ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ 300 ሚሊዮን ሥራዎችን ሊተካ እንደሚችል ተጠቆመ
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) በዓለም ዙሪያ በሰዎች የሚሰሩ 300 ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራዎችን ሊተካ እንደሚችል የኢንቨስትመንት ባንኩ ጎልድማን ሳክስ ሪፖርት አመለከተ።
በዚህም በአሜሪካ እና በአውሮፓ በሰው ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል ሩቡን ሊተኩ የሚችሉ ሲሆን፣ ምርታማነት እና እድገትንም ይጨምራሉ ተብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመረቱ ሸቀጦች እና ምርቶችን እንዲሁም አገልግሎቶችን በሰባት በመቶ ሊጨምር ይችላል ብሏል ሪፖርቱ።
“አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከሰው ሥራ የማይለዩ ይዘቶችን መፍጠር የሚችል ትልቅ እድገት ላይ ደርሷል” ይላል ዘገባው።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኮምፒውተሮች የተለያዩ የተሻሻሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስብስብ ሲሆን፣ ከእነዚህም ተግባራት ውስጥም ማየት፣ ቋንቋ መተርጎም፣ መረዳት፣ መረጃ መተንተን፣ ጥቆማዎችን መስጠት እና ሌሎችንም ያካትታል።
ጄኔሬቲቭ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በበኩሉ ጽሑፍ፣ ምስል፣ ድምጽ እና ሰው ሰራሽ መረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዓይነት ይዘቶችን ለማዘጋጀት እና ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
የቅጥር ዕድሎች
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት የማፍሰስ ዕቅድ አለው።
ይህም በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ያለውን ምርታማነት ለመጨመር የታለም ነው።
ሆኖም በሰዎች ሕይወት ላይ ስለሚያመጣው ተጽዕኖ ሕዝቡን ለማረጋጋትም እየሞከረ ይገኛል።
“አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሰዎችን ተግባራት ሙሉ የሚያደርግ እና የማያደናቅፍ አለመሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ነገር ግን ቴክኒሎጂው የሰዎችን ሥራ ይነጥቃል ማለት አይደለም፤ የተሻለ ያደርጋል እንጂ” በማለት የቴክኖሎጂ ፀሐፊ ሚሼል ዶኔላን ዘ ሰን ለተባለው ጋዜጣ ተናግረዋል።
ሪፖርቱ በበኩሉ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ሊለያይ እንደሚችልም ነው ያስታወቀው።
በዚህም 46 በመቶው በአስተዳደር እንዲሁም 44 በመቶ በሕግ ሙያዎች ውስጥ የሚሰሩ ተግባራት በማሽን ሊተኩ ወይም አውቶማቲክ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአንዳንድ ዘርፎች የሚኖረው ተጽዕኖ ያነሰ እና የሰዎችንም ተግባር መተካት የሚችለው በጥቂቱ ነው።
ከእነዚህም ውስጥ በግንባታ ላይ 6 በመቶ እንዲሁም በጥገና ውስጥ 4 በመቶ የሚሆኑት ናቸው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተካት የሚቻለው።
ቢቢሲ ቀደም ሲል አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሙዚቃው ዘርፍ እየተጫወተ ባለው ሚና የአንዳንድ አርቲስቶች ስጋት መሆኑንም ዘግቧል።
“የደመወዝ ቅነሳ”
“እርግጠኛ የምሆንበት አንዱ ጉዳይ ምን ያህል ሥራዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንደሚተኩ የምናውቅበት መንገድ የለም” ሲሉ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦክስፎርድ ማርቲን ትምህርት ቤት የሥራ ዳይሬክተር ካርል ቤኔዲክት ለቢቢሲ ተናግረዋል ።
“ቻትጂፒቲ (ChatGPT ) ለምሳሌ በአማካይ የመጻፍ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ድርሰቶችን እና መጣጥፎችን እንዲያዘጋጁ አስችሏቸዋል።”
“በዚህም ጋዜጠኞች የበለጠ ፉክክር የሚያጋጥማቸው ሲሆን፣ ይህም ደመወዝ እንዲቀንስ ያደርጋል። ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሥራዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ካላየን በስተቀር” ይላሉ።
“የጂፒኤስ ቴክኖሎጂን እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪውን ኡበርን እናስበው። በለንደን ውስጥ ያሉ መንገዶች እና ጎዳናዎችን ማወቅ ብዙም ጥቅም አይኖረውም። እናም ልምድ ያላቸው እና ነባር አሽከርካሪዎች ከፍተኛ የደመወዝ ቅነሳ እንዳጋጠማቸው አይተናል። በምርምራችን መሰረት 10 በመቶ ክፍያቸው እንዲቀነስ ሆኗል” በማለት ያስረዳሉ።
“ያስከተለው ዝቅተኛ ደመወዝ እንጂ አሽከርካሪዎችን መቀነስ አልነበረም።”
“በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በፈጠራ ሥራዎች ላይ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ይላሉ።
መራራ ያለው እውነት
ሪፖርቱ ዋቢ ባደረገው ጥናት መሠረት በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች በአውሮፓውያኑ 1940 ላይ ያልነበሩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ነገር ግን ከአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ጀምሮ የተፈለሰፉ የቴክኖሎጂ ለውጦች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በበለጠ በፍጥነት ሰዎች ሥራቸውን እንዲያጡ ምክንያት መሆናቸውን ሌሎች ጥናቶች ይጠቁማሉ።
እናም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንደ ቀድሞው የመረጃ ቴክኖሎጂ እድገት አካሄድ ካለው በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሰዎች ሥራን ሊቀንስ እንደሚችል ሪፖርቱ ይደመድማል።
ሆኖም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለረጅም ጊዜ በዓለማችን ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ሲሉ የሪዞሉሽን ፋውንዴሽን የምርምር ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቶርስተን ቤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሁሉንም እርግጠኛ የሆኑ ትንበያዎችን ከጥርጣሬ ጋር ማየት አለብን” ሲሉም ያስረዳሉ።
አክለውም “ቴክኖሎጂው ለወደፊቱ እንዴት እንደሚቀየር ወይም ተቋማት በምን መንገድ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች እንዲሚያዋህዷቸው አናውቅም” ብለዋል።
“ይህ ማለት ግን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምንሰራበትን መንገድ አያደናቅፍም ማለት አይደለም። ነገር ግን ከፍተኛ ምርታማነት እና ዝቅተኛ ዋጋ ባላቸው አገልግሎቶች ላይ በማተኮር የኑሮ ደረጃች ከፍ ሊልበት የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጠራል። ሌሎች ኩባንያዎች እና ኢኮኖሚዎች ከቴክኖሎጂ ለውጥ ጋር በተሻለ ሁኔታ ከተላመዱ ሰዎች ላይ የሚያመጣው ተጽእኖን ልናይ ይገባል።”