በዩኬ የሶስት ሰዎችን ዘረ መል በማጣመር በዘር ከሚተላለፍ በሽታ ነጻ የሆኑ ልጆች እንዲወለዱ ማድረግ ተቻለ

በዩናይትድ ኪንግደም ከሶስት ሰዎች የተውጣጡ ዘረ መሎችን (ዲኤንኤ) በማጣመር በዘር ከሚተላለፍ እና አብዛኛውን ጊዜ ገዳይ ከሆነው 'ማይቶኮንድሪያል' ከተሰኘው በሽታ ነጻ የሆኑ ስምንት ልጆች ተወለዱ።

በዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች ፈር ቀዳጅነት የተጀመረው ይህ ዘዴ የእናት እንቁላልን፣ የአባት ስፐርምን ከለጋሽ ሴት እንቁላል ጋር በማዋሃድ ልጆች እንዲወለዱ የሚያደርግ ነው።

ይህ ቴክኒክ በዩናይትድ ኪንግደም ህጋዊ ሆኖ ለአስር ዓመት ቢቆይም በአሁኑ ወቅት ግን ተግባራዊ ተደርጎ ሊድን ከማይችለው እና በዘር ከሚተላለፈው ማይቶኮንድሪያል በሽታ ነጻ የሆኑ ልጆች እንዲወለዱ በማድረግ ለፍቱንነቱ ማረጋገጫ ተገኝቷል ተብሏል።

ማይቶኮንድሪያል በሽታ የጄኔቲክ ቀውሶችን የሚያሳይ ህመም ነው።

እነዚህ የጄኔቲክ ሁኔታዎች በተለምዶ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፉ ሲሆን ሰውነትን ኃይል በማሳጣት አደጋ ላይ የሚጥል ህመም ነው።

ማይቶኮንድሪያ በሰውነቶቻችን ባሉ መላ ህዋሶች የሚገኙ ጥቃቅን የህዋስ ክፋይ ናቸው።

እነዚህ የህዋስ ክፋዮች በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ምግብ ኦክስጅንን በመጠቀም አካላችን እንደ ነዳጅ የሚጠቀምባቸውን ኃይል ያመርታሉ። ለመተንፈስም ምክንያቶቻችን ናቸው።

የማይቶኮንድሪያ ጉድለት በሰውነታችን የኃይል እጥረት እንዲያደርግ ምክንያት ነው።

ልብ ያለ አግባብ እንዲመታ፣ የአዕምሮ ጉዳት፣ ማንቀጥቀጥ፣ አይነስውርነት፣ የጡንቻ መዛል እና የሰውነት ክፍሎቻችን አገልግሎት መቆምን ያስከትላል።

ይህ ሁኔታ የከፋ የአካል ጉዳት ሊያስከትል እንዲሁም አንዳንድ ህጻናትም በተወለዱ በቀናት ውስጥ ይሞታሉ።

ባሉት መረጃዎች ከ5 ሺህ ህጻናት መካከል አንዳቸው በማይቶኮንድሪያል በሽታ ተጠቅተው ይወለዳሉ።

ጥንዶች የቀድሞ ልጆቻቸው፣ የቤተሰብ አባላት ወይም እናትየዋ በዚህ ተጠቅታ ከሆነ የሚወልዱት ልጆች የተጋለጡ እንደሆኑ ያውቃሉ።

የሶስት ሰዎችን ዘረ መል በማጣመር የተወለዱት ልጆች አብዛኛውን ዘረመላቸው እንዲሁም የጄኔቲክስ አሻራቸውን ከወላጆቻቸው የሚወርሱ ሲሆን ፤ከለጋሿ ሴት ደግሞ በአነስተኛ መጠን፣ 0.1 በመቶ ያገኛሉ። ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያልፍ ይሆናል።

በዚህ ሂደት ያለፉ ቤተሰቦች የግል መረጃቸውን ለመጠበቅ በሚል ማናቸውም ቢሆን በይፋ መናገርን አልፈቀዱም።

ሆኖም ማንነታቸው ሳይገለጽ በጋራ ሂደቱ በተካሄደበት የኒውካስል የወሊድ ማዕከል በኩል መግለጫ ሰጥተዋል።

"ከዓመታት እርግጠኛ አለመሆን በኋላ ይህ ህክምና ተስፋ ሰጠን፤ ከዚያም ልጃችንን አሳቀፈን" ስትል በዚህ ሂደት ሴት ልጅ የተገላገለች እናት ተናግራለች።

እናቲቱ አክላም "ልጆቻችን አሁን ስንመለከታቸው በተስፋ እና መጪውን ብሩህ በሆነ መልኩ ነው። ምስጋናችን ከቃላት በላይ ነው" ብላለች።

በቴክኒኩ ወንድ ልጅ የተገላገለች እናት በበኩሏ "ለዚህ ለላቀ ህክምና ምስጋና ይግባው እናም ለተደረገልን ድጋፍ እንዲሁ እናመሰግናለን። አሁን አነስተኛው ቤተሰባችን ተሟልቷል" ስትል ገልጻለች።

"በማይቶኮንድሪያል በሽታ የተጫነኝ የስሜት ሸክም አሁን ተነስቶልኛል፤ እናም በሱ ምትክ ተስፋ፣ ደስታ እና ጥልቅ ምስጋና ተሞልቻለሁ" በማለትም አክላለች።