ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ፣ እስራኤል እና ምዕራባውያንን የተቹት የሳዑዲው ልዑል ለምን አነጋጋሪ ሆኑ?
የሐማስ ጥቃትን እና የእስራኤል ያልተቋረጠ የአጸፋ እርምጃን ተከትሎ ከሳዑዲ አረቢያ ንጉሣውያን መካከል ጉልህ ተጽእኖ ያላቸው ልዑል ቱርኪ አል-ፋይሳል የሰነዘሩት ትችት ከሌሎች አረብ አገራት ባለሥልጣናት የተለየ መሆኑ ትኩረትን ስቧል።
በተለይ መካከለኛው ምሥራቅን ባቃወሰው በዚህ ግጭት ዙሪያ የልዑሉ አስተያየት የሳዑዲ መሪዎችን አቋም በግልጽ የሚያንጸባርቅ ነው ተብሎ ታምኗል።
በሳዑዲ አረቢያ የአመራር ክበብ ውስጥ ጉምቱው እና ከፍተኛ አክብሮት ያላቸው የፖለቲካ አመራር ልዑል ቱርኪ፣ ከግጭቱ መቀስቀስ አንስቶ ሲቪሎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ሐማስን እና እስራኤልን በይፋ አውግዘዋል።
“በዚህም ሰለባዎች እንጂ ጀግኖች አይኖሩም” ብለዋል።
በአሜሪካ ሂዩስተን ውስጥ በሚገኘው ራይስ ዩኒቨርስቲ ለታደሙ ሰዎች ልዑሉ ባደረጉት ንግግር፣ እስራኤል እየፈጸመች ባለው የአየር ጥቃት ምክንያት በአረቡ ዓለም ቁጣ የተፈጠረ ሲሆን፣ ከሌሎች በተለየ ሐማስን ከእስራኤል ጎን ተችተውታል።
የሐማስ ድርጊት ሲቪሎችን ማጥቃትን ከሚከለክለው ከእስላማዊው ትዕዛዝ ተቃራኒ ነው ብለዋል። በሐማስ ጥቃት ከተገደሉት እና ከታገቱት አብዛኞቹ ሲቪሎች ናቸው።
ጠንቃቃ እና አርቆ አሳቢ መሆናቸው የሚነገርላቸው የቀድሞው ዲፕሎማት እና የሳዑዲ የስለላ ተቋም አዛዥ የሆኑት ልዑል ቱርኪ፣ ትችታቸው በሐማስ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም።
እስራኤልን “በጋዛ የሚገኙ ሲቪሎችን በጅምላ በቦምብ በመደብደብ” ከመክሰሳቸው በተጨማሪ ዌስት ባንክ ውስጥ “ልጆችን፣ ሴቶችን እና ወንዶችን” ሳትለይ ሁሉንም እያሰረች ነው ብለዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የሐማስን ጥቃትን በተመለከተ “ያለምክንያት የተፈጸመ ጥቃት” በማለት የሚጠቀሙትን አገላለጽንም ተችተዋል። “እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ላይ ለዘመናት ከፈጸመችው በላይ . . . ምን ምክንያት ያስፈልጋል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
አክለውም “ሁሉም በወታደራዊ ኃይል የተወረረ ሕዝብ ወረራን የመቃወም መብት አለው” ብለዋል።
ልዑል ቱርኪ በተጨማሪም ምዕራባውያን ፖለቲከኞችን “እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ እንባቸውን ያፈሳሉ” ነገር ግን “እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሲገድሉ ሐዘናቸውን እንኳን ለመግለጽ ፈቃደኛ አይደሉም” በማለት አውግዘዋቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቀናት በፊት እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት፣ አገራቸው የግጭቱ ሰለባ ለሆኑ ለሁሉም ሲቪሎች እንደምታዝን ተናግረው ነበር።
ይህ የልዑሉ ሐማስን፣ እስራኤልን እና ምዕራባውያንን በግልጽ የተቹበት ንግግር ትኩረትን የሳበው ከኋላው ባነገበው መልዕክት ምክንያት እንደሆነ እየተዘገበ ነው።
በሳዑዲ ንጉሣዊ አስተዳደር ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ልዑል ቱርኪ፣ እንዲህ ያለውን አስተያየት ሲሰነዝሩ ከዘውዳዊው ምክር ቤት ይሁንታን ሳያገኙ የሚሆን አይደለም።
ይህ የሳዑዲ የፖለቲካ ማዕከል ደግሞ ባለፈው ሐሙስ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በተገናኙት እና በአገሪቱ አመራር ውስጥ ኃያል በሆኑት ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሚመራ ነው።
የታዋቂው እና ሳዑዲን ወደ ዘመናዊነት የመሩት በመጨረሻም በ1975 (እአአ) የተገደሉት የንጉሥ ፋይሳል ልጅ የሆኑት ልዑል ቱርኪ የንጉሣዊው ቤተሰብ አባል ናቸው። ወንድማቸውም በ2015 (እአአ) እስከሞቱበት ድረስ ለረጅም ዓመታት የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ።
በአሜሪካ እና በብሪታኒያ ውስጥ ባሉት ታዋቂዎቹ ፕሪንስተን፣ ኬምብሪጅ እና ጆርጅታውን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተማሩት ልዑል ቱርኪ፣ የምዕራባውያንን ባህል እና አስተሳሰብን በተመለከተ ተጠቃሽ ግንዛቤ አላቸው። ይህም በዋሽንግተን እና በለንደን ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎች ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማዳበር አስችሏቸዋል።
በተጨማሪም ለ24 ዓመታት በተለይ በአፍጋኒስታን ላይ ልዩ ኃላፊነት የተሰጠውን የውጭ አገራት የደኅንነት እና የመረጃ አገልግሎት የሆነውን የሳዑዲ አረቢያ የስለላ ተቋምን መርተዋል።
በአሜሪካ ላይ በአል ቃኢዳ የተፈጸመውን የመስከረም 11 ጥቃትን ተከትሎም መጀመሪያ በለንደን፣ ከዚያም በዋሽንግተን የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል።
ለንደን እያሉ የኤምባሲያቸው የመገናኛ ብዙኃን ቃል አቀባይ የነበረው በ2018 (እአአ) ቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ በመንግሥት ወኪሎች የተገደለው ጀማል ኻሾግጂ ነበር። ሳዑዲ ግድያው ተፈጸመው ባለሥልጣናት ባላወቁት ሁኔታ ነው ስትል አስተባብላለች።
አሁን የ78 ዓመት አዛውንት የሆኑት ልዑል ቱርኪ፣ በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ውስጥ ይፋዊ የሆነ የመንግሥት ሥልጣን ባይኖራቸውም፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚያደርጓቸው ንግግሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሳዑዲን አቋም በተዘዋዋሪ የሚያንጸባርቁ ናቸው።
የሳዑዲ አረቢያ መሪዎች ሐማስን አይወዱትም። ለነገሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያሉ በርካታ መንግሥታትም በተመሳሳይ ሐማስን ይጠሉታል።
የግብፅ፣ የዮርዳኖስ፣ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የባህሬን መሪዎች ሐማስን እና የሚከተለውን አብዮታዊ መልክ ያለው “ፖለቲካዊ እስልምና” ለዓለማዊ አስተዳደራቸው እንደ ስጋት ይመለከቱታል።
በያሲር አራፋት ፋታህ ፓርቲ የሚመራው የፍልስጥኤም ባለሥልጣን በአውሮፓውያኑ 2007 የተፈጠረውን ግጭትን ተከትሎ በሐማስ ከጋዛ መባረሩ ይታወሳል። በወቅቱ የፓርቲው አንዳንድ አባላት ከረጃጅም ሕንጻዎች ጣራ ላይ እስከ መወርወር ደርሰው ነበር።
ሐማስ መሠረቱን ጋዛ ውስጥ ያደርግ እንጂ የፖለቲካዊ አመራሩ ጽህፈት ቤት የሚገኘው ኳታር ውስጥ ነው። ዋነኛው ደጋፊው ግን የሳዑዲ አረቢያ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ተቀናቃኝ የሆነችው ኢራን ናት።
ሳዑዲ እና ኢራን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ፍጥጫቸውን ለማብቃት በይፋ ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ አሁንም ድረስ በመካከላቸው የሰፈነው መጠራጠር እንዳለ ነው። ቢሆንም ግን ሁለቱም እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን የቦምብ ድብደባ በጋራ በማውገዝ ለፍልስጥኤማውያን አገር መመሥረት ያላቸውን ድጋፍ ደግመው አረጋግጠዋል።
አሁን ያለበትን ሁኔታ ማወቅ አዳጋች ቢሆንም ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬን እና ሞሮኮ እንዳደረጉት ሁሉ ሳዑዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል በሂደት ላይ ነበረች። ይህ ሁኔታ አሁን ተገትቷል።
በርካታ ተንታኞች ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመው አደገኛው ጥቃት በከፊል እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እያደረገች ያለውን ጥረት ለማደናቀፍ በማሰብ የተፈጸመ ነው ብለው ያምናሉ።
ይህ የግንኙነት መሻሻል አዲስ በሚፈጠረው የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሐማስን እና ኢራንን የሚያገልል ይሆናል የሚል ስጋት መፈጠሩ ሐማስ ጥቃቱን እንዲፈጽም አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ።
ሁለት ሳምንት ከሞላው ጥቃት እና ጦርነት በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ የነበረው ሁኔታ ወደ ቦታው ሊመለስ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
በሐማስ ጥቃት በቆሰለችው እስራኤል በኩል ሁኔታውን ቻል አድርጋ የመቀጠል ምልክትን እያሳየች አይደለም። እንዲሁም በጎዳናዎቻቸው ላይ ፀረ አስራኤል ተቃውሞዎችን እየተመለከቱ ያሉት የአረብ መንግሥታት ተቆጥተዋል። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት ነገሮች ወደ ነበሩበት የመመለሳቸው ነገር ከባድ ነው።
ሳዑዲ አረቢያ ሐማስን ትጥላው እንጂ ፍልስጥኤማውያንን ለመደገፍ ዘግጁ ናት። አሁን እየተካሄደ ያለው ግጭት ሲቆም በእስራኤል የአየረ ጥቃት የወደመችውን ጋዛን መልሶ ለመገንባት ሳዑዲ አረቢያ እጇን መዘርጋቷ የሚጠበቅ ነው።
በሳዑዲ አረቢያ ንጉሣውያን ዘንደ ከፍተኛ ተጽእኖ ያላቸው ልዑል ቱርኪ አል ፋይሳል የሚናገሯቸው ነገሮች የመንግሥታቸው አቋም ነጸብራቅ መሆኑ ይታመናል።
ለዚህም ከሳዑዲ በኩል በቀጣይነት ለሚመጣ ማንኛውም ነገር የልዑል ቱርኪ ንግግርን ትኩረት ስጥቶ መከታተል የሚያመለክተው ነገር ቀላል የሚባል አይደለም።