ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ "በመበስበስ ላይ ያሉ" ያሏቸውን የአውሮፓ አገራት እና "ደካማ" መሪዎቻቸውን ወቀሱ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ አገራት መሪዎችን "ደካማ" በማለት ወቅሰው፤ ዋሽንግተን ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ልትቀንስ እንደምትችል ጠቆሙ።
ከአሜሪካው ፖለቲኮ ዲጂታል ጋዜጣ ጋር ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሰ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ትራምፕ፤ የአውሮፓ አገራትንም "በመበስበስ ላይ ያሉ" በማለት ወርፈዋል።
እነዚህ አገራት ስደትን መቆጣጠር ወይም ዩከሬን ከሩሲያ ጋር የገባችበትን ጦርነት ለመቋጨት ጥብቅ እርምጃ አልወሰዱም ብለዋል። ዩክሬን "እስከምትወድቅ ድረስ" እንድትዋጋ አድርገዋል በማለትም ከስሰዋል።
የአውሮፓ መሪዎች አሜሪካ መራሹ የሰላም ጥረት፤ በፍጥነት መፍትሔ ለማምጣት ሲል የአህጉሩን የረዥም ጊዜ ጥቅም ይጎዳል የሚል ፍራቻ አላቸው። በዚህም የተነሳ አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ሞክረዋል።
ለትራምፕ ንግግር ምላሽ የሰጡት የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩቬት ኩፐር፤ መከላከያ ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት እና አህጉሪቱ ከዩክሬን የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በመጥቀስ አውሮፓ ውስጥ የሚታየው "ጥንካሬ" መሆኑን አስገንዝበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አክለውም፤ ትራምፕ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን በመጥቀስ "ለሰላም እየሠሩ ነው"፤ "አንድ ፕሬዝዳት ደግሞ (ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን) እስካሁን ድረስ በድሮን እና በሚሳኤል ጥቃት ግጭቱን የበለጠ ለማባባስ እየፈለገ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለማድረግ ሲሉ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ላይ የሚያደርጉትን ጫና አበርትተዋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ግዛቱን ለሞስኮ አሳልፎ እንዲሰጥ እየጎተጎቱም ይገኛሉ።
ዘለንስኪ ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ዩክሬን እና አውሮፓ "ጦርነቱን ለመቋጨት ወደሚያስችል እርምጃ የሚወስዱ ሁሉም ክፍሎች" ላይ በንቃት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። የሁለቱ አካላት የሰላም ዕቅድ በአሁኑ ሰዓት ይበልጥ እንደዳበረም አክለዋል።
የሰላም ዕቅዱ ረቡዕ ዕለት ለአሜሪካ ይቀርባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ትራምፕ በአውሮፓ ላይ አዲሱን ትችታቸውን ያሰሙት የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬን የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም ስለሚደረገውን የጋራ ጥረት ለመወያየት በለንደን ከተሰበሰቡ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
አውሮፓ ጦርነቱ እንዲቋጭ ማድረግ ትችል እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ፤ "ያወራሉ ግን አይፈጽሙም። ጦርነቱ ደግሞ እንዲሁ መካሄድ እየቀጠለ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከሳምንታት በፊት ከዩክሬን እና ሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር የተናጠል ንግግር በማድረግ ጦርነቱን ለመቀስቆም ሞክረዋል። እስካሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
ዩክሬን፤ በአሜሪካ የተዘጋጀው የሰላም ዕቅድ ወደፊት ሊፈጸሙ ለሚችሉ ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚያጋልጣት ትሰጋለች። በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ አሜሪካ ለስምምነቱ ከምታደርገውን ድጋፍ እንድትቆጠብ ለማድረግ በአውሮፓ እና በኔቶ መሪዎች ላይ ጫና እያሳደሩ ነው።
ትራምፕ ማስረጃ ባያቀርቡም ዘለንስኪ ለሰላም እንቅፋት እንደሆኑ እሑድ ዕለት ጠቁመዋል። ሩሲያ በአንጻሩ ለሰላም ዕቅዱ ጥሩ ምልከታ እንዳላት አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከፖለቲኮ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የዩክሬን ተደራዳሪዎች በአሜሪካ የተዘጋጀውን ዕቅድ "እንደወደዱት"፤ ዘለንስኪ ግን እስካሁን ድረስ እንዳላነበቡት ተናግረዋል።
ዩክሬን የዘገየውን ምርጫ ማካሄድ እንዳለባት በድጋሚ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዝዳንቱ፤ ጦርነቱን ምርጫ ላለማድረግ እየተጠቀመችበት ነው ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ሰኔ 2016 ዓ.ም. ቢጠናቀቀም የሩሲያን ወረራ ተከትሎ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ምርጫውም ታግዷል።
ከዚህ የትራምፕ ንግግር በኋላ ጋዜጠኞችን ያነጋገሩት ዘለንስኪ በበኩላቸው፤ "ለምርጫ ዝግጁ" መሆናቸውን ተናግረዋል። ሕጉን ሊቀይር የሚችል ዕቅድ እንዲዘጋጅ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉም ገልጸዋል።