ሆስፒታሎቿ በቁስለኞች እና በአስከሬን በተጨናነቁባት ጋዛ የአየር ጥቃቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
ማስጠንቀቂያ፡ በዚህ ጽሑፍ አንዳንዶችን ሊረብሹ የሚችሉ መረጃዎች ተካተውበታል
በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው አል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል የአስከሬን መሸፈኛ እያለቀበት ነው።
አስከሬኖች ግቢ ውስጥ ተከማችተዋል። ጸሎት ሲካሄድና ዘመድ አዝማድ በሐዘን ብዛት ራሳቸውን ሲስቱ ይታያል።
የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች የቆሰሉትን ለማከም እና በጣም የተጎዱትን ለማዳን ደፋ ቀና ይላሉ። የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ቀን ከቀን ወደ ቀን እየተመናመነ ነው።
ጉዳት በደረሰባቸው ሰዎች በተሞላው ሆስፒታል ሐኪሞች አንዱን ታካሚ አስተናግደው ወደ ሌላኛው ለመሄድ ይጣደፋሉ።
እሁድ እለት ከሆስፒታሉ የወጡ አንዳንድ ምስሎች ለማጋራት የሚከብዱ ናቸው። ሁለት ጨቅላዎችን ጨምሮ በርካታ ህጻናት ህይወታቸውን አጥተዋል።
በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣናት እንደተናገሩት እስራኤል በፈጸመችው የቦምብ ድብደባ በአንድ ምሽት ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል ጦር ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሐማስ መሪ መኖሩን የሚያረጋግጥ የስለላ መረጃ በማግኘቱ እና ከአካባቢው ወደ እስራኤል እንዲተኮስ ትዕዛዝ በመስጠቱ" አካባቢው ዒላማ ተድርጓል ብሏል።
እሁድ ጠዋት በርካታ መኪናዎች የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል ሲያመላልሱ ታይተዋል።
"እዚህ የነበርነው ገና ጎህ ሳይወጣ ጀምሮ ነው። አስከሬኖቹ ሙሉ በሙሉ የሆስፒታሉን ግቢ ሞልተውታል። በሆስፒታሉ ውስጥ፣ ውጪ እና ማቀዝቀዣዎች ውስጥ አስከሬኖች ሞልተዋል" ሲል የሆስፒታሉ ሠራተኛ ተናግሯል።
"የአስከሬኑ ቁጥር በርካታ በመሆኑ በቂ መሸፈኛ የለንም። አንዳንድ አስከሬኖች ተቆራርጠው ለየብቻ እየመጡ ነው። አስከሬኖቹ በጣም በመጎዳታቸው ለመለየትም አንችልም::"
ሁኔታውን “መቋቋም የማይቻል” ሲሉ ገልጾ፣ “ከዚህ በፊት ብዙ ብንመለከተም፣ አሁን ግን ብዙ አይተን የማናውቃቸው ነገሮች ገጥመውናል” ብሏል።
የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ወደ ሦስተኛ ሳምንት መዝለቁን ተለከትሎ ተመሳሳይ ክስተቶች በሌሎች ሆስፒታሎችም እየታዩ ነው።

በጋዛዋ ቴል አል ሀዋ ከተማ አካባቢ በሚገኘው አል-ቁድስ ሆስፒታል፣ 23 ዶክተሮች እና ነርሶች ከ500 በላይ ህመምተኞችን ሲያስተናግዱ በአቅራቢያው ባሉ ሕንፃዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የሆስፒታሉ ሐኪም ለቢቢሲ በላከው መልዕክት ገልጿል።
በሆስፒታሉ የተጠለሉ ታካሚዎች እና ሠላማዊ ሰዎች "በአስፈሪ ሁኔታ" ውስጥ እንደሚኖሩ ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ሐኪም በድምጽ ባስተላለፈው መልዕክት ገልጿል።
የጤናው ዘርፍ "አደጋ" ውስጥ ነው ከማለት ባለፈ ሐኪሞች መጀመሪያ ማንን ማከም እንዳለባቸው ወደ መወሰን ገብተው። ቅድሚያ ያላገኙት ወረፋ ይጠብቃሉ።
"ብዙዎቹ ቁስለኞች ለቀዶ ሕክምና ቀናትን ይጠብቃሉ" ብሏል ሐኪሙ።
የሐኪሞች ቁጥርም ተመናምኗል። የተወሰኑት ሲገደሉ ሌሎቹ ደግሞ ሆስፒታል ለመድረስ አልቻሉም። የቀሩት ሐኪሞች እዚያ ተጠልለው ከሚገኙት 1200 ተፈናቃዮች ጋር ህንጻቸውን ተጋርተዋል።
"120 የተለያየ ጉዳት ያጋጠማቸው ሰዎች አሉ። 10 ታካሚዎች በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ። ሥር የሰደደ ህመም ያለባቸው 400 ያህል ታካሚዎችም አሉን" ሲል ዶክተሩ ተናግሯል።
"ወደ 1 ሺህ 200 የሚጠጉ የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ። እነዚህን ሁሉ ማንቀሳቀስ ቀላል ባለመሆኑ ሆስፒታሉን ላለመልቀቅ ወስነናል።"
የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ያሉ ነዋሪዎች በሙሉ ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሸሹ በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ደቡባዊ ጋዛ ተሰደዋል። አሁንም ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሰሜን ጋዛ በቤታቸው ቀርተዋል።
እርዳታ የጫኑ የመጀመሪያዎቹ 20 መኪኖች ቅዳሜ በግብጽ የድንበር ማቋረጫ በኩል መግባት ቢችሉም፤ በጋዛ ያሉ ሆስፒታሎች ተጨማሪ የህክምና ቁሳቁስ ይፈልጋሉ።
ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ አንዳንድ የምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶች ቢገቡም፣ ምንም አይነት ነዳጅ ጋዛ አልደረሰም። ሆስፒታሎች የኤሌትሪክ ኃይል የሚያገኙት በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ጀነሬተሮች ነው።

የፎቶው ባለመብት, MEDICAL AID FOR PALESTINIANS
120 ሕፃናት በማሞቂያ ክፍል ውስጥ ሲሆኑ ያለጊዜ የተወለዱ 70 ሕፃናት ደግሞ አጋዥ መተንፈሻ ተገጥሞላቸዋል ሲል እሑድ ዕለት ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል። ከዚህ ቀደም ጋዛ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከእስራኤል ነበር።
"120 አራስ ልጆች በማሞቂያ ክፍል ውስጥ አሉን። 70 አራስ ሕፃናት ደግሞ አጋዥ መተንፈሻ ተገጥሞላቸዋል” ሲሉ የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጆናታን ክሪክስ ተናግረዋል።
የፍልስጤማውያን የህክምና እርዳታ ድርጅት የጋዛ ዳይሬክተር ፊክር ሻልቱት አንዳንዶቹ ሕፃናት የተወለዱት በጦርነት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።
"እናቱ በአየር ድብደባ ከተገደለች በኋላ ዶክተሮች ሊያድኑት የቻሉት የ32 ሳምንት ህጻን አለ። እናቱ እና ቤተሰቡ በሙሉ ሞተዋል፤ ህጻኑ ግን ድኗል"ብለዋል።
ጄኔሬተሮቹ መስራት ካቆሙ ልጁ እና በክፍሉ ውስጥ ያሉ ያሉ ህጻናት ህይወታቸው ማለፉ እርግጥ ነው ብለዋል።
በህይወት ያቆያቸው የነዳጅ አቅርቦት በመመናመን ላይ ይገኛል።












