ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የሚያስቀይም ቃል ተጠቅመዋል ተባለ

የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ለመግለፅ እጅግ አስፀያፊ ቃል መጠቀማቸው ተሰምቷል።

ይህ መሆኑ ጳጳሱ ምናልባት ስለጉዳዩ ያላቸው አተያይ ምንድነው የሚለው አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

በጣሊያኑ የጳጳሳት ጉባዔ ላይ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ወንዶች ከወሲብ ርቀው ለቅስና ልምምድ መውሰድ ይችላሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ፍራንሲስ ይህ ሊሆን አይገባም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በጣሊያንኛ እያወሩ የነበሩት ሊቀ-ጳጳሱ 'ፍሮቺያጊኔ' የተሰኘውን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የሚውል አስፀያፊ ቃል ተጠቅመዋል ተብለዋል።

ምንም እንኳ ስብሰባው ዝግ የነበረ ቢሆንም የጣሊያኑ የምርመራ ዘገባ ድረ-ገፅ ዳጎስፒያ የፖፕ ፍራንሲስን ንግግር ይፋ አድርጓል።

ሌሎች የጣሊያን መገናኛ ብዙኃንም የተለያዩ ምንጮች እየጠቀሱ ሊቀ-ጳጳሱ ሌሎችን ሊያስቀይም ይችላል የተባለውን ቃል መጠቀማቸውን አረጋግጠዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ በዝግ ጉባዔው ላይ አሰምተውታል የተባለው ንግግር ብዙዎችን ያስደነገጠ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከዚህ በፊት በይፋ ወጥተው ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ያላቸው አመለካከት ለዘብ ያለ መሆኑን መግለፃቸው ብዙዎች ግራ እንዲጋቡ አድርጓል።

ተራማጅ የሆኑ የሊቀ-ጳጳሱ ደጋፊዎች ምንም እንኳ ቤተ-ክርስትያኗ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ይህ ነው የሚባል መብት ባትሰጥም፤ ፍራንሲስ ግን ያላቸው አመለካከት ለዘብተኛ ነው ሲሉ ይከራከሩላቸዋል።

ሊቀ-ጳጳሱ በተሾሙ ሰሞን ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ተጠይቀው "እኔ ማን ሆኜ ነው የምፈርደው?" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በቅርቡ ደግሞ የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያ ቀሳውስት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጥንዶችን ሊባርኩ ይገባል ማለታቸው ወግ አጥባቂ የሚባሉ የኃይማኖቱ መሪዎችን አስቆጥቶ ነበር።

ፖፕ ፍራንሲስ በአንዳንድ ንግግሮቻቸው ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ወደ ቤተ-ክርስትያኗ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበው ያውቃሉ።

ይህ መሆኑን ተከትሎ አንዳንዶች ምናልባት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የሆኑ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ወደፊት ቄስ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር። ይህን የሚያደርጉት ግን ልክ እንደሌሎቹ ቄሶች ከወሲብ ከራቁ ብቻ ነው።

ነገር ግን በዝግ ስብሰባው ላይ ይህንን ሐሳብ ውድቅ ከማድረጋቸውም በላይ ከአንድም ሁለት ሶስቴ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ሊያስቀይም የሚችል ንግግር ማድረጋቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ስፔንኛ ተናጋሪ የሆኑት ሊቀ-ጳጳሱ ምናልባት ጣሊያንኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ስላልሆነ ቃሉ ምን ያህል አስፀያፊ እንደሆነ አልተረዱት ይሆናል ሲሉ ደጋፊዎቻቸው ይከላከላሉ።

ፖፕ ፍራንሲስ ምንም እንኳ ጣሊያንኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ባይሆንም አርጀንቲና ውስጥ ጣሊያንኛ ተናጋሪ የሆኑ ቤተሰብ መሐል ነው ያደጉት።

ቫቲካን ይህን በተመለከተ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።