በአዲስ አበባ ተገቢ ያልሆነ የክፍያ ጭማሪ በሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

በአዲስ አበባ ተገቢ ያልሆነ ጫና እና የትምህርት ክፍያ ጭማሪ በሚፈፅሙ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤት ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በርካታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ተረድቻለሁ ብሏል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለትምህርት አገልግሎት እና ምዝገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት እና ስልጠና ጥራት ፣ የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ባለስልጣን ባወጣዉ የማስፈጸሚያ ማኑዋል መስረት እየሰሩ አይደለም ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ያለውን ወሳኝና አስቸጋሪ ወቅት መሆኑን አስታውቆ ይህንንም በጋራ ለማለፍ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል።

"አሁን ባለንበት ወቅት ተደጋግፈን የምናልፍበት እንጂ አንዱ በሌላዉ ላይ ጫና የሚፈጥርበት አይደለም" ብሏል።

በዚህም መሰረት የግል ትምህርት ቤት ከደንበኞቻቸው ጋር በመነጋገር እና በመግባባት እንዲሰሩ አሳስቧል።

ነገር ግን ይህንን ተላልፈው በሚሰሩና በሚቀርበው ጥቆማ መሰረት ፈጣንና የማያዳግም እርምጃ ቢሮ ለመውሰድም እንደሚገደድ አሳስቧል።

ከዚህ ቀደም ለቢሮው እና ለወላጅ ምላሽ በመስጠታቸዉ እና የማስተካከያ እርምጃ በመውሰዳቸዉ በ41 ትምህርት ተቋማት ላይ ተጥሎ የነበረዉ እገዳ እንዲነሳላቸዉ እና አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አስታውሷል።

ቢሮው የግል ትምህርት ተቋማቱ የትምህርት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ እና ለከተማው ነዋሪ የስራ እድል ከመፍጠር ረገድ ሚናቸው ላቅ ያለ ነው ብሏል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የተቀመጡትን መመሪያዎች በማክበር ላከናወኑት ተግባርም እውቅና ሰጥቷል።