ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ባሌ ለዓመታት በመድኃኒት እያደነዘዘ ይደፍረኝ ነበር"
ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሑፍ የሚረብሽ ይዘት ሊኖረው ይችላል።
ኬት (ስሟ ተለውጧል) ከባለቤቷ ጋር አንድ ምሽት ቁጭ ብላ ስታወራ የነገራት ነገር ከባድ ነበር።
"ስደፍርሽ ነበር። ለዓመታት እያደነዘዝኩ ፎቶ ሳነሳሽ ነበር።"
ኬት የምትናገረው ጠፋት። ፈዛ ቀረች። የሚናገረውን ለመረዳት ተሳናት።
"እራት ፓስታ እንበላለን እንደሚለው ዓረፍተ ነገር ቀለል አድርጎ ነበር የነገረኝ" ትላለች።
ከመጋረጃ ጀርባ ባለቤቷ በዝባዥ ነው። የህመም ማስታገሻ መድኃኒት ከአግባብ ውጪ ይጠቀማል።
ኬት ከእንቅልፏ ስትነቃ ባለቤቷ ከእሷ ጋር ወሲብ ሲፈጽም ታገኘዋለች። ፈቃዷን ሳትሰጠው እና በእንቅልፍ ላይ ሳለች ነበር። በትዳር ውስጥም ቢሆን ያለ ፈቃድ የሚፈጸም ወሲብ እንደ መድፈር ይቆጠራል።
ወዲያው ባለቤቷ ይጸጸታል። እንቅልፍ ወስዶት እንደነበርና የሚያደርገውን እንደማያውቅ ይነግራታል።
ህመም እንዳለበትም ነግሯታል። ኬት ወደ ሕክምና ወሰደችው።
ማታ ማታ ሻይ ውስጥ ማደንዘዣ መድኃኒት ይሰጣት እንደነበር አላወቀችም። መድኃኒት ሰጥቶ እያደነዘዘ ይደፍራታል።
ድርጊቱን ከተናዘዘ በኋላ ኬት ፖሊስ ጣቢያ ብትሄድ ሕይወቱ እንደሚያበቃለት ስለነገራት ለፖሊስ ሳታመለክት ቀረች።
ሆኖም ግን የነገራት ነገር ለወራት ረበሻት። ሰውነቷ ላይ ጫናው ይስተዋል ጀመር።
ሰውነቷ በጣም ቀነሰ። ታመመች። ጭንቀት ያሰቃያትም ነበር።
ባለቤቷ እንደሚደፍራት በነገራት በዓመቱ ለእህቷ ነገረቻት።
እህቷ ለእናቷ ከተናገረች በኋላ እናቷ ለፖሊስ ደውለው ጠቆሙ። የኬት ባለቤት ታሰረ።
ኬት ባለቤቷ ከታሰረ ከአራት ቀናት በኋላ ወደ ፖሊስ ደውላ ክሱን ልትቀጥልበት እንደማትፈልግ ተናገረች።
"ዝግጁ አልነበርኩም። ሐዘኑ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለልጆቼም ጭምር ነበር። በዚህም ምክንያት የሚያውቁት አባታቸው ሆኖ አይቀጥልም" ትላለች።
ሆኖም ባለቤቷ ከዚያ በኋላ አብሯት እንዲኖር አልፈለገችም።
ከስድስት ወር በኋላ ወደ ፖሊስ ተመልሳ ሄደች። በመርማሪ ማይክ ስሚዝ የሚመራ ምርመራም ተጀመረ።
ከከፍተኛ ወንጀል መትረፏን መርማሪው ነገራት።
"የነበረኝ አቅም እንዲመለስ ረዳኝ። አቅሜን መነጠቄን አላወቅኩም ነበር። መርማሪው መደፈሬን አረጋገጠልኝ" ትላለች።
ከባለቤቷ ጋር አሁን ተለያይታለች። ለኬት እውነቱን ከነገራት በኋላ የሥነ ልቦና አማካሪ ማነጋገር ጀምሯል።
የሕክምና ውጤቱ በማስረጃነት ቀርቧል።
ለሥነ ልቦና ባለሙያ ባለቤቱን በመድኃኒት አደንዝዞ ወሲብ ይፈጽም እንደነበር ገልጿል።
የመድኃኒት ሱሰኞች ለማገገም በሚገናኙነት ቡድን ውስጥም ይሄንን አምኗል። በዚህ ቡድን ንግግር ሲያደርግ ኬትም ነበረች።
ፖሊስ የሰበሰበውን ማስረጃ ለዐቃቤ ሕግ ቢያቀርብም ክስ አልተመሠረተም። ለምን ክስ እንዳልተመሠረተ ኬት አልገባትም።
"ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ በቂ ማስረጃ ካለ ክስ መመሥረት አለበት። የእኔ ጉዳይ እንዲህ ከተጓተተ የሌሎች ደግሞ እንዴት ሊሆን ነው?"
ኬት ክሱ በድጋሚ እንዲመረመር ጠየቀች።
ከስድስት ወር በኋላ የቀድሞ ባለቤቷ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተነገራት።
"ከዚህ ቀደም በዐቃቤ ሕግ የተላለፈው ውሳኔ የተሳሳተ ነበር" ተባለች።
የምርመራ ክፍል ቃል አቀባይ "ብዙን ጊዜ በመጀመሪያው ዙር ክስ እናቀርባለን። በዚህ ጉዳይ ይሄንን ማሳካት ባለመቻላችን ተጎጂዋ ላይ ላሳደርነው ጫና ይቅርታ እንጠይቃለን" ብለዋል።
ጉዳዩ ፍርድ ቤት የተወሰደው የኬት የቀድሞ ባለቤት ድርጊቱን ካመነ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2022 ነበር።
በፍርድ ቤት ቃሉን ሲሰጥ ኬት ተኝታ ሳለ ታስራ ስትነቃ በፈቃዷ ወሲብ መፈጸም ትፈልግ ነበር ብሏል። ያደነዝዛት የነበረው ለመድፈር ሳይሆን ሳትነቃ እጇን ለማሰር እንደሆነ ቢናገርም በፍርድ ቤት ተዓማኒነት አላገኘም።
"ንግግሩ የሚያናድድ ነው። በሕይወቷ የገጠማት የከፋ ነገር ሆኖ ሳለ በፈቃዷ ያደረገችው ነገር አስመሰለው" ይላሉ መርማሪው።
ከአንድ ሳምንት በኋላ የቀድሞ ባለቤቷ በመድፈር፣ በወሲባዊ ጥቃት እና አድንዛዥ መድኃኒት በመስጠት ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ዳኛው ፍርዱን ሲያስተላልፉ "ከራሱ ጋር በፍቅር የወደቀ እና የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያሳድድ ሰው ነው። ጸጸትም አይታይበትም" ብለዋል።
የ11 ዓመት እስራት እና ለዕድሜ ልክ ዕግድ ተፈርዶበታል።
ፍርዱ ከተላለፈ ከሦስት ዓመታት በኋላ ኬት ከልጆቿ ጋር ሕይወቷን ለመግፋት እየሞከረች ነው።
ከአስደንጋጭ ክስተት በኋላ የሚከሰተው ሕመም (post-traumatic stress disorder ወይም PTSD) እንዳለባት ተነግሯታል።
ፈረንሳዊቷ ዥዜል ፔሊኮን የቀድሞ ባለቤቷ በዕፅ እያደነዘዘ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት አስደፍሯት ፍርድ ቤት ቀድቦ በቅርቡ እንደተፈረደበት ይታወሳል።
ኬት ሕይወቷ ከዥዜል ጋር እንደሚመሳለል ትናገራለች።
"ዥዜል የሚያስፈልጋት ድጋፍ እና እርዳታ እንዲደረግላት ስፀልይ ነበር" ትላለች።
በመድኃኒት ወይም በዕፅ አደንዝዞ መድፈር አልያም ወሲባዊ ጥቃት ማድረግ ኬሚካል ኮንትሮል (Chemical control) ይባላል።
ፕሮፌሰር ማሪን ሄስተር መድኃኒት አደንዝዞ መድፈር እየተለመደ መምጣቱን ይናገራሉ።
"ጥቃት ፈጻሚዎች ከሚጠቀሙበት መንገድ አንዱ ነው። ቤት ውስጥ መድኃኒት ካለ ጥቃት አድራሾች ይጠቀሙበታል" ይላሉ።
አልኮል መጠጥ ውስጥ ማደንዘዣ መጨመር እየጨመረ እንደመጣም የእንግሊዝ እና ዌልስ የቤት ውስጥ ጥቃት ኮሚሽነር ኒኮል ጃኮብስ ይገልጻሉ።
"ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል የሚወጡ ሕጎች እየተተገበሩ መሆኑን ማወቅ የሚቻለው ለፖሊስ ሪፖርት የሚደረግ የቤት ውስጥ ጥቃት በአግባቡ ሲመዘገብ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።
ጥቃት አድራሾች ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ ተጎጂዎችም ሕይወታቸውን ዳግመኛ እንዲገነቡ ድጋፍ ይሻሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ አልኮል መጠጥ ውስጥ የሚጨመር ማደንዘዣን ለመከታተል አዲስ መመሪያ እያዘጋጀ ነው።
ከዚህ ቀደምም አልኮል መጠጥ ውስጥ ማደንዘዣ መጨመር ወንጀል ሲሆን፣ አዲሱ መመሪያ እስከ 10 ዓመት በእስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ያደርገዋል።
ተጎጂዎች ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ ለማበረታታት መመሪያው እንደሚረዳ ይታመናል።
ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው መሥሪያ ቤት ሚኒስቴር የሆኑት ጀስ ፊሊፕስ እንደሚሉት አልኮል መጠጥ ውስጥ ማደንዘዣ መጨመር "የሰዎችን ደኅንነት እና የነጻነት ስሜት የሚጋፋ የከፋ ወንጀል ነው።"
ኬት ፍትሕ አግኝታለች። ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን ወደ ክስ ላለመውሰድ እንደወሰነ ቢቀር ኖሮ ግን ፍትሕ አይሰፍንም ነበር።
"ከምታስቡት በላይ በዝምታ ውስጥ ጥቃቶች ይፈጸማሉ። እኔ እስካሁን ድረስ ምን እንደደረሰብኝ እና እንዴት ተጽዕኖ እንዳደረሰብኝ ለማወቅ እየሞከርኩ ነው" ትላለች ኬት።