ቼልሲ ከ አርሰናል፤ የለንደኑን ደርቢ ማን ይረታል? የመርሲሳይድ ደረቢንስ ማን ያሸንፋል?

ዚንቼንኮ እና ሙድሪክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከዓለም አቀፍ እረፍት በኋላ ተመልሷል። ቅዳሜና እሑድ በርካታ የደርቢ ጨዋታዎች ተሰድረዋል።

ቼልሲ ከአርሰናል፤ ሊቨርፑል ከኤቨርተን ተጠባቂ ጨዋታዎች ናቸው። ማንቸስተር ሲቲ ከብራይተንም አዝናኝ ኳስ የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የቢቢሲው ክሪስ ሱተን ቅዳሜና እሑድ እንዲሁም ሰኞ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ሊቨርፑል ከኤቨርተን

በአውሮፓውያኑ 2021 በርንሊን ይዘው ወደ አንፊልድ ያቀኑት ሾን ዳይሽ ድል ቀንቷቸው ነበር። አሁን ከኤቨርተን ጋር ይህን ድል ይደግሙት ይሆን?

ኤቨርተን ከሊቨርፑል ጋር ሲጫወት ያለው ታሪክ ይህን ያህል አመርቂ የሚባል አይደለም። ባለፉት 13 ዓመታት ኤቨርተን ሊቨርፑልን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ያሸነፈው።

የሊቨርፑል የመሐል መስመር ጠንካራ ሆኗል የሚለው ሱተን በዚህኛው ጨዋታ ኤቨርተን የተለየ ውጤት ያገኛል ብዬ አላስብም ይላል።

ሊቨርፑል ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመኖች ኤቨርተንን ቢያንስ በሁለት ጎል ልዩነት አሸንፏል። በዚህኛውም ጨዋታ ሁለት ጎል በማግባት ያሸንፋል እላለሁ ይላል ሱተን።

ግምት፡ 2 - 0

ቦርንመዝ ከዎልቭስ

ቦርንመዝ ከዎልቭስ

ይህ ለቦርንመዝ ትልቅ ጨዋታ ነው። የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት የጓጉት አሠልጣኝ አንዶኒ ኢራዎላ ውጤቱን እጅግ ይፈልጉታል።

የቀድሞው የቦርንመዝ አሠልጣኝ ጋሪ ኦኒል ዎልቭስን ይዘው ወደ ቀድሞ ክለባቸው ይመጣሉ።

ኦኒል ይህን ጨዋታ በመርታት የቦርንመዝ ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ያሳያል ብዬ አምናለሁ ይላል ሱተን።

ግምት፡ 0 - 1

ብሬንትፈርድ ከበርንሊ

በርንሊ በሜዳቸው እያስመዘገቡ ያለው ውጤት አስከፊ ነው። ከአምስት ጨዋታዎች አምስቱንም ተሸንፈዋል። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ከሜዳቸው ውጭ ውጤት ማስመዝገብ ነው።

የበርንሊ ተጫዋቾች ወደፊት ሲገሰግሱ አስፈሪ ቢሆኑም የተከላካይ መስመራቸው ደካማ ነው። ይህ ደግሞ ለብሬንትፈርድ መልካም አጋጣሚ ነው።

ብሬንትፈርድ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻሉም። ቢሆንም ግን የውጤት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል ማለት ከባድ ነው።

ንቦቹ በሜዳቸው በዚህ ዓመት ድል ማስመዝገብ አለመቻላቸው አስገራሚ ነው። የመጀመሪያውን ውጤት ከበርንሊ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ያገኛሉ ይላል ሱተን በግምቱ።

ግምት፡ 2 – 1

ሲቲ ከ ብራይተን

ማንቸስተር ሲቲ ከብራይተን

ይህ የሳምንቱ አዝናኝ ጨዋታ እንደሚሆን የሱተን እምነት አለው። ሁለቱም ቡድኖች ደስ የሚል ኳስ የሚጫወቱና ውጤት የሚሹ ናቸው።

ሲቲዎች ይህን ጨዋታ ከተሸነፉ ከ2016 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በመረታት ደካማ ታሪክ ያስመዘግባሉ።

ነገር ግን የመሐል ሜዳ ሞተሩ ሮድሪ ወደ ጨዋታ ስለሚመለስ ሲቲ ወደ ቀደመ አቋሙ ይመለሳል የሚል ግምቱን ሱተን ያስቀምጣል።

ሲቲ ከብራይተን ምን አይነት ፈተና እንደሚገጥማቸው አለማወቃቸው ትልቁ ፈተናቸው ነው የሚለው ሱተን ጨዋታዎች በጎል የተንበሸበሸ እንደሚሆን ይጠብቃል።

ጎሎች የሚታዩበት፤ አዝናኝ እና አስደሳች ጨዋታ እንደምናይ እሙን ነው ይላል።

ግምት፡ 6 - 2

ኒውካስል ከክሪስታል ፓላስ

ኒውካስል ከክሪስታል ፓላስ

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ዓመት ሶስት ጊዜ ተገናኝተው አንድም ጎል አላየንም። ምንም እንኳ ኒውካስል በሜዳው አንድ ጎል አስቆጥሮ በቂ ባለሆነ ምክንያት ቪኤአር ጎሉን ቢሽረውም።

ሱተን የክሪስታል ፓላሱ አሠልጣኝ ሮይ ሆጅሰን በዚህኛውም ጨዋታ ያለጎል ቢመለሱ ቅር የሚሰኙ አይመስለኝም ይላል።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ አቋም ላይ ያሉት ኒውካስሎች ይህን እንዲሆን የሚፈቅዱ አይሆንም።

ግምት፡ 2 - 0

ኖቲንግሃም ፎሬስት ከሉተን

ሉተን በያዝነው የውድድር ዘመን እያደረጉ ያሉትን ሳላደንቅ አላልፍም። አንዳንዶች ከቶተንሃም ጋር የነበራቸውን ጨዋታ ማሸነፍ ነበረባቸው ይላሉ።

ከበርንሊ ጋር በነበራቸው ጨዋታው ባለቀ ሰዓት መረታታቸው ይታወሳል።

ነገር ግን ሉተን ቁጭ ብሎ የሚመለከት ቡድን አይደለም። ተጫዋቾቹ የሚቻላቸውን ያደርጋሉ። ወደፊት ለመገስገስ ይሞክራሉ።

ቢሆንም ፎረስት በሜዳቸው ጠንካራ ናቸው።

ግምት፡ 2 - 1

ቼልሲ ከአርሰናል

ቼልሲ ከአርሰናል

ይህን ጨዋታ መገመት ትንሽ አዳጋች ነው። አርሰናል ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ወደ ስታምፈርድ ብሪጅ አቅንተው አሸንፈዋል።

በሌላ በኩል ቼልሲ ቀስ በቀስ ቅርፅ እየያዘ መጥቷል። በተለይ ደግሞ በራሒም ስተርሊንግ የሚመራው የፊት መስመር አደገኛ እየሆነ መጥቷል።

አርሰናል፤ ማንቸስተር ሲቲን ከረታ በኋላ ቼልሲን ማሸነፍ ይችላል ወይ የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው።

የመድፈኞቹ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ዕቅዱ ምን እንደሆነ ባለውቅም ጨዋታውን መቆጣጠር ከቻለ ነጥብ ይዞ ሊመለስ እንደሚችል አምናለሁ ይላል ሱተን።

ግምት 0 - 1

ሼፊልድ ዩናይትድ ከማንቸስተር ዩናይትድ

ሱተን፤ ደጋግሜ እንደምለው በማንቸስተር ዩናይትድና በግብ ጠባቂያቸው አንድሬ ኦናና ላይ ያለኝ እምነት ደካማ ነው ይላል።

ከዓለም አቀፉ እረፍት በፊት በ11ኛው ሰዓት ብሬንትፈርድን ባያሸንፉ ኖሮ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ይገቡ ነበር።

ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ለሃገሩም ሆነ ለክለቡ ጎል ያላስቆጠረው ማርከስ ራሽፈርድ ከማክሰኞ ምሽት ለእንግሊዝ ጎል ማስቆጠሩ የራስ መተማመኑን ይመልሰዋል።

ሼፊልድ ዩናይትድ ቀላል ተጋጣሚ ባይሆኑም ይህን ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ በድል እንደሚወጣው ሱተን ያምናል

ግምት፡ 0 - 2

እሑድ

አስተን ቪላ ከዌስትሃም

አስተን ቪላ ከዌስትሃም

ሁለቱም ቡድኖች የውድድሩን ዓመት በመልካም ሁኔታ ነው የጀመሩት። ሁለቱም ጎል ለማግባት የሚሰንፉ አይደሉም። ይህ ጨዋታ አጓጊ እንደሚሆን ሱተን ያስባል።

ነገር ግን አስተን ቪላ በሜዳቸው የተሻለ ክብረ ወሰን መያዛቸው ድሉ ወደነሱ ያቀናል እንድል ያደርገኛል ይላል።

የቪላው አጥቂ ኦሊ ዋትኪንስ ጥሩ አቋም ላይ መሆኑ ጨዋታዋን ባለሜዳዎቹ እንዲያሸንፉ ያስችላል ብዬ በድፍረት እንድናገር አድርጎኛል።

ግምት፡ 2 - 1

ሰኞ

ቶተንሃም ከፉልሀም

ቶተንሃም ከፉልሀም

ለሁለት ተከታታይ ጊዜ የወሩ ምርጥ አሠልጣኝ ተብለው የተመረጡት የቶተንሃሙ አለቃ አንጌ ፖስቴኮግሉ ቀጣዩን ጨዋታ ያሸንፋሉ ወይ ትልቁ ጥያቄ ነው።

ፉልሀም ቶተንሃም ከካራባዎ ዋንጫ ውጭ ማድረግ ችለዋል። ነገር ግን ጨዋታው በፉልሀም ሜዳ ነበር።

ስፐርስ ይህን ጨዋታ በሜዳቸው ማድረጋቸው የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እንዲኖራቸው ያደርጋል። ቶተንሃም በያዝነው ዓመት ጥሩ ባይጫወቱ እንኳ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ግምት፡ 3 - 1