በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ቀናት ከባድ ውጊያዎች መካሄዳቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

በአማራ ክልል ወራት ባስቆጠረው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ባለፉት ቀናት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ተባብሶ መቀጠሉን በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ባለፈው ዓመት የመጨረሻ ወራት ተቀስቅሶ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ወታደሮች መካከል እየጠነከረ እና ጋብ እያለ ሲካሄድ የቆየው ውጊያ ባለፈው ሳምንት በብዙ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱ ተነግሯል።

የክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግሥቱ በተለያዩ ጊዜያት የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ መግታት መቻሉን ቢገልጹም አሁን እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች በነዋሪዎች ዘንድ የደኅንነት ስጋት መፈጠሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።

ዛሬ [ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም.] ቢቢሲ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ሰዎችን በምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች፣ በሰሜን ሸዋ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች “ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ ነው” ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ጦርነቱ ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች አንዱ የቋሪት ወረዳ ነው። የወረዳው ነዋሪ የሆኑት ሙሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አቶ አበበ፣ ከአራት ቀን በፊት ጀምሮ የወረዳውን ማዕከል ለመቆጣጠር “የመንግሥት ወታደሮች ዘመቻ ከፍተው ከባድ ውጊያ እየተደረገ” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተኩሱ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ነው የሚሉት አቶ አበበ፣ ውጊያው ከተጀመረ አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ዛሬ ማክሰኞ ከቢቢሲ ጋር እየተነጋገሩ በነበረበት ወቅት ጭምር መቀጠሉን ገልጸዋል።

“መከላከያ ሠራዊት አካባቢዎቹን ያለምንም ልዩነት በከባድ መሣሪያ እየደበደበ ነው” ያሉት አቶ አበበ፣ ጦርነቱ በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን በመጥቀስ፣ ምንም እንኳ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት መግለጽ ባይችሉም በአካባቢያቸው ያሉ ቤቶች እና ተቋማት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል።

በቋሪት ወረዳ ከወራት በፊት ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. በፋኖ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ጦርነት ተካሂዶ እንደነበር ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሌላ ነዋሪ ያስታወሱ ሲሆን፣ “ወዲያው መከላከያ አካባቢውን ለቆ ወጥቶ ነበር” ብለዋል።

ከዚያም በኋላ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ጊዜያት አካባቢውን መልሶ ለመቆጣጠር ተደጋጋሚ መከራ ማድረጉን እና በዚህም ምክንያት “በተፈጸሙ የድሮን እና የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት” መድረሱን አመልክተዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል አንድ ዞን በሆነው በምሥራቅ ጎጃም አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥም ባለፉት ቀናት በከባድ መሣሪያ የታገዘ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በዞኑ በተለይ የቢቡኝ ወረዳ ማዕከል የሆነችውን ድጎ ጽዮንን ለመቆጣጠር ከቅዳሜ ጀምሮ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የወረዳው ነዋሪ አቶ መላኩ ቢሻው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግጭቱ ዛሬም [ማክሰኞ] ለአራተኛ ቀን ቀጥሏል ያሉት አቶ መላኩ፣ ከወረዳዋ ማዕከል ድጎ ጽዮን በተለያዩ አቅጣጫዎች ውጊያ እተካሄደ ነው ብለዋል።

ለቀናት የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ ትናንት [ሰኞ] “ከሞጣ አቅጣጫ የተተኮሰ መድፍ አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል” ብለዋል።

መድፉ የተተኮሰው “የከተማዋ ነዋሪ ለለቅሶ ተሰብስቦ በነበረበት ወቅት ሲሆን” ቅምቡላው ሜዳ ላይ ማረፉን አቶ መላኩ ገልጸዋል። ነገር ግን በለቅሶው ምክንያት የተሰባሰበው ሰው በአቅራቢያ ስለነበር “ፍንጣሪው አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን” ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህ ውጪ በነዋሪዎች ላይ እስካሁን የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እንደማያውቁ የገለጹልን አቶ መላኩ፣ “መከላከያ በያዛቸው አካባቢዎች ግን ወጣቶች መታፈናቸውን እና አንዳንዶቹም ‘ፋኖን ትደግፋላችሁ’ በሚል ሰበብ መገደላቸውን ሰምቻለሁ” ብለዋል።

ቢቡኝ ወረዳ እንደ ቋሪት ወረዳ ሁሉ ከሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር የምትገኝ መሆኑንም ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ተቀስቅሶ አሁን እየተባባሰ ያለው ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ ይገኛል።

ለአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ከሚቀርቡት የአማራ ክልል ዞኖች አንዱ በሆነው ሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ “በወታደራዊ ሄሊኮፕተር ጭምር የታገዘ ጥቃት መፈጸሙን እና በዚህ ምክንያት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን” ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ሳህለ መሳፍንት [ስማቸው የተቀየረ] የተባሉት የወረዳው ነዋሪ እንደገለጹት በአንኮበር ወረዳ ከእሁድ [25/2016 ዓ.ም.] ጀምሮ ነዋሪውን ስጋት ውስጥ የከተተ ከባድ ጦርነት በመከላከያ ሠራዊት እና በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች መካከል እተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በወረዳው ወደራ፣ አልዩ አምባ፣ ሃራምባ እና ደረቦ በተባሉ የገጠር ቀበሌዎች ላይ “የአየር ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል አቶ ሳህሌ።

ጨምረውም በአካቢቢው ባለ አንድ “ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት፣ በርካታ ሰዎች እንደሞቱ እና ከሟቾቹ መካከልም መምህራን” እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።

አቶ ሳህለ ለቢቢሲ እንዳሉት “ከእሁድ ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው ውጊያ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ባሉ ሌሎች አካባቢዎች፣ በተለይ በመንዝ እና በአንጾኪያ አካባቢዎች መኖሩን” በአካባቢዎቹ ካሉ ነዋሪዎች ሰምተዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ በመትገኘው በታሪካዊቷ ከተማ ላሊበላ ውስጥም በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ መኖሩን ሮይተርስ የዜና ወኪል የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠቅሶ ዘግቧል።

እየተካሄደ ያለው ውጊያም የከባድ መሳሪያን ያካተተ በመሆኑ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን ከአለት የተፈለፈሉትን የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትን ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል በሚል በነዋሪዎቹ ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል።

እሁድ ዕለት ከአብያተ ክርስቲያናቱ አቅራቢያ ከሚገኝ ስፍራ ላይ የመከላከያ ወታደሮች አስራ አንድ ጊዜ ከባድ መሳሪያ በአካባቢው ወደሚገኙ ተራሮች መተኮሳቸውን አንድ ዲያቆን ለሮይተርስ ተናግሯል።

የከባድ መሳሪያ ተኩሱ የሚፈጥረው ንዝረት በጥንታዊ ቅርሶቹ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ አዲስ የተቀሰቀሰው ውጊያ ባለፈው ቅዳሜ መጀመሩን ሁለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ባለፉት ቀናት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በአካባቢው ባሉ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መካሄዱን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚህም በዞኑ ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

በሌሎችም የአማራ ክልል አካባቢዎች ግጭቶች እና ውጊያዎች እየተካሄዱ ስለመሆናቸው ከተለያዩ ምንጮች እየተነገረ ቢሆንም፣ በበርካታ ስፍራዎች የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ያለውን ሁኔታ ከነዋሪዎች ማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።

ቢቢሲ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች እየተካሄዱ ናቸው ስለተባሉት ግጭቶች እና ውጊያዎች ተጨማሪ መረጃ ከክልሉ መስተዳደር ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ባለፈው ሳምንት በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ያስቆመው ስምምነት የተፈረመበትን አንደኛ ዓመት አስመልክተው ምዕራባውያን አገራት ባወጡት መግለጫ ላይ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት እንዳሳሰባቸወቅ ገልጸው ነበር።

በትግራይ ክልል የተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን በመበተን ወደ ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት ለማስገባት እንዲሁም ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ግጭት መቀስቀሱ ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች በክልሉ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን ለቀናት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የክልሉ መስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቆ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ ተሰማርቷል።

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በአማራ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር መቆጣጠሩን ቢገልጽም አሁንም ድረስ በታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭቶች እየተካሂዱ በመሆናቸው በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል።

በዚህም ሳቢያ በክልሉ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የትራንስፖርት እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች የተቋረጡ መሆናቸውን እንዲሁም የመድኃኒት እና የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረት ማጋጠሙን በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይ በአማራ ክልል ለወራት በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ግድያ እና መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ መንግሥት ሪፖርቱ በአስተማማኝ መረጃ ላይ ያልተመሠረት እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው በማለት ተቃውሞታል።