ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ምሕረት ከተደረገላቸው በኋላ ሪፐብሊካን ፓርቲን ሳይቀላቀሉ የቀሩትን ዴሞክራት የኮንግረስ አባል ወቀሱ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ምሕረት ከተደረገላቸው ከሰዓታት በኋላ ፓርቲያቸውን ሳይቀይሩ ዴሞክራቶችን ወክለው ለምርጫ እጩነት የቀረቡትን ሄንሪ ኩዌየርን "ታማኝነት ይጎድለዋል" በማለት ወቀሱ።
ትራምፕ፤ ባለፈው ዓመት በሙስና እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ በማቅረብ ወንጀል ለተከሰሱት የቴክሳስ ተወካይ ምሕረት ያደረጉት ረቡዕ ዕለት ነበር። ለፖለቲከኛው ምሕረት ያደረጉት "ድንበሮች ይከፈቱ [የሚለውን ፖሊሲ] በድፍረት በመቃመው" በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ፖለቲካዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል በሚል ነበር።
ምሕረት የተደረገላቸው ዲሞክራቱ ሄንሪ ኩዌየር የቀድሞ ፓርቲያቸውን ትተው ሪፐብሊካኖችን እንደሚቀላቀሉ ተጠብቆ ነበር። ፖለቲከኛው ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ ሪፐብሊካኖች በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በጠባብ ልዩነት የያዙትን አብላጫ ወንበር እንደሚያጠናክሩ ተስፋ ሰንቀው ነበር።
ሄንሪ ኩዌየር ግን ምሕረት ከተደረገላቸው ከሰዓታት በኋላ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው በድጋሚ ለምርጫ ለመወዳደር ራሳቸውን በእጩነት በማቅረብ የሪፐብሊካኖችን ተስፋ አምክነዋል። ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው "ምን ዓይነት የታማኝነት ጉድለት ነው" ሲሉ ኩዌየርን ተችተዋል። "እንግዲያውስ፤ በቀጣይ ጊዜ ጥሩ ሰው መሆን የለም" ብለዋል።
በባይደን አስተዳደር ሥር የነበረው የፍትሕ መሥሪያ ቤት ኩዌየር እና ባለቤታቸው ላይ ክስ የመሰረተው በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም ከሚፈልጉ አካላት 600,000 ዶላር ተቀብለዋል በሚል ነበር። ለፖለቲከኛው ገንዘብ ሰጥተዋል የተባሉት ባለቤትነቱ የአዘርባጃን መንግሥት የሆነ የነዳጅ ኩባንያ እና ስሙ ያልተጠቀሰ የሜክሲኮ ባንክ ናቸው።
ጥፋተኛ እንዳልሆኑ የሚገልጹት ጥንዶች፤ ሴራ፣ ሙስና፣ የገንዘብ ማጭበርበር፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ለውጭ ድርጅቶች ወኪል ሆኖ መንቀሳቀስን የሚከለክለውን ሕግ የመጣስ ወንጀሎችን ጨምሮ 14 ክሶች ቀርቦባቸዋል።
ትራምፕ እሑድ ዕለት ባጋሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው "ግራ አክራሪ" ዴሞክራቶች መካከለኛ ዴሞክራት የሆነው ኩዌየር እና ቤተሰቡን "ለማጥፋት" "በምሕረት የለሽነት" ዘምተዋል ሲሉ ከስሰዋል። "ይህንን ሁሉ [የሚያደርጉት] ሄንሪ የድንበር ደኅንነት [እንዲጠበቅ] በጽኑ ስለፈለገ ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ረዘም ባለ ጽሑፋቸው ፖለቲከኛውንም ሆነ ቤተሰቡን አነጋገረው እንደማያውቁ፤ ነገር ግን "እጅግ በመጥፎ ሁኔታ ለተንገላታው" ቤተሰቡ "በመታገላቸው በጣም ጥሩ ስሜት እንደሚሰማቸው" ገልጸዋል።
ኩዌየር ምሕረት ከተደረገላቸው በኋላ ዴሞክራት ፓርቲን ወክለው ለመወዳደር መወሰናቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ "ከሳምንታት በፊት እርሱ እና ባለቤቱ ቀሪ ሕይወታቸውን በእስር ቤት እንዲያሳልፉ ይፈልጉ ከነበሩ፤ ምናልባትም አሁንም ከሚፈልጉ ግራ አክራሪ ቆሻሾች ጋር መሥራት ቀጥሏል" ብለዋል።
ይህ ዓይነቱ "የታማኝነት ማጣት" የቴክሳስ መራጮች እና አባታቸው ምሕረት እንዲደረግለት ለፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ የጻፉትን የኩዌየር ሴት ልጆች የሚያስደስት እንደማይሆን ትራምፕ በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ኩዌየር በበኩላቸው እሑድ ዕለት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በዴሞክራቲክ ፓርቲ እንደሚቀጥሎ አስረግጠዋል። "አሜሪካዊ ነኝ፣ ቴክሳን ነኝ እና ዴሞክራት ነኝ፤ በዚሁ ቅደም ተከተል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ስላሰፈሩት ጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት ፖለቲከኛው፤ "ወግ አጥባቂ ዴሞክራት ነኝ፤ ነገር ግን ከፕሬዝዳንቱ ጋር እሠራለሁ" ብለዋል።