7-0፡ በአንፊልድ 'ክብሩን ያጣው' ዩናይትድ ‘የቁም ሞት ሞተ’

‘የተዋረደየተፈረካከሰ አሳፋሪ’

ጋሪ ኔቪል የቀድሞ ክለቡ በሊቨርፑል ማመን በሚያቅት ሁኔታ 7 ለ 0 በሆነ ውጤት ከተረታ በኋላ ክለቡን የገለጸበት ቃላቶች ናቸው።

የዩናይትድ አምበል የነበረው ጋሪ ኔቪል ለዚህ ታሪካዊ ሽንፈት ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴሽ ነው ይላል።

ዩናይትድ በሊቨርፑል 7 ለ 0 በሆነ ውጤት ሲሸነፍ ይህ በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ነው። 7ለ0 መሸነፍ ግን ለቀያይ ሴጣኖቹ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ከዚህ ቀደም እአአ በ1926፣ 1930 እና በ1931 እንድ ቅድመ ተከተላቸው በብላክበርን ሮቨርስ፣ አስቶን ቪላ እና ዎልቭስ 7ለ0 ተረምርመው ነበር።

በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ዩናይትዶች በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ተንቀሳቅሰው ነበር። የተቆጠረባቸውም 1 ጎል ብቻ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ነገሮች ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀያይረው 6 ጎሎችን አስተናግደዋል።

“ሁለተኛው አጋማሽ ፍጹም አሳፋሪ” ነበር ሲል ጋሪ ኔቪል ለስካይ ስፖርት ተናግሯል።

“የዚህን ግጥሚያ አደገኛነት አልተረዱትም። የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች በቁማቸው ነው የተበሉት”

ከሽንፈቱ በኋላ ብዙ ትችቶችን እያስተናገደ ያለው ብሩኖ በአንድ ክስተት ተቀይሮ የገባው የሊቨርፑሉ ስቴፋን ኳስ ይዞ ሲያልፈው ተከትሎ ኳስ እንደማስጣል ሲቆም ታይቷል። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ረዳት ዳኛውን ሲገፈተር ታይቷል።

በ85ኛው ደቂቃ ማርከስ ራሽፈርድ ተቀይሮ ሲወጣ ቅያሬው ለምን ተከናወነ በሚል በሚመስል መልኩ ብሩኖ ጥያቄ ማስነሳቱ ለጋሪ ኔቪል የሚዋጥ አይደለም።

“እጁን ወደ ላይ አንስቶ፤ ‘እኔ ለምን አልተቀየርኩም’? በማለት ይጠይቃል” ብሏል ኔቪል ከጨዋታው በኋላ ስለ ብሩኖ ሲናገር።

“ይህ ከማንችስተር ዩናይትድ አምበል የሚጠበቅ አይደለም። እርግጠኛ ነኝ ቴን ሃግ ለዚህ ማረሚያ ይሰጣል”

ብዙ ትችቶችን ያስተናገደው ብሩኖ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች መልስ ለመስጠት ወደ ኋላ አላላም። “እጅግ ያበሳጫል፣ ተስፋ ያስቆርጣል፤ በጣም መጥፎ ውጤት ስለሆነ አሳዛኝ ነው” በማለት ተናግሯል።

ትናንት የተፈጠረው ችግር ምን ነበር?

ሌላኛው የዩናይትድ የቀድሞ አምበል ሮይ ኪን ችግር ያልሆነ ነገር የለም ይላል።

ዩናይትድ የፕሪሚየር ሊግ አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም በሂደት ጥሩ ለውጥ በማምጣት ካለፉት 22 ጨዋታዎች 49 ነጥቦችን መሰብሰብ ችለው ነበር።

በትናንት ምሽቱም ጨዋታ ዩናይትድ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ ተሻረበት እንጂ አማካዩ ካዜሚሮ ጎል አስቆጥሮ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ግን ነገሮች በፍጥነት ተቀያየሩ። “ነገሮች ሲበላሹ ዋና ተጫዋቾች ጠፉ’ ይላል ሮይ ኪን።

“በዳሎት እና አንቶኒ መካከል መግባባት አልነበረም። አንቶኒ ስራው ባለመስራቱ ዩናይትድ በ10 ተጫዋች የሚጫወት ነበር የሚመስለው። . . . ምሳሌነቱን በተግባር ማሳየት የነበረበት ብሩኖ እጁን በተደጋጋሚ ሲያወዛውዝ ነበር” በማለት የተናገረው ደግሞ የማንችስተር ሲቲ የቀድሞ አማካይ ሚካህ ሪቻርድስ ነው።

አስልጣኝ ቴን ሃግ በበኩላቸው ቡድናቸው በሁለተኛው አጋማሽ "እንደ ቡድን አልተጫወተም።"

"ሁለተኛው አጋማሽ እኛ አልነበርንም። የኛን ደረጃ የሚመጥን አልነበረም። . . . እቅዳችንን አልተከተልንም፤ የምናረገው ጠፍቶን ነበር። ሥራችንን አልሰራንም። . . . ፕሮፌሽናል አልነበርንም" ሲሉ ቴን ሃግ ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።