መስክ የትዊተር ግዢን አጠናቀው የኩባንያውን ኃላፊዎች ከስራ አሰናበቱ

የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር ኤሎን መስክ፣ የትዊተርን የ44 ቢሊየን ዶላር ግዥ ማጠናቀቁን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እና የኩባንያው ባለሃብቶች አስታወቁ።

መስክ የትዊተርን ግዢ እንዳጠናቀቁ ዋና ዋና የሚባሉ የኩባንያውን የሥራ ኃላፊዎች ማባረራቸው ተነግሯል።

መስክ ከስራ ካሰናበቷቸው መካከል የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓራግ አግራዋል፣ የፋይናንስ ኦፊሰር ኔድ ሴጋል እና የኩባንያው ከፍተኛ የሕግ እና የፖሊሲ ኃላፊ ቪጃያ ጋዴ እንደሚገኙበት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

መስክ በትዊተር ገጹ ላይ "ወፏ ነጻ ሆናለች" በማለት ትዊተር ግዢው መፈጸሙን አመላክቷል።

አሜሪካዊው ቢሊየነር ትዊተር የተሰኘውን የማኅበራዊ ትስስር ኩባንያ በ44 ቢሊየን ለመግዛት የገባው የውል ስምምነት አቋርጦ እንደነበር ይታወሳል።

መስክ ስምምነቱን ለማፍረስ በምክንያትነት የጠቀሱት ትዊተር ምን ያክል ሐሰተኛ ተጠቃሚዎች እንዳሉት በቂ መረጃ ሊሰጠኝ አልቻለም የሚል ነበር።

መስክ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ ኩባንያው ላይ ያለው ፍላጎት ገንዘብ መስራት ብቻ አይደለም ብሏል።

ትዊተር እስካሁን የማኅበራዊ ትስስር ኩባንያው ለመስክ ስለመተላለፉ ያለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ በኩባንያው ያሉ ቀደምት ባለሃብት ስምምነቱ መፈፀሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስምምነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አግራዋል እና የፋይናንስ ኦፊሰሩ ሴጋል ሳንፍራንሲስኮ ከሚገኘው የትዊተር ዋና መስሪያ ቤት መውጣታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የትዊተር የሥራ አስፈጻሚ አባል እና መስራች አባል ቢዝ ስቶንም፣ ለዋና ሥራ አስፈጻሚው አግራዋል፣ ሴጋል እና ጋዴ ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

እንደ ኒው ዮርክ ስቶክ ኤክስቸንጅ ድረ ገጽ ከሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ኩባንያው አክሲዮን ድርሻዎችም ዛሬ ለገበያ ከመቅረብ ይታገዳሉ።

ኤሎን መስክ የማሕበራዊ ሚዲያ ትስስር ኩባንያውን የገዛው ሰብዓዊነትን ለመርዳት እና የሰለጠነ እና የተለመደ የዲጂታል ከተማ አደባባይ እንዲኖር በመፈለጉ እንደሆነ ተናግሯል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ መስክ ሳንፍራንሲስኮ ወደሚገኘው የትዊተር ዋና መሥሪያ ቤት መታጠቢያ ሰሃን [ሲንክ] ይዞ ሲሄድ የሚያሳይ ቪዲዮውን በትዊተር ገጹ አጋርቷል።

በርካታ ተንታኞች፣ የብዙ ቴክኖሎጂ አክሲዮኖች ዋጋ ማሽቆልቆሉን እና የትዊተር ተጠቃሚዎችን ለመሳብ እና ለማሳደግ የሚያደርገው ትግል በጣም ከፍተኛ ነው በማለት መስክ ለኩባንያው አሁን የሚከፍለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ ይሟገታሉ።

በቅርቡም የቴስላ መስራች የሆነው መስክ፣ “ምንም እንኳን እኔን ጨምሮ ሌሎች ባለሃብቶች ለትዊተር ከልክ በላይ እየከፈልን ቢሆንም፣ ትዊተር ለረጂም ጊዜ የተዳከመ፣ ነገር ግን አስደናቂ አቅም ያለው ነበር” ብለዋል።