በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዳሳሰቡት የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ

በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት እየተፈጸሙ ያሉ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ጥቃቶች እንዳሳሰቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ አርብ ኅዳር 07/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉ የድሮን ጥቃቶች እና ሌሎች ግጭቶች በክልሉ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱት አውዳሚ ጉዳት በእጅጉ እንዳሳሰበው አመልክቷል።

በአማራ ክልል ውስጥ ካለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ለወራት እየተካሄደ ባለው ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ሌሎችም ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ግጭቱን በተመለከተ ከዚህ በፊትም መግለጫ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ባወጣው መግለጫ ላይ በተለይ በመንግሥት ኃይሎች የሚፈጸሙ የሰው አልባ አውሮፕላኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ጉዳቶች እየደረሱ መሆናቸውን ገልጿል።

በማሳያነትም ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ዋደራ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ከመንግሥት ኃይሎች በኩል ተፈጽሟል በተባለ የድሮን ጥቃት ሦስት መምህራንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገላቸውን አመልክቷል።

መግለጫው ጨምሮም በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ በሚገኝ የተወሰነ ስፍራ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች እንደነበሩ የደረሱት ሪፖርቶች መጠቆማቸውን ገልጿል።

በተመሳሳይ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋበር ከተማ በሚገኝ የአውቶብስ መናኸሪያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአውቶብስ ለመሳፈር ሲጠብቁ የነበሩ 13 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።

ይህ የድሮን ጥቃት በተፈጸመበት ጊዜ የፋኖ ታጣቂዎች በአካባቢው ይንቀሳቀሱ እንደነበር እና በደብረ ማርቆስ እንዲሁም በሌሎች የምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንም ገልጿል።

ቀደም ባሉ ክስተትም ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም. በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ በምትገኘው ጯሂት ከተማ የመንግሥት ኃይሎች በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ በፈጸሙት የከባድ መሳሪያ ጥቃት 6 ሰዎች መገደላቸውን እና 14 መቁሰላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መግለጫ ጠቅሶ፣ አብዛኞቹ ሰዎች የተገደሉት ቤታቸው ውስጥ ሳሉ ነው ብሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በመግለጫው ላይ እንዳለው እንዲህ አይነቶቹ ጥቃቶች በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ “በዘፈቀደ የሰዎችን ሕይወት ከማጥፋት ጋር” የሚስተካከል ነው ሲል አሳስቧል።

በመንግሥት ኃይሎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ከሚሞቱ ሰዎች በተጨማሪም የፋኖ ታጣቂዎች በተመሳሳይ በሚወስዷቸው እርምጃዎች 21 የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት መገደላቸውንም መግለጫው አሳውቋል።

በመንግሥት ባለሥልጣናቱ ላይ ግድያው የተፈጸመው በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች በተለያዩ ቀናት መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፣ በጥቅምት 17/2016 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዓለም በር እና ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም. አዊ ዞን ጅባይት ወረዳ ውስጥ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣውን ይህን መግለጫ በተመለከተ ከመንግሥት በኩል አስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ያወጣው ይህ መግለጫ በአማራ ክልል ላይ ያተኮረ ይሁን እንጂ በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች የቀጠሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የዘፈቀደ እስሮች እንዳሳሰቡት ገልጿል።

መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ውጥረት ተባብሶ ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ወደለየለት ግጭት መገባቱ ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥቱ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ ኃይሎቹን ቢያሰማራም፣ ክልሉ ወደ መረጋጋት ሳይመለስ ግጭቱ ባስ፣ ቀዝቀዝ እያለ ወራት ተቆጥረዋል።

በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት መቀጠሉ ያሳሰባቸው የተለያዩ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ ቢያርቡም ቀውሱ በአሁኑ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል።