ቦይንግ በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አደጋዎች የ25 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲጣልበት ተጠየቀ

የቦየንግ ኃላፊ ዴቭ ካልሀውን የአሜሪካ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቦየንግ ኃላፊ ዴቭ ካልሀውን የአሜሪካ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት

ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ በሆኑ ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖች አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ቦይንግ የ24.8 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲጣልበት ጠየቁ።

የአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች ጠበቃ ቦይንግ በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን ወንጀል የፈጸመ ነው ሲል ገልጾታል።

የቤተሰቦቹ ጠበቃ ፖል ካሴል ቦይንግ ውድ በሆነው የሰው ልጆች ሕይወት ላይ ጥፋት በማድረስ ለፈጸመው ወንጀል የተጠየቀው የገንዘቡ መጠን “ተገቢ እና ትክክል ነው” ብለዋል።

ቢቢሲ በተመለከተው ባለ 32 ገጽ ደብዳቤ ላይ ጠበቃው የአሜሪካ መንግሥት በ2010 እና 2011 ዓ.ም. በደረሱት እና የ346 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፉት አደጋዎች ቦይንግን የሚመሩ ሰዎች ሊጠየቁ ይገባልም ብሏል።

በደብዳቤው ላይ የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቭ ካልሁን ማክሰኞ ሰኔ 12/2016 ዓ.ም. በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርበው የጠየቁት ይቅርታም ተጠቅሷል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው “ለፈጠርነው ሐዘን ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

ኃላፊው ንግግር ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት በአደጋው ቤተሰቦቻቸው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ቁጣቸውን ሲገልጹ እና ንግግራቸውን ሲያስተጓጉሉ ታይተዋል።

346 ሰዎች የሞቱባቸው ሁለቱ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋዎች በተለያዩ ጊዜያት ቢከሰቱም የተከሰከሱበት ምክንያት ግን ፍጹም ተመሳሳይ የሚባል ነው።

በመጋቢት ወር መግቢያ 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላን በተነሳ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ በአውሮፕላኑ የነበሩ 157 መንገደኞች እና የበረራ ሠራተኞች በሙሉ ሕይወታቸው አልፏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ደግሞ ከኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ ጃካርታ የተነሳው ተመሳሳይ አውሮፕላን ከተነሳ 13 ደቂቃ በኋላ የጃቫ ባሕር ላይ ወድቆ በውስጡ የነበሩ 189 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸወን አጥተዋል።

የሁለቱም አደጋዎች መንስኤ በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ በተፈጠረ ችግር ነበር።

የቦይንግ ኃላፊ በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቀት ኩባንያቸው ስህተት መሥራቱን አምነዋል። ካለፈው “ስህተቱ” ተምሯል ሲሉም ተደምጠዋል።

ችግሩን የጠቆሙ ሰዎች ላይ ቦይንግ የበቀል እርምጃ እንደወሰደም ኃላፊው ለምክር ቤቱ የእምነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ከሦስት ዓመታት በፊት ከሁለቱ አደጋዎች ጋር በተገናኘ በቦይንግ ላይ ጀምሮት የነበረውን የማጭበርበር ወንጀል ክስ ዳግም ሊመለሰበት ማሰቡም ተሰምቷል።

ይህ ክስ ቦይንግ በአሜሪካ የአውሮፕላን ምርት ተቆጣጣሪዎችን ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ማክስ 8 ቦይንግ 737 አውሮፕላንን በተመለከተ የሚያሳስት መረጃም መስጠቱን ያሳያል።

ባለፈው ጥር ወር ንብረትነቱ የአላስካ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላን በረራ ላይ እያለ በሩ ተገንጥሎ ክፍተት ከተፈጠረ በኋላ የአሜሪካ ዐቃቢያነ ሕጎች ቦይንግ ሕግ ተላልፏል ብለዋል።

እስከ ቀጣዩ ሐምሌ አጋማሽ ድረስም የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ይህንን ጉዳይ መቀበል ወይም አለመቀበሉ ይታወቃል።

ጠበቃ ካሴል የፍትህ መሥሪያ ቤቱ ገለልተኛ ተቆጣጣሪ አካል የቦይንግን ደኅንነት እና አስተማማኝነት እርምጃዎች እንዲያጣራ ደንበኞቹ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውንም ገልጿል።

ማክሰኞ በአሜሪካ ምክር ቤት በነበረው የቦይንግ ኃላፊ ማብራሪያ ላይ በአደጋዎቹ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች ፎቶዎችን ይዘው ታድመው ነበር።

በ2011 ዓ.ም. በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ አባቱን ያጣው ዚፖራ ኩሪያ “ከእንግሊዝ ድረስ ወደ ዋሽንግተን የመጣሁት ቦይንግ በኩባንያው ውስጥ ያደረገውን የደኅንነት ማሻሻያ በአካል ተገኝቼ ለመስማት ነው” ብሏል።

“ቦይንግ እና ኃላፊዎቹን ለ346 ሰዎች ሞት በወንጀል እስኪጠየቁ ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ላይ ግፊት ማድረጌን እቀጥላለሁ። ፍትህ እስከምናገኝ እረፍት አይኖረንም” ሲልም አክሏል።