በአዲስ አበባ ለሶስት ወራት ያህል የቤት ኪራይ ጭማሪ ታገደ

በአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ለዘጠና ቀናት መጨመር እንደማይቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አስታውቋል።

አስተዳደሩ በማህበራዊ ትስር ገፁ በትናንትናው እለት እንዳስታወቀው የቤት ኪራይ ጭማሪን ለማገድ በቀረበ ደንብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

በደንቡ መሰረትም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለሶስት ወራት ተከልክሏል ብሏል።

ደንቡ ከፀደቀበት ነሐሴ 18፣ 2013 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።

አስተዳደሩ ይህንን ደንብ ለማውጣት ምክንያቱም አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በቤት ኪራይ ላይ ዋጋ ጭማሬ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ በመሆኑ ነው ብሏል።

ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ባሻገር አለግባብና የወቅቱን ሁኔታ ያላገናዘበ የቤት ኪራይ ጭማሪ የነዋሪውን ሕይወት በእጅጉ እየፈተነው እንደሚገኝም አስፍሯል፡

እየታየ ያለውን አላግባብ የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ለመገደብና የነዋሪውን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነም አስፍሯል።

በዚሀ መሰረት በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ጭማሪ ባደረገ አካል ላይ በደንቡ ተዘርዝሮ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆኑም ተቀምጧል።

በከተማዋ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ እንደሆነ ገልፆ ምንም እንኳን ይህ በአብዛኛው አሳማኝ እና ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለውና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የተፈጠረ ነው ብሏል።

ይህ የኑሮ ውድነትም የከተማውን ነዋሪ ለከፍተኛ ችግር እንዳደረገም ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍና የዜጎች የኑሮ ጫና እንዲቀንስ የተለያዩ እርምጃዎችንም እየወሰደ ነው ተብሏል።

በ2012 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በርካቶች ችግር ውስጥ በገቡበት ወቅት የከተማው ነዋሪዎች እርስ በርስ ከመረደዳት በተነሳ መንፈስ ቤት አከራዮች የወራት የቤት ኪራይ ዋጋ ለተከራይ በራሳቸው ተነሳሽነት ቀንሰው ችግሩን በጋራ ለመፍታት መሞከራቸውን አውስቷል። በወቅቱም በህግ ተቀምጦ የነበረውን የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር የሚከለክለውን ድንጋጌ ሳይጨምር ነው ይህም የመተበባር ስሜት እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል።