በላሊበላ በከባድ መሳሪያ ጭምር የሚካሄደው ውጊያ ለቅርሶች ደኅንነት ስጋት ሆኗል

በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እና በታሪካዊቷ ከተማ ላሊበላ አካባቢ በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከረቡዕ ጠዋት ጀምሮ ከባድ ውጊያ ሲካሄድ እንደነበረ እና ታሪካዊ ቅርሶች ደኅንነት እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ቀናት አንስቶ ከከተማዋ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው ውጊያ ማክሰኞ እና ረቡዕ ቀጥሎ በከባድ መሳሪያ ጭምር ሲካሄድ እንደነበረ ከፍተኛ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የላሊበላ ቅርሶች ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ስጋት የላቸውም ብሏል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ “የላሊበላ ከተማ እና ቅርሶቿ በሙሉ ከክልሉ መረጃ እስካጣራሁበት እስከአሁን ሰዓት ድረስ ሰላም ናቸው” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም በቅርሱ ዙሪያ አሉባልታዎች እየተናፈሱ እንደሆነ ገልጸው ይህንንም በተመለከተ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት በዓለም ቅርስነት በምትታወቀው የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ እና የቱሪስቶች መዳረሻ በሆነችው ላሊበላ ከተማ ሊያርፍ የነበረ አውሮፕላን በከተማዋ በነበረ ውጊያ ምክንያት ሳያርፍ መመለሱን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት ቀናት በታሪካዊቷ ከተማ በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ከባድ ውጊያ የጥንታውያኑን አብያተ ክርስቲያንት ደኅንነትን አደጋ ላይ እንዳይጥለው ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያናገረው አንድ ዲያቆን እንደገለጹት ለአብያተ ክርስቲያናቱ መጠለያነት የተሰሩ የብረት ሽፋኖች በተባራሪ ጥይቶች መመታታቸውን ተናግረዋል።

ስማቸው ያልተጠቀሰው ዲያቆን እንደተናገሩት “[ተዋጊዎቹ] ሁሉንም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች እየተጠቀሙ ነው። የተኩሱ ንዝረት ይሰማኛል” በማለት ውጊያው በከተማዋ ውስጥ የፈጠረውን ስጋት እና የደቀነውን አደጋ ገልጸዋል።

ባለፉት ቀናት የላሊበላ ከተማ የተለያዩ ክፍሎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች ስር ቆይተው እንደነበር ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሦስት ነዋሪዎች ተናግረዋል። ነገር ግን ረቡዕ ዕለት ለሰዓታት ከተካሄደ ውጊያ በኋላ የከተማዋ አብዛኛው ክፍል በፋኖ ታጣቂዎች እጅ ስር መግባቱን ቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ በበረታበት ጊዜ ከተማዋን ለቀናት መቆጣጠር ችለው እንደነበር ይታወሳል።

በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ በታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረገው ግጭት ቅዳሜ ዕለት እንደ አዲስ ማገርሸቱን አንድ ነዋሪ “ውጊያው አይሎ፣ ዛሬ [ረቡዕ] ጠዋት ከአንድ ሰዓት ገደማ ጀምሮ ቀኑን ሙሉ በከባድ መሣሪያ ጭምር ሲካሄድ መዋሉን” ተናግረዋል።

በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል እስከ ማክሰኞ ድረስ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩ ሲሆን፣ ረቡዕ ጠዋት ተቀሰቅሶ ለረጅም ሰዓታት ከተካሄደው ከባድ ውጊያ በኋላ ግን “በከተማዋ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያሉት የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ ነዋሪው ገልጸዋል።

ነዋሪዎች በውጊያው በመላዋ ከተማዋ ውስጥ የሚሰሙ እና ከባድ ንዝረትን የፈጠሩ የከባድ ጦር መሳሪያዎች ተኩስ ልውውጥ እንደተካሄደ እና “ብዙ ሰው” እንደተጎዳ ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቅዳሜ’ ዕለት በሁለቱ ኃይሎች መካከል ይካሄድ የነበረው ግጭት እና ተኩስ ይሰማ የነበረው ከከተማዋ ራቅ ብሎ እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪ፣ በታሪካዊቷ ከተማ በከባድ ማሳሪያ ጭምር ውጊያ መካሄዱ “የሚያሳዝን እና ተደርጎ የማይታወቅ ነገር ነው እያየን ያለነው” ብለው ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

በላሊበላ ከተማ ባለፉት ቀናት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ክፍት የነበሩ ሲሆን፣ ረቡዕ ጠዋት ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ በከተማዋ ያሉ ተቋማት ዝግ ሆነው ውለዋል። ሰዉ ከቤቱ ሳይወጣ መዋሉንም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት ቀናት በተካሄዱ ግጭቶች ምክንያት የተገደሉ የከተማው የፖሊስ አባላት እና ሚሊሻ ቤተሰቦች ሐዘን ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ነዋሪ፣ በውጊያው የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በትክክል አይወቁ እንጂ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ውጊያው ወደ ከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል በመስፋት ከባድ መሳሪያዎችን ጨምሮ መካሄዱ የሚፈጠረው ንዝረት በጥንታዊዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሯል።

“ተኩሱ የሚፈጥረው የመሬት ንቅናቄ ስላለ ቅርሱ ላይ ጉዳት ያመጣል ብለን እንሰጋለን። እግዚአብሔር በፈቀደ ይጠብቀዋል ብለን እናስባለን” ከዚያ ውጪ ውጊያው ከከተማ ውጪ የማይሆን ከሆነ የኢትዮጵያውያን ቅርስ ላይ ጉዳት የመድረስ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ከባድ ውጊያ ምክንያት በላሊበላ ከተማ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውን ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ መምህርት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መምህሩ ግጭቱ እንደ አዲስ ቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ሳይቆም “ጠዋት ደህና ቢሆን ከሰዓት ጦርነት ነው የሚሆነው። ዛሬ [ረቡዕ] ግን ሙሉ ቀን በጣም ከፍተኛ ውጊያ ነው የተካሄደው” በማለት ላሊበላ ከተማ ላይ እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ተካሂዶ አያውቅም ብለዋል።

አክለውም ከዚህ ቀደም ውጊያዎች ከከተማዋ ውጭ ይካሄዱ እንደነበር በመጥቀስ “ለአብያተ ክርስቲያናቱ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር” በማለት “ዕድሜዬ 40 ዓመት ሆኗል። ላሊበላ ከተማ ውስጥ እንደዛሬው ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ አልገጠመኝም። ቤት ውስጥ ተደብቀን ነው ያለነው” ብለዋል።

በላሊበላ ከተማ ስላለው ሁኔታ ከአማራ ክልል እና ከሰሜን ወሎ ዞን መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የፌደራል መንግሥቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለሮይተርስ በሰጡት አስተያየት በላሊበላ እና በአካባቢዋ ግጭት ስለመኖሩ የሚወጡ ሪፖርቶችን አስተባብለው ስፍራው ሰላም መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ውጥረት ተባብሶ ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ወደለየለት ግጭት መገባቱ ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥቱ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ ኃይሎቹን ቢያሰማራም፣ ክልሉ ወደ መረጋጋት ሳይመለስ ግጭቱ ባስ፣ ቀዝቀዝ እያለ ወራት ተቆጥረዋል።

በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት መቀጠሉ ያሳሰባቸው የተለያዩ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ ቢያርቡም ቀውሱ በአሁኑ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል።