው በኋላ በተደጋጋሚ በእርጎ ጥቃት ሲያደርስባቸው ይታያል። ከዚያም በመደብሩ ባሉ ሌሎች ሰዎች ተገፍትሮ ከመደብሩ እንዲወጣ ተደርጓል።

ይህ ክስተት ያጋጠመው በኢራን አስገዳጅ የሆነው ሂጃብ የመልበስ ሕግ እንዲቀየር ከፍተኛ ተቃውሞ ለወራት ሲካሄድ ከሰነበተ በኋላ ነው።

ሦስቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያስታወቀው መንግሥታዊው ሚዛን የዜና ወኪል ለመደብሩ ባለቤትም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል ብሏል።

በኢራን ሴቶች ጸጉራቸውን በሂጃብ ሳይሸፍኑ መንቀሳቀስን የሚከለከል ሲሆን በአንዳንድ ትላልቅ ከተሞች ግን ሴቶች ሕጉን በመተላለፍ ጸጉራቸውን ሳይሸፍኑ በአደባባይ ይታያሉ።

ይህ ሕግ በርካታ የኢራን ማሕብረሰብ አባላትን የሚያስቆጣ ሲሆን ለወራት የዘለቀ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኢራን ተቀጣጥሎ ነበር።

የዚህ ተቃውሞ መነሻ ደግሞ አንዲት የ22 ዓመት ወጣት ሂጃብ በአግባቡ አለበሰችም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሳለች ሕይወቷ ማለፉ ነበር።

በታቀውሞዎቹ ምክንያት በ10ሺዎች የሚቆጠሩ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ሲሆን ከአደባባይ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ አራት ሰዎች ደግሞ በሞት ተቀጥተዋል።

ሂጃብ መልበስ ግዴታ መሆኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢደርስበትም የኢራን መንግሥት ግን ሕጉን ከማስፈጸም ወደ ኋላ አላለም።

ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 23/2015 ዓ.ም. የኢራን ፕሬዝዳንት ኤብራሂም ራይሲ የኢራን ሴቶች “ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን” ለመወጣት ሂጃብ መልበሳቸው ግዴታ ነው ብለዋል።