ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘ፈቃዱ አይታደስም’ በተባለው አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የተፈጠረው ምንድን ነው?
ከሰሞኑ የሦስተኛ ተርም ክፍያ ያልከፈሉ የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ወላጆች እና መምህራን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ አራት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ አቶ አለማየሁ ጌታቸው የተባሉ ወላጅ እንደሚሉት ባለፈው ዓመት 75 በመቶ ክፍያ ቢጨምሩም ቀድሞ የተገባላቸው ቃል አልተሟላም።
በዚህ ላይ የወላጅ ኮሚቴዎች ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ መልስ እስከሚሰጠን የሦስተኛ ተርም ክፍያ ሳንከፍል ቀረን የሚሉት አቶ አለማየሁ፣ በዚህም ምክንያት ያልከፈሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ እንዳይገቡ መከልከላቸውንና ቢቢሲ እስካነጋገራቸው ባለፈው አርብ ድረስ ሙሉ በሙሉ ትምህርት እየተሰጠ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ የትምህርት ክፍያ ላይ የ75 በመቶ ጭማሪ ያደረገው ለመምህራን ደመወዝ ለመጨመር ቃል በገባው መሠረት እንደነበር ያስታወሱት ወላጆች እና መምህራን፣ ይህ ግን እንዳልተፈፀመ ተናግረዋል።
“ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን አገልግሎትን ሳያሻሽል፣ ክፍያ እንድንጨምር ተጠይቀናል” ሲሉም ይከሳሉ።
የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት እና በዚያው ትምህርት ቤት ሦስት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት አቶ ተመስገን ሁሴንም ትምህርት ቤቱ ከክፍያ ባሻገር በበርካታ ጉድሎቶች የተቃወሰ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በዚሁ ጉዳይ ላይ ከትምህርት ሚኒስትሩ ጋር ከአንድም ሁለት፣ ሦስቴ መወያየታቸውን፤ ነገር ግን ትምህርት ቤቱ ጉድለቶቹን ባለማረሙ ኢንተርናሽናል [ዓለም አቀፍ] ፈቃዱ መነጠቁንም አቶ ተመስገን አስታውሰዋል።
የአንድነት የትምህርት እና ሥልጠና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳባ አታሮ (ኢንጂነር) በበኩላቸው ከወላጆች ስምምነት ውጪ የተጨመረ ክፍያም ሆነ ያልተሰጠ አገልግሎት የለም ሲሉ የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ የወላጅ ኮሚቴው “አትክፈሉ፣ አሊያም የከፈላችሁ ሰዎች እኛ በምንላችሁ አብራችሁ ቁሙ” የሚል እንቅስቃሴ አድርጎብናል ሲሉ ይከሳሉ።
የወላጆች ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተመስገን ግን ከዚህ ቀደም የተደረገውን 75 በመቶ ጭማሪ ቢከፍሉም ተማሪዎቹ መማሪያ መጽሐፍ የላቸውም፤ የሚያገኙት አገልግሎትም በቂ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።
ትምህርት ቤቱ በተደጋጋሚ ክፍያ የጨመረው ለመምህራን እስከ መቶ በመቶ ደመወዝ ለመጨመር እንደሆነ ገልጾላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ለመምህራኑ የተደረገው ጭማሪ አነስተኛ [10 በመቶ] በመሆኑ ሥራቸውን ለመልቀቅ የተገደዱ መኖራቸውን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ የሚገኙ ዓለም አቀፍ እና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ላይ መሰል ቅሬታ ሲነሳ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ከዚህ ቀደም ከአገሪቷ ሕግ ውጪ በውጭ ምንዛሬ የሚያስከፍሉ እንዲሁም ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ በመንቀሳቀስ በማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ከተመሠረቱ በኋላ ወደ ትምህርት ኢንቨስትመንት ተቀይረው ከፍተኛ ክፍያ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተዘግቧል።
ሌላኛው ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ በአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ልጃቸውን የሚያስተምሩ ወላጅ “ትምህርት ቤቱ ከሚያስከፍለው ያልተገባ ክፍያ በተጨማሪ የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ማነጽ ሲገባው ለተማሪዎች የባህርይ መበላሸት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል” ሲሉ ይከሳሉ።
በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የማይጠበቁ ነገሮች ከመስተዋላቸው በተጨማሪ አደንዛዥ እፅ እና አደገኛ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ተማሪዎች መበራከታቸውንም ይናገራሉ።
ላለፉት 11 ዓመታት በዚያው ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ የቆዩት እኝህ ወላጅ፣ አሁን ላይ ያለው ችግር ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እና በትምህርት ቤቱ ላይ ያላቸው እምነት በመሸርሸሩ ልጆቻቸውን ከእቅፋቸው አውጥተው በውጭ አገር ለማስተማር ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
“አገራችን ላይ ልጆቻችን በተገቢው መንገድ ማስተማር ካልቻልን፣ ያለንን ጥሪት አሟጠን ወደ ባሕር ማዶ ከማንጋጠጥ ውጪ ምን ማድረግ እንችላለን?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ ወላጅም “ትምህርት ቤቱ ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ ሲል” ለመምህራኑ የሚከፍለው አነስተኛ ደመወዝ በልጆቹ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
የመምህራን ደመወዝ ጭማሪ
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ መምህር ትምህርት ቤቱ በየሁለት ዓመቱ የተማሪዎች ክፍያ ላይ እና ለሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደረግ ገልጸው፣ በዚህም መሠረት በ2015 ዓ.ም. እስከ መቶ በመቶ ጭማሪ እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም ወላጆች ጭማሪ ባለማድረጋቸው ቃል የተገባላቸው ሳይፈጸም መቆየቱን ይናገራሉ።
ሆኖም በ2016 ዓ.ም. ትምህርት ቤቱ በትምህርት ክፍያ ላይ የ75 በመቶ ጭማሪ አድርጓል።
ወላጆች ይህንን ጭማሪ ለማድረግ የተስማሙትም ትምህርት ቤቱ በደመወዝ ማነስ ምክንያት መምህራን እየለቀቁብን ነው ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ለመፍታት እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ወላጆች እና ሦስት መምህራን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ “ከስምምነቱ ባነሰ ሁኔታ በትምህርት ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ የተገለጸልን እንደ ሥራ አፈጻጸማችን ከ10 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ እንደሚደረግልን ነው። ጭማሪው ቃል የተገባው እና የጠበቅነው አይደለም” ብለዋል መምህራኑ።
በትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራን ደመወዝ በአማካይ ከ12 እስከ 14 ሺህ ብር እንደሚደርስ የሚጠቅሱ አንድ መምህር፣ በ2016 ዓ.ም. የፒርሰን ሥርዓተ ትምህርት ከተጀመረ በኋላ የሥርዓተ ትምህርቱን ጫና ለመቋቋም በሚል ለመምህራን ብቻ የ2000 ብር ጭማሪ እንደተደረገ ይናገራሉ።
የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ግንቦት 14/2016 ዓ.ም የጻፈውና ቢቢሲ የተመለከተው ደብዳቤም፣ ትምህርት ቤቱ ለመምህራን ደመወዝ ለመጨመር ከወላጆች ጋር መግባባት ላይ ደርሶ ከመስከረም ወር ጀምሮ ከ75 እስከ 100 በመቶ የትምህርት ክፍያ ላይ ጭማሪ ቢያደርግም፣ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለመምህራን የተደረገው ጭማሪ ከ10 እስከ 40 በመቶ እንደሆነ ይገልጻል።
ይህም ከፍተኛ የተባለው 40 በመቶ የተጨመረላቸውም ጥቂት ሠራተኞች መሆናቸውን ደብዳቤው ይጠቁማል።
በደመወዛቸው ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መልስ አለማግኘታቸውን ደብዳቤው ያትታል።
ሥራ አስፈጻሚዋ ግን ባለፈው ዓመት ወላጅ ባልጨመረበት ጊዜ 15 በመቶ ጭማሪ መደረጉን አስታውሰው፣ በዘንድሮው ዓመትም በዝቅተኛ ከ45 እስከ 50 በመቶ፣ በመካከለኛ ከ45 እስከ 60 በመቶ፣ በከፍተኛ 80 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለበዓል ሦስት ሺህ ብር ጉርሻ መሰጠቱን ተናግረዋል።
የመምህራን መልቀቅ በሁሉም ትምህርት ቤት የሚያጋጥም መሆኑን የሚገልጹት ሥራ አስፈፃሚዋ፣ “ሌሎች ተመሳሳይ ሥርዓተ ትምህርት የሚተገብሩ ትምህርት ቤቶች ክፍያቸው ከፍ ያለ በመሆኑ መምህራንን በተሻለ ክፍያ ይወስዱብናል፤ ነገር ግን በተቻለን መጠን መምህራንን ለመያዝ ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል።
“15 ሺህ ብር ለመጽሐፍ ኪራይ”
ከመምህራን ደመወዝ ጭማሪ በተጨማሪ ትምህርት ቤቱ እየተገበረ ላለው የውጭ ሥርዓተ ትምህርት በቂ የመማሪያ እና ማስተማሪያ መጽሐፍት እንደሌሉትም በወላጆች እና በመምህራን ተነስቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ወላጆች እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ የሚጠቀመውን የውጭ ሥርዓተ ትምህርት ለማስተማር የሚውሉ የመማሪያ እና የመምህራን መምሪያ መጽሐፍ በበቂ ሁኔታ የሉትም።
በመሆኑም ለልጆቻቸው ትምህርት ከሚከፍሉት የተጋነነ ክፍያ በተጨማሪ ለመጽሐፍ ኪራይም እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ሦስት ልጆቻችውን በትምህርት ቤቱ እንደሚያስተምሩ የሚናገሩ አንድ ወላጅ፣ ለሁለት ዓመት ለሦስት ልጆቻቸው የመጽሐፍ ኪራይ 45 ሺህ ብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።
ለመጽሐፍት አቅርቦት አለመሟላት ከትምህርት ቤቱ አስተዳዳር የሚሰጣቸው ምክንያት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢሆንም ወላጆቹ ግን ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ነው ይላሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህራንም የፒርሰንን ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍትን ከኢንተርኔት እያወጡ ያስተምሩ እንደነበር እና በኋላ ላይም መጽሐፉ ቀድሞ እጃቸው ከገባ ጥቂት ተማሪዎች እየተዋሱ ያስተምሩ እንደነበር ይናገራሉ።
ሦስተኛው የትምህርት ተርም ላይ ትምህርት ቤቱ መጽሐፍ አምጥቶ የነበረ ቢሆንም ለሁሉም ተማሪዎች ማዳረስ እንዳልተቻለም መምህራኑ ገልጸዋል።
“ትምህርት ቤቱ ያመጣቸውን የሳይንስ፣ የእንግሊዝኛ እና የሒሳብ መጽሐፍት መውሰድ የቻሉት መከራየት የሚችሉት ብቻ ናቸው” ብለዋል።
አቶ አለማየሁ ጌታቸው የተባሉ ወላጅም ልጆቻቸው ሥርዓተ ትምህርቱን የሚማሩበት መማሪያ መጽሐፍ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
የአንድነት የትምህርት እና ሥልጠና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳባ አታሮ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ወላጆች በምዝገባ ጊዜ የመጽሐፍ ኪራይ ይከፍሉ እንደነበር አስታውሰው፣ ትምህርት ቤቱ ከወላጆች ጋር በመስማማት እየተገበረ ያለው የፒርሰን ሥርዓተ ትምህርት ከመጣ በኋላ ግን መጽሐፍ ለማግኘት ወላጆች እንደ አዲስ መክፈል እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ከመጽሐፉ አቅርቦት ጋር በተያያዘም መጽሐፉን የሚያስመጣው አካል 50 በመቶ ቅድመ ክፍያ መጠየቁን፣ ይህንንም ለወላጅ ኮሚቴ ማሳወቃቸውን፤ ነገር ግን በዚህ ዓመት የትምህርት ክፍያ ተጨምሮ ስለነበር መግባባት ላይ ሳይደረስ መቅረቱን ያስረዳሉ።
ወላጆች ትምህርት ቤቱ ራሱ መጽሐፉን እንዲያስመጣ መጠየቃቸውንም ይገልጻሉ።
ሥራ አስፈጻሚዋ እንደሚሉት ከሆነ በዚያን ጊዜ ለሁሉም የትምህርት ዓይነቶች እና ለሁሉም ተማሪዎች የሚያስፈለገው የመጽሐፍ ዋጋ ግምት 82.5 ሚሊዮን ብር ነበር።
ትምህርት ቤቱ መጽሐፉን የማስመጣት አቅም እንዲሁም የማስመጫ ፈቃድ ስለሌለው መጽሐፍ ማስመጣት አልቻለም ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ሥርዓተ ትምህርቱን እንዲተገብሩ የፈቀደላቸው የምሥራቅ አፍሪካው ተወካይ ለመምህራን የሚሆኑ መጽሐፍት በኦንላይን እንዲቀርቡ ማድረጉን ያነሳሉ።
ትምህርት ቤቱም በራሱ ወጪ ለሁሉም ተማሪዎች በዲጂታል መጽሐፍ እንዲመጣ አድርጓል የሚሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ መጽሐፍቱን ለማስመጣት ቢሞክሩም ለግዥ እና ለማስመጫ ወደ 600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መጠየቃቸውን፤ ይህንንም ገንዘብ ከባንክ ለማግኘት ተጨማሪ ከፍያ መጠየቃቸውን አስረድተዋል።
“ትምህርት ቤቱ መጽሐፍ ለማምጣት ማስተባበር ቢኖርበትም፣ መክፈል ግን የወላጆች ኃላፊነት ነው” ብለዋል ሥራ አስፈጻሚዋ።
አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ ላስመጣቸው መጽሐፍት [ከስምንተኛ ክፍል እስከ ፕሪፓራቶሪ ለአራት የትምህርት ዓይነት] ለሁለት ዓመት ኪራይ 15 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ቢጠየቁም፣ መጽሐፉን የወሰዱት 25 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች
በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከሚያስተምሯቸው አራት ልጆቻቸውን አንደኛው ልዩ ፍላጎት ያለው ተማሪ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አለማየሁ፣ ከመደበኛው በተጨማሪ ሌሎች ክፍያዎችን እንደሚከፍሉ፤ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የትምህርት ክፍሉ አስተባባሪ እንደሌለውና ልጆቹ ገብተው ዝም ብለው እንደሚወጡ ይናገራሉ።
“ከመደበኛው 75 በመቶ ጭማሪ በላይ 30 በመቶ ተጨማሪ እንከፍላለን፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ለመምህሩ 9 ሺህ ብር ተጨማሪ እከፍላለሁ” ይላሉ።
ሆኖም በከተማዋ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ “ትምህርት ቤቱ ይህንን እንደ መልካም አጋታሚ ተጠቅሞ እየበዘበዘን ነው” ሲሉ ይከሳሉ።
በትምህርት ክፍሉ ከዚህ ቀደም አስተባባሪ ሆነው ሲሰሩ የነበሩትን ግለሰብ ተክተው እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹ የትምህርት ክፍሉ አስተባባሪ ሙሉእመቤት አሰፋ ግን የክፍያ ሥርዓቱ ከቀደመው የተለየ አለመሆኑንና ወላጆች ሳይስማሙበት የተደረገ ክፍያ አለመኖሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ ተማሪዎች የሚማሩበት የተለየ ሥርዓተ ትምህርት ባይኖርም፣ የተማሪዎቹን ፍላጎት እና አቅም ባገናዘበ መልኩ በትምህርት ቤቱ በሚቀረጹ የማስተማሪያ ዘዴዎች ትምህርቱ እየተሰጠ እንደሆነ አስተባባሪዋ አብራርተዋል።
ወላጆች ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ የሆነውም ልጆቹ ካላቸው ፍላጎት አኳያ ሊሟሉላቸው የሚገቡ ነገሮች ከሌሎቹ ተማሪዎች የተለየ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ትምህርት ቤቱ ማግኘት ያለበትን ትቶ ነው ለልጆቹ ይህንን የትምህርት ዕድል ያመቻቸው” ሲሉም ወላጆቹ ያቀረቡትን ቅሬታ አጣጥለዋል።
እንደ ሙሉእመቤት ከሆነ በትምህርት ቤቱ ውስጥ 56 ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ይማራሉ።
“ተደባዳቢ ገዝተው የሚመጡ ተማሪዎች”
የትምህርት ቤቱ አስተዳዳር የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ለማነጽ ያለበትን ጉድለት ተከትሎ ተማሪዎች እርስ በእርስ የሚደባደቡበት ሁኔታ መፈጠሩን ወላጆች ይናገራሉ።
በአንዳንድ ሁኔታዎችም የተጣሉ ተማሪዎች ከውጭ ተደባዳቢ ገዝተው ልጆችን ማስደብደብ መስተዋሉንም ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አደንዛዥ እፆች እና መድኃኒቶች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ወላጆቹ ትዝብታቸውን አጋርተዋል።
“ትራማዶል የሚባለው ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የማይሸጥ መድኃኒት በትምህርት ቤቱ ውስጥ በ50 ብር እንደሚሸጥ፣ ማሪዋና የተባለ እፅ ሳይቀር ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ውስጥ እንደሚጠቀሙ ከልጆቻችን ሰምተናል” ብለዋል ወላጆች።
ይህ ሁኔታ የተፈጠረው በትምህርት ቤቱ አስተዳዳር የላላ ቁጥጥር ምክንያት ነው ሲሉም ይወቅሳሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ መምህርም እንደሚሉት በትምህርት ቤቱ ባለው የአስተዳደር ችግር ምክንያት የሚለቁ መምህራን በመበራከታቸው የማይሸፈኑ ክፍለ ጊዜዎች አሉ።
በዚህም ምክንያት ከግቢ ውጪ የሚወጡ እና በግቢ ውስጥም ላልተገባ የሥነ ምግባር ችግር የሚጋለጡ ተማሪዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
በልጆች ሥነ ምግባር ላይ የወላጆች ሚና የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም፣ የመምህራኑ ደስተኛ አለመሆንና ቁጥጥሩ የላላ መሆን ለልጆቹ ሥነ ምግባር መበላሸት ምክንያት እንደሆነም ይናገራሉ።
“አደንዛዥ እፅ የመጠቀም አዝማሚያዎች አሉ። ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይታያሉ። ፍተሻዎች ቢደረጉም በረቀቀ ሁኔታ ቦርሳቸው ውስጥ ይዘው በመምጣት የሚጠቀሙ መኖራቸውን ታዝበናል። እነዚህ ተማሪዎች ግን ጥቂት ናቸው” ይላሉ።
ከትምህርት ቤት በመቅረት በቡድን መደባደብ እና ገንዘብ በወለድ መበዳደር በዕድሜ ከፍ ያሉ ልጆች ላይ እንደሚስተዋል ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህራን ገልጸዋል።
ሥራ አስፈጻሚዋ በበኩላቸው የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ለማነጽ የወላጅም ሚና ወሳኝ መሆኑን አስምረው፣ በትምህርት ቤቱ በኩል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
“የደኅንነት ካሜራዎች አሉ። አርተፊሻል ሲጋራ ሲያጨሱ የተገኙ ተማሪዎች አሉ። ነገር ግን የተጋነነ ችግር አይደለም ያለው” ሲሉም ከድርጊታቸው ባልታረሙ ተማሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢያንስ 20 የሚደርሱ ተማሪዎች በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ከትምህርት ቤቱ መባረራቸውን ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
ከድብድብ ጋር በተያያዘም ለፈተና ብቻ እንዲመጡ የተደረጉ እና ቤታቸው ተቀምጠው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።
“እነዚህን ልጆች እንወዳቸዋለን። አስፈላጊው እርዳታ እና ክትትል እናደርግላቸዋለን” ሲሉም ይህ ችግር በጋራ መታገልን የሚጠይቅና የትምህርት ቤቱ ብቻ ሳይሆን አገራዊም ዓለም አቀፋዊም ችግር መሆኑን አብራርተዋል።
አሁን ላይ በወላጆች እና በመምህራን ከፍተኛ ቅሬታ እየተነሳበት ያለው አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት፣ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ቅሬታ ቀርቦበታል።
ትምህርት ሚኒስቴር መጋቢት 04/2016 ዓ.ም. ለትምህርት ቤቱ በጻፈው ደብዳቤም በትምህርት ቤቱ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው ትምህርት ቤቱ ለ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የሚያቀርበው የፈቃድ እድሳት ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጿል።
የትምህርት ቤቱ ሥራ አስፈጻሚም ይህንን አረጋግጠው፣ “ትምህርት ቤቱ የተመሠረተውም ሲሠራ የቆየውም ኢንተርናሽናል ሆኖ ስለሆነ ፈቃዱን ለማሳደስ ጥረት እያደረገ ነው። ፈቃዱ ይመለስለታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በሒደት ላይ ነው” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ የግል እና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ላይ ተመሳሳይ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር።
ከሦስት ዓመት ገደማ በፊትም ሁለት የግል ትምህርት ቤቶች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የክፍያ መመሪያ ተላልፈው በመገኘታቸው በጊዜያዊነት ታግደው ነበር።
እነዚህ ትምህርት ቤቶች አንድነት ኢንተርናሽናል እና ሄሌኒክ-ግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ነበሩ።
አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በተለያዩ የክፍል ደረጃዎች የሚገኙ ከሁለት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስተምራል።