የተባበሩት መንግሥታት በአማራ ክልል ከሐምሌ ወር ወዲህ ቢያንስ 183 ሰዎች ተገድለዋል አለ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ውስጥ ከገቡ ወዲህ ከሐምሌ ወር አንስቶ እስካሁን ድረስ 180 በላይ ሰዎች ተገድለዋል አለ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የመብቶች ጥሰት ተበራክቷል ያለ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች እያሽቆለቆሉ መምጣታቸው አሳሳቢ ነው ብሏል።

ከሳምንታት በፊት ተቀስቅሶ እየተባባሰ በሄደው ግጭት ከፈረንጆቹ ሐምሌ ወር አንስቶ ቢያንስ 183 ሰዎች መገደላቸውን የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያሰባሰበውን መረጃ ጠቅሶ አመልክቷል።

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለሳምንታት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ውጊያዎች የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት መድረሱ እንዲሁም ንብረት መውደሙ ሲዘገብ ቆይቷል።

መንግሥትን ይህን በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመቆጣጠር በዋናነት በክልሉ ላይ እንደአስፋለጊነቱም በመላው አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

የተመድ ተቋም በመግለጫው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለሥልጣናት ተጠርጣሪዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ፣ የሰዓት ዕላፊ ገደቦችን እንዲጥሉ እንዲሁም የመሰብሰብ መብቶችን እንዲገፉ ሥልጣን እንደሚሰጥ አመልክቷል።

ተፈጻሚ እየሆነ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ቢያንስ 1 ሺህ ሰዎች በመላው አገሪቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጾ፤ አብዛኞቹ ታሳሪዎች የፋኖ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ ወጣት የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው ብሏል።

ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የቤት ለቤት አሰሳ ሲካሄድ መቆየቱን፣ ጉዳዩን በተመለከተ ሲዘግቡ የነበሩ ሦስት ጋዜጠኞች መታሰራቸውን እና ታሳሪዎች መሠረታዊ የሆኑ መገልገያዎች በሌሏቸው ማዕከላት መታሰራቸውንም መግለጫው አብራርቷል።

ድርጅቱ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የጅምላ እስርን እንዲያቆሙ፣ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ገደቦች በፍርድ ቤት እንዲረጋገጡ እና ከሕግ ውጪ የታሰሩ እንዲለቀቁ ጠይቋል።

መንግሥት የታሳሪዎች አያያዝ ዓለም አቀፍ ደንብ እና ደረጃን የሚያሟላ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጨምሮ የመብት ተቆርቋሪዎች ታሳሪዎች የሉበትን ሁኔታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲጎበኙ ፍቃድ እንዲሰጥ ተመድ ጠይቋል።

የፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች አንዳንድ የክልሉን ከተሞች እየተቆጣጠሩ፤ የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ ወደ ገጠራማ ቦታዎች እንደሸሹ ሪፖርት እየተደረገ ባለበት ወቅት፣ በዚህ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ግድያዎችን እና የመብት ጥሰቶችን እንዲያቆሙ መግለጫው ጠይቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን አክሎም፣ የትኛውም አለመግባባት በንግግር እና በፖለቲካዊ ሂደት መፍትሄ ሊሰጠው ይገባልም ብሏል።

ኮሚሽኑ በአማራ እና በትግራይ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ወልቃይት ጠገዴ/ምዕራብ ትግራይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ታስረው እንደነበርም ገልጿል።

በምዕራብ ትግራይ በአማራ ፖሊስ፣ በአካባቢው አስተዳዳሪዎች እና የወልቃይት ወጣቶችን ያካተት የአካባቢው ሚሊሻ አባላት ተሳታፊ በሆኑበት ዘመቻ ከ250 ያላሱ የትግራይ ተወላጆች ታስረው እንደነበረ ሰምቻለሁ ብሏል።

እነዚህ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት የትግራይ ተወላጆች በወልቃይት ወጣቶች አማካይነት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ቁጥጥር ሥር ወዳለ ቦታ እየተወሰዱ ሳለ በአገር መከላከያ ሠራዊት እጅ መግባታቸውንም ገልጿል።

እንደ ተመድ ኮሚሽን ከሆነ መከላከያም ለትግራይ ተወላጆቹ ወደ ምዕራብ ትግራይ እንዲመለሱ ወይም ደግሞ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ቁጥጥር ሥር ወዳሉ አካባቢዎች እንዲሄዱ አማራጭ ሰጥቷል።

ኮሚሽኑ ከአማራ እና ትግራይ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ጥቃት አሳሳቢ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች በፍጥነት፣ በገለልተኝነት እና በብቃት ሊመረመሩ እንዲሁም ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብሏል።

ከሐምሌ ወር መጨረሻ አንስቶ በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀሰው እና የተባባሰው ግጭት ክልሉን ከባድ ቀውስ ውስጥ አስገብቶታል።

ባለፉት ሳምንታት ጋብ ብሎ የነበረው ግጭት ካለፈው ሳምንት ማብቂያ አንስቶ በበርካታ ቦታዎች ላይ እየተካሄደ መሆኑ ተዘግቧል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ በሆነው በደብረ ታቦር ከተማ ለቀናት በታጣቂዎች እና በመንግሥት ሠራዊት አባላት መካከል በተካሄደ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዳግም ያገረሸው ግጭት ከደብረ ታቦር በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ፣ በፍኖተ ሰላም እና በሰሜን ሸዋ አካባቢ ባለፉት ቀናት ማጋጠሙ ተዘግቧል።