ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በጣልያን ሙሉ ወጪን የሚሸፍን የትምህርት ዕድል እንዴት ማግኘት ይችላሉ?
የትም ይሁን የት መማር ደግ ነው።
የተሻለ ተማሪ ቤት መገኘት ደግሞ ዕድለኝነት ነው።
ዕድሉ ከተገኘስ?
ሙሉ ወጪ ተሸፍኖ፤ የኪስ ገንዘብ ተጨምሮ በተሻለ ቦታ መማርን ማን ይጠላል? - ማንም።
ጥያቄው ግን ይህ ዕድል እንዴት ይገኛል የሚል ነው?
አቤኔዜር ታረቀኝ በጣልያኗ ፒሳ ከተማ ትምህርቱን እየተከታተለ ነው።
ፒሳ የሂሳብ፣ የሥነ ፈለክ እና የፍልስፍና ሊቁ ጋሊሊዮ ጋሊሊ መገኛ ናት።
ከተማዋ በ11ኛው ክፍለ ዘመን በተገነባው እና በዘመመው ማማም ስሟ ዝነኛ ነው።
ምን አልባት፣ ከዚያ ቀጥሎ የዩኒቨርሲቲዎች ከተማ በመሆኗ ትታወቃለች።
ከጠቅላላ ነዋሪው የተማሪው ቁጥር እንደሚልቅ በሚነገርባት ፒሳ ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ።
በእነዚህ ለክፍለ ዘመናት በቆዩ ዩኒቨርሲቲዎች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።
በከተማዋ ከአራቱም የዓለም ማዕዘናት የተሰባሰቡ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ይገኛሉ።
የሚበዙት ደግሞ በ‘ስኮላርሺፕ’ የሚማሩ ናቸው።
አቤኔዘርም ከእነዚህ ተማሪዎች አንዱ ነው።
በምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ስሬ በተሰኘች ከተማ ተወልዶ ያደገው አቤኔዘር በልጅነት ዘመኑ ቀለሜ የሚባል ዓይነት ተማሪ ነበር።
ከ1ኛ እስከ 12ኛ እዚያው ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተምሮ በ2006 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሏል።
በ2012 ዓ.ም. ደግሞ በህክምና ተመረቀ።
ከምርቃት በኋላ በኮሮናቫይረስ ህክምና ማዕከል ውስጥ ሠርቷል።
ከዚያ ቀጥሎ ወደ ፒሳ አቅንቶ በኒውሮሳይንስ በሁለተኛ ዲግሪ ሙሉ ወጪው ተሸፍኖ እየተማረ ነው።
አቤኔዘር ይህንን ዓይነቱን ዕድል ጊዜ ወስዶ በኢንተርኔት ሲፈልግ ቆይቷል።
ሆኖም ጓደኛው በተመሳሳይ የትምህርት መስክ በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ዕድሉን ማግኘቱ ነገሮችን ቀላል አድርጎለታል።
አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ረድኤት ሌንጮ ሮም የሚገኘውን ሳፒያንሳ ዩኒቨርሲቲን ከተቀላቀለች አንድ ዓመት አልፏታል።
በዩኒቨርሲቲው በማኅበራዊ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ስትከታተል ከእሷ ኪስ የሚወጣ ነገር የለም። የትምህርት ዕድሉን ኮመን አፕ (common app) በተሰኘ መተግበሪያ በኩል አግኝታዋለች።
በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒሳ ባዮሮቦቲክስ የሚማረው ብሩክ አስራት ደግሞ ዕድሉን ከጓደኞቹ ጋር በጋራ እየፈለገ እየተጠያየቀ ነበር ያገኘው።
በቢሾፍቱ ከተማ ያደገው ብሩክ በ2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሜዲካል ኢንጅነሪንግ ተመርቋል።
ቀጥሎም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ረዳት መምህር ሆኖ ለሁለት ዓመታት ሠርቷል።
በእነዚህ ጊዜያት “ስኮላርሺፕ ማፈላለግ ዋነኛ ሥራዬ ነበር” ይላል።
ከሳንታ አና ዩኒቨርሲቲ በሙሉ ስኮላርሺፕ በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቀው አፈወርቂ ዮሐንስ ደግሞ ይህንን የትምህርት ዕድል ከሌሎቹ በተለየ መንገድ ነበር በእጁ ያስገባው።
መቀለ ተወልዶ ያደገው አፈወርቂ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበር።
በዚያ ወቅት በፈጠረው ትውውቅ አማካኝነት ዕድሉን አግኝቷል።
አሁን በሳንታ አና ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ዶክትሬት ተመራማሪ የሆነው አፈወርቂ ቀደም ብሎ ኔዘርላንድስ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን በስኮላርሺፕ ተምሯል።
አራቱም ተማሪዎች በተለያየ መንገድ ጣልያን ላይ ለትምህርት ተገኝተዋል።
ሁሉም ተማሪዎች ፍላጎቱን ለሚያውቅ፣ የሚጠበቅበትን ለሚያደርግ እና ጊዜ ለሰጠው ሰው በጣልያን የትምህርት ዕድል ማግኘት ከባድ አይደለም ይላሉ።
ዕድሎች እንዴት ይገኛሉ? የሚያገጥሙ ስህተቶች ምንድን ናቸው? ሂደቱ ምን ይመስላል?
በጣልያን የትምህርት ዕድሎች የሚገኙበት መንገድ
ተማሪዎች ለትምህርት ወደ ጣልያን የሚገቡበት መንገድ ብዙ ነው።
የተለመደው ግን ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጡትን ማስታወቂያ ተከትሎ ነው።
እነዚህ ማስታወቂያዎች ጊዜያቸው የተለያየ ብቻ ሳይሆን በቁጥርም የበዙ ናቸው።
ታዲያ አንድ ተማሪ የሚፈለገውን ትምህርት እና ዩኒቨርሲቲ ከእነዚህ ሁሉ መካከል እንዴት ማግኘት ይችላል?
አቤኔዘር እንደሚለው የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት “ተማሪው የሚፈልገውን ኮርስ ማወቅ ነው።”
ቀጥሎ ይህንን ትምህርት የትኛው ዩኒቨርሲቲ፣ በየትኛው ቋንቋ እንደሚሰጥ እና ወጪን እንደሚሸፍን ማረጋገጥ ነው።
“አንድ ሰው ስኮላርሺፕ ለመፈለግ ሲነሳ፤ መጀመሪያ ምንድን ነው የምፈልገው? ከዚያ በኋላ ያ መማር የሚፈልገው ትምህርቶች የት የት ዩኒቨርሲቲ ይሰጣል? የሚለው ነው። ይኼ ሁሉ እጁ ላይ ያለ ነው ሌላ ሦስተኛ ወገን ሳይገባ መጨረስ ይችላል” የሚለው አቤኔዘር ነው።
“አሁን ኢንተርኔት እጃችን ላይ አለ። ከእኛ የሚጠበቀው የምንፈልገውን ነገር ጽፈን መፈለግ ነው። ለምሳሌ ጣልያን ውስጥ በእንግሊዝኛ የሚሰጡ ኮርሶች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ልናውቅ የምንችለው ሰርች (ስንፈልግ) ስናደርግ ነው” ሲል ያስረዳል።
ይህ መንገድ ለትምህርት ዕድል ፈላጊዎች ልፋትን ያቀላል።
ብሩክ እሱ መቀጠል የሚፈልግበት የትምህርት መስክ በአገር ውስጥ ማግኘት አልቻለም።
“አንዴ አቅጣጫዬን መርጫለሁ። መቀጠል ያለብኝ በትምህርት መሆን እንዳለበት ስላመንኩኝ ዕድሎችን በደምብ መከታተል ጀምሬያለሁ” ይላል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበረበት ወቅት ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር እያወራ፣ እየጠየቀ ዕድሉ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል አውቋል።
በዚህ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒሳ እሱ የሚፈልገው ዓይነት ዕድል እንዳለው ተረዳ።
ከዚያም የማመልከቻ ቀኑን ለማወቅ የዩኒቨርሲቲውን ድረ ገጽ እና ማኅበራዊ ገጾች መከታተል ጀመረ።
“ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒሳ የተለያዩ ዲፓርትመንት ጥሪዎችን የጨረሻ ቀን ያወጣል። ‘ቀኑ ሳያልቅባችሁ ከዚህ እስከ እዚህ’ ተመዝገቡ እያሉ ያስተዋውቃሉ” የሚለው ብሩክ የዩኒቨርሲቲው የኢንስታግራም ገጽ ለዚህ ቀላል እንደሆነ ያስረዳል።
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት በተዘጋበት ወቅት ረድኤት የውጪ አገራትን የትምህርት ዕድል ስትመለከት ነበር።
ያኔ ገና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት አልወጣም ነበር።
“መጀመሪያ ትከረቴን የሳቡት አሜሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ። ምክንያቱም እነሱ የ12ኛ ክፍል ውጤት አይጠይቁም ነበር” ትላለች።
ረድኤት የትምህርት ዕድሎች በምታፈላልገበት ጊዜ ኮመን አፕ (common app) የተሰኘ መተግበሪያ ነገሮችን ቀላል አድርጎላታል።
በዚያ መተግበሪያ አማካኝነት የማመልከቻ ክፍያ የማይጠይቁ ዕድሎችን ስትፈልግ ነበር።
“ምክንያቱም ማመልከቻዬን ይቀበሉት አይቀበሉት እርግጠኛ አይደለሁም። ሁለተኛ ደግሞ 75 እና 80 ዶላር ለእኔ በጣም ብዙ ነው” ስትል ተገልጻለች።
ኮመን አፕ በተማሪው ፍላጎት መሠረት በዓለም ዙሪያ ያሉ የትምህርት ዕድሎችን ይዘረዝራል። የማመልከቻ ጊዜ እና አስፈላጊ መረጃዎችን ይጠቁማል።
ረድኤት ‘ቶፍል’ ወይም ‘አይ ኤል ቲ ኤስ’ [በውጭ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ለመግባት የሚጠየቁ ፈተናዎች] የማይጠይቁ ዕድሎችን በዚሁ መተግባሪያ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ታስረዳለች።
የ12ኛ ክፍል ውጤት ሲወጣ ደግሞ በርካታ ዕድሎችን የምታይበት አጋጣሚ ፈጠረላት።
“ዕድሌን ለማስፋት ብዙ ቦታ ስሞክር ነበር” ስትል ትጠቅሳለች።
በርካታ ተማሪዎች ዕድሉን የሚያገኙት አቤኔዘር፣ ብሩክ እና ረድኤት ባገኙት መንገድ ቢሆንም ሌሎች መንገዶችም አሉ።
ለምሳሌ አፈወርቂ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበረበት ወቅት ለጥናት ወደ ትግራይ ክልል ከሄደ ፕሮፌሰር ጋር በፈጠረው ትስስር የትምህርት ዕድል አገኝቷል።
በግብርና የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው አፈወርቂ የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በተለያዩ ምክንያት ኢትዮጵያ ሊመጡ ወይም ስለ ኢትዮጵያ መረጃ ሊፈልጉ እንደሚችሉ ያነሳል።
“አንዳንድ ጊዜ አጥኚዎች በሚመጡበት ጊዜ ከእነሱ ጋር ስትተዋወቅ፣ በተግባር ያንተን ብቃት እና ፍላጎት ያያሉ። ስለዚህ በግልም [ወደ ሚያስተምሩበት ተቋም] ሊወስዱህ ይችላሉ። ያ የሚሆነው ግን እነሱ ለጥናት ሲመጡ ከእነሱ ጋር መተዋወቅ፣ ያለህን አቅም ማሳየት ስትችል ነው” ይላል።
የትምህርት ዕድል ዓይነቶች
የጣልያን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በየዓመቱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ እንደሚያገኙ ያመለክታል።
እነዚህ የትምህርት ዕድሎች አንዳንዶች የተማሪውን የትምህርት ብቃት የሚመለከቱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ መስፈርቱን የሚያሟሉ ግን አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ላይ ያነጣጥራሉ።
በዚህ መሠረት በጣልያን ሦስት ዋነኛ ሙሉ ወጪን የሚሸፍኑ የትምህርት ዕድል ዓይነቶች አሉ፡
‘ኢንቨስት ዩር ታለንት’፡ ይህ የነጻ የትምህርት ዕድል በጣልያን ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር አማካኝነት የሚቀርብ ነው። በተጨማሪም የጣልያን ንግድ ኤጀንሲ እና ንግድ ምክር ቤትም ይደግፉታል።
‘ኢንቨስት ዩር ታለንት’ ከ130 በላይ የድኅረ ምረቃ የትምህርት ዘርፎችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ይሸፍናል።
በኢንጂነሪንግ፣ በአድቫንስድ ቴክኖሎጂስ፣ በኪነ ህንጻ፣ በዲዛይን፣ በኢኮኖሚክስ እና በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፎችን ዕድሎችን ይሰጣል።
እነዚህን የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎች በጣልያን በሚገኙ የተመረጡ የሙያ እና የቀለም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲከታተሉ ያስችላል።
ይህ ዕድል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ17 አገራት የሚመጡ ዕድሜያቸው ከ26 ዓመት የማይበልጥ ተማሪዎችን ይቀበላል።
‘ኢንቨስት ዩር ታለንት’ በየዓመቱ ከታኅሣሥ 21 እስከ የካቲት 22 ባለው ጊዜ ለማመልከት ክፍት ነው። ሆኖም የማመልከቻ ቀናቱ ከዓመት ዓመት ሊለያይ ይችላል።
የጣልያን መንግሥት ስኮላርሺፕ፡ ይህ ስኮላርሺፕ በጣልያን በርካታ ተማሪዎችን የሚያካትት እና ትልቁ ነው። በተመሳሳይ ዕድሉ በጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በገንዘብ የሚደግፈው ነው።
በዚህ ዕድል በርካታ የትምህርት ዘርፎች የተካተቱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ120 አገራት ተማሪዎች የተከፈተ ነው። ዕድሜያቸው ከ29 በታች የሆኑ ተማሪዎች በዚህ ዕድል መጠቀም ይችላሉ።
ይህኛው የትምህርት ዕድል የማመልከቻ ጊዜው በሰኔ ወር ይከፈታል። የዚህ ዓመት የማመልከቻ ጊዜ ሰኔ 13/2016 ዓ.ም ይጀምራል።
የክልል መንግሥታት ስኮላርሺፕ፡ ይህ ዓይነቱን የትምህርት ዕድል የጣልያን ግዛቶችን የሚያስተዳድሩ መንግሥታት በገንዘብ የሚደግፉት ነው። ዕድሎቹ መንግሥታቱ ባለችው አቅም እና ፍላጎት መሠረት በሚቀበሉት የተማሪዎች ብዛት፣ የትምህርት ዓይነት፣ የሚሸፍነው ወጪ እና የማመልከቻ ጊዜ ይለያያል።
በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ወይም በሃይማኖት ተቋማት በኩል የሚሰጡ የትምህርት ዕድሎችም አሉ።
የትምህርት ዕድሎቹ ትክክለኛ መረጃ እና ‘ሊንክ’ በጣልያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር፣ በትምህት ሚኒስቴር እና አንዳንዴም በኤምባሲዎች ድረ ገጽ ይገኛል።
አስፈላጊ ሰነዶች እና ማስረጃዎች
አንዳንድ አመልካች የስኮላርሺፕ ማስታወቂያ ካገኘ በኋላ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በጥንቃቄ ማንብብ እንደሚገባ ተማሪዎቹ ያነሳሉ።
ከማመልከት በፊት የተዘረዘሩ ሰነዶችን (list of documents) “በእጃችንን መኖሩን እርግጠኛ መሆን ይገባናል” የሚለው አፈወርቂ ነው።
አፈወርቂ ሁለተኛ ዲግሪውን በኔዘርላንድስ በስኮላርሺፕ ነበር የተማረው።
“የሚያስፈልገውን ሰነድ ሳታዘጋጅ ወደ ስኮላርሺፕ ስትሄድ በጣም ስለሚንዛዛ [ሂደቱ] ተስፋ ያስቆርጣል። ረዥም ነው ብሎ የሚተወው ብዙ ሰው አለ” ሲል አክሏል።
አቤኔዘርም ይህንን ሀሳብ ይጋራዋል።
ለማመልከት “ከመጣደፍ” ይልቅ መመሪያዎችን በሚገባ ማንብበ ነገሮችን ያቀላል ይላል።
“እያንዳንዱን ማንበብ አለብን ኮርሱ ምንድን ነው? መቼ ነው የሚጀምረው? ምን ዓይነት ሰነድ ማቅረብ አለብን ሚለውን ማየት አለብን። ድረ ገጾቹ ላይ ሁሉም ነገር አለ። [እሱን] ቁጭ ብሎ ማንበብ እና መረዳት [ያስፈልጋል]” ሲል ያስረዳል።
ብሩክ በተለይ የሚቀርቡ የትምህርት/ሥራ ማስረጃ (CV) በሚዘጋጅበት ወቅት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላል።
“በኋላ ሲቪ ላይ እንዲህ እንዲህ ብለሃል፣ እንዴት ነው አብራራልን ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ላይ መጠንቀቅ ይኖርብናል” ሲል ይመክራል።
በተጨማሪም የፍላጎት መግለጫ ጽሁፍ (Motivation letter) እና የምስክርነት ጽሁፍ (recommendation letter) ዓይንት ሰነዶችም እውነታውን የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይገባል ይላል።
ተማሪዎች የተሳተፉባቸውን ክበቦች እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሁም የወሰዷቸውን ሥልጠናዎች መጥቅስ የተሻለ ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ ረድኤት ትናገራለች።
“ለምስሌ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ምንም የሥራ ልምድ ላይኖረው ይችላል። ግን የወሰድነው ኮርስ ካለ [ብንጠቅሰው] የተሻለ ተቀባይነት ለማግኘት ይረዳል” ስትል ትናገራለች።
ጨምራም ለትምህርቱ ያለን ፍላጎት በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ መገለጽ ይገባዋል ትላለች።
በዩኒቨርሲቲ ተቀባይነት ማግኘት እና ስኮላርሺፕ
አንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ከቅበላ ጋር ነጻ የትምህርት ዕድል ያቀርባሉ። ስለዚህ ሁለት የተለያየ ማመልከቻ ማስገባት አይጠበቅም አንዳንዱ ደግሞ ተማሪውን እንደተቀበሉት ይገልጹና ወጪን እንደማይሸፍኑ ያሳውቃሉ።
ረድኤት የጣልያን የትምህርት ዕድልን በዚህ መልኩ ነበር ያገኘችው።
የሚቀበላትን ዩኒቨርሲቲ ካገኘች በኋላ ወጪዋን የሚሸፍኑላት ዕድል ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ባለበት ክልል ፈልጋ አግኝታለች።
ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የሚቀበሉበት ጊዜ እና ስኮላርሺፕ የሚቀርብበት ጊዜ ሊለያይ አይገባውም።
አቤኔዜር የገጠመው ጥሩ ምስሌ ነው።
ወደ ፒሳ ለትምህርት ከመሄዱ አስቀድሞ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ በጀርመን የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎት ነበር።
አቤኔዘር በፒሳ ያገኘው ዕድል የኪስ ገንዘብን ጨምሮ በዓመት 9 ሺህ 200 ዩሮን ይሸፍናል።
“ፈተናውን አልፌ ዩኒቨርሲቲው ተቀብሎኝ ነበር። ግን አልተቀበልኩትም ምክንያቱም ስኮላርሺፕ አልነበረውም። በራሴ ለመማር ደግሞ አቅም የለኝም” ብሏል።
ብሩክም እንዲሁ የማመልከቻ እና የዩኒቨርሲቲውን የቅበላ (admission) ጊዜ በማጣጣም አመልክቷል።
የፒሳ ከተማን የሚያጠቃልለው የቱስካና ግዛት መንግሥት የሚሰጠውን ዕድል ያገኘ ሲሆን፣ ከትምህርታዊ እና የቤት ክፍያ ውጪ 5 ሺህ 700 ዩሮን የሚሸፍን ዕድል አግኝቷል።
ብሩክ አመልካቾች የቅበላ ጊዜን ከስኮላርሺፕ ጋር እያስተያዩ ዕድሎችን መፈለግ እንዳለባቸው ይጠቅሳል።
“አድሚሽን አገኘህ ማለት መጣህ ማለት አይደለም። ዋናው ነገር ስኮላርሺፑ ነው” ይላል።
እናም ተማሪዎች የትምህርት ዕድል ሲፈልጉ ወጪን የሚሸፍን እንደሆነ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
ያ ካልሆነ ደግሞ ባመለከቱበት ወቅት ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን የሚቀበሉ ስኮላርሺፕ መኖራቸው ማጣራት አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ደረጃ ወይም ‘Rank’ በዚህ ሂደት ወሳኝ ነው።
ምክንያቱን ተማሪዎቹ ሲያስረዱ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በቀላሉ ይቀበላሉ።
መቀበላቸው መልካም ነው።
ችግሩ ግን ለእነዚህ ተቋማት ክፍያን የሚሸፍን ስኮላርሺፕ ማግኘት ነው።
ስኮላርሺፕ በምን ምክንያት ላይሳካ ይችላል?
ይህ ጥያቄ አጭር መልስ የለውም።
ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መስፈርቶች አመልካቾችን ይመርጣሉ።
ሆኖም አመልካቾች የሚያቀርቧቸው ሰነዶች እና የቃል ፈተናው ስኮላርሺፑን ማግኘት ወይም ማጣትን እንደሚወሰኑ ተማሪዎቹ ይናገራሉ።
ብሩክ ወደ ቃል ፈተና ሲሸጋገር ከጠበቀው የተለየ ነገር ገጥሞታል።
“ጣልያን ውስጥ ያለው ኢንተርቪው ኢትየጵያ ካለው ይለያል። ያኔ መረጃውን አልነበረኝም። እኔ ተዘጋጅቼ የነበረው ለተለመዱ ጥያቄዎች ነበር። [ስቀርብ ግን] ወደ ስድስት ፕሮፌሰሮች ነበሩ። መጀመሪያ ራሴን አስተዋወቅኩኝ። ከዚያ ቀጥታ ስለ መመሪቂያ ጹሁፌ ነው የጠየቁኝ። በመጀመሪያ ዲግሪ ከተማርነው ነገር ጋር የሚገናኝ ነገር ጠይቀውኛል። በጣም የሚያተኩሩት ከትምህርት ጋር የሚያያዝ ነገር ላይ ነው” ሲል ይገልጻል።
የተማሩትን፣ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በሚገባ የተረዱ አመልካቾች በዚህ ሂደት ውስጥ በቀላሉ አሸናፊ እንደሚሆኑ ብሩክ ይናገራል።
ሌላኛው ጉዳይ የሚቀርበው የትምህርት ማስረጃ እና ሰነድ ነው።
ብሩክ ተማሪዎች በሚያመለክቱበት ጊዜ የሚያመለክቱበትን የትምህርት ክፍል ዩኒቨርሲቲ መሠረት ያደረገ ጽሁፍ ቢያዘጋጁ የተሻለ ነው ይላል።
“አንዳንድ ሰው አንድ ሞቲቬሽን ሌተር (የፍላጎት መግለጫ) ለሁሉም ማመልከቻዎቹ እሱን ያስገባል። እሱ ጥሩ አይደለም። ከምናመለክተበት ዲፓርትመንት ጋር የተያያዘ ቢሆን አሪፍ ነው” ይላል።
አለመመረጥ ወይም ‘Rejection’ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም የምትለው ደግሞ ረድኤት ነች።
በሙከራ ውስጥ እጅግ የተለመደው ነገር ተቀባይነት አለማግኘት ነው ትላለች።
ጨምራም አንድ ዕድል ላይ ከማተኮር በተመሳሳይ ጊዜ ሌሎች አማራጮን ማየት “የመሳካት ዕድልን ያሰፋል” ትላለች።
በዚህ ሀሳብ አፈወርቂም ይስማማል።
የሁለተኛ ዲግሪውን በኔዘርላንድስ ለመማር ሲመርጥ ከብዙ ሙከራ በኋላ እንደሆነ ይጠቅሳል።
“እኔ በጣም ብዙ [ስኮላርሺፕ] ነበር የምሞክረው አንድ ዩኒቨርሲቲ ላይ አላተኩርም፤ በዓመት እስከ አምስት እሞክር ነበር” ይላል።
አቤኔዘር “ትምህርቱን የምር የሚፈልገው ሰው” ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው ይላል።
“በየጊዜው ኢሜይል እየከፈቱ መመለስ፣ የደረሰበትን ደረጃ መከታተል፣ የሚፈለጉ ሰነዶችን ማቅረብ ያስፈልጋል። ስኮላርሺፕ መጥቶላት ኢ ሜይል ባለማየቷ፣ ያለፋት ልጅ አውቃለሁ” ይላል።
ቀጥሎም “በእኔ ዙሪያ ካሉ ሰዎች ተነስቼ ስናገር፣ አብዛኛው ሰው በራሱ መሞከር አይፈልገም። እያንዳንዱን ነገር እያዩ፣ እያነበቡ መሥራት አይፈልጉም። ሁሉም ነገር በአንድ ክሊክ ቁጭ ብሎ መጨረስ የሚፈልግ ሰው አለ። ሳትለፋ የሚመጣ ነገር የለም ” ሲልም ይናገራል።