ኔታንያሁ ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን አስከሬን እንዲፈልግ ጫና ለማድረግ "ቁርጠኛ መሆናቸውን" ተናገሩ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ መሪነት በተፈጸመው ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች በተዘጋጀ መታሰቢያ ላይ በጋዛ የሚገኘውን የታጋቾች አስከሬን ለማስመለስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አገራቸው ሽብርተኝነትን በ"ሙሉ ኃይል" መዋጋቷን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ ይህንን ያሉት ሐማስ የሁለት ተጨማሪ ታጋቾችን አስከሬን ከመለሰ ከሰዓታት በኋላ ቢሆንም የቀሩትን 19 አስከሬኖች ማግኘት እንዳልቻለ ተናግሯል።

ባለፈው ሳምንት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ሐማስ ሁሉንም አስከሬኖች ባለመመለሱ በእስራኤል ቁጣ ቀስቅሷል።

አሜሪካ በበኩሏ ይህንን እንደ ተኩስ አቁም ጥሰት እንደማታየው ገልጸላች።

እንዲሁም ሐሙስ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ "ሰዎችን መግደሉን ከቀጠለ" ውጊያው እንደገና እንዲቀጥል ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የዩኤስ ፕሬዝደንት በትሩዝ የማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ሐማስ በጋዛ በአገር ውስጥ ያሉተቀናቃኞቻቸው ዒላማ አድርገዋል በሚል የወጡ ሪፖርቶችን በመጥቀስ "ከመግባት እና ከመግደል ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖረንም" ሲሉ ጽፈዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ወታደሮችን በጋዛ እንደማያሰማሩ ተናግረው ነበር።

ባለፈው ሐሙስ የእስራኤል መንግሥት ሐማስ ለዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ረቡዕ ምሽት ያስረከበው ሁለት አስከሬኖች ኢንባር ሃይማን እና ሻምበል ሙሀመድ አል አታራሽ እንደሆኑ ማረጋገጡን አስታውቋል።

ሐማስ ከሰኞ ጀምሮ ያስረከበው የታጋቾች አስከሬን ቁጥር ከ28ቱ ዘጠኝ ብቻ ነው።

ሰኞ ዕለት በሕይወት ያሉት 20 ታጋቾች መለቀቃቸውን ተከትሎ እስራኤል 250 እስረኞች እና 1,718 በተለያዩ ማቆያዎች ታጉረው የነበሩትን ፍልስጤማውያንን ለቅቃለች።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው የቀሩትን አስከሬኖች ማፈላለግ እንደሚቀጥል ገልፆ ነገር ግን ከፍተኛ ጥረት እና ልዩ መሳሪያዎችን እንደሚፈልግ አስታውቋል።

እስራኤል ለአስከሬኖቹ መዘግየት ወደ ጋዛ የሚሄደውን የእርዳታ መጠን እንደምትገድብ በማስፈራራት ምላሽ ሰጥታለች።

ሐሙስ ዕለት ኔታንያሁ ለመስከረም 26ቱ ሐማስ ጥቃት በተዘጋጀ መታሰቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር የሁሉንም እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎች አስከሬን ከጋዛ ለማስመለስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አክለውም እስራኤል ዳግም ጥቃት የሚቃጣባት ከሆነ ዳግም ወታደራዊ ዘመቻዋን ለመጀመር ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል።

"ከሽብርተኝነት ጋር የምናደርገው ትግል በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል፤ ክፋት ጭንቅላቱን እንዲያነሳ አንፈቅድም፤ ሊጎዳን የሚነሳን በተመጣጣኝ ኃይል እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል።

የእስራኤል ጦር መስከረም 26 ለደረሰው ጥቃት ምላሽ በጋዛ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት ቢያንስ 67,967 ሰዎች መግደሉን ሐማስ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

20 ነጥቦች የያዘው የሰላም ዕቅድ ያለበትን ደረጃ ላይ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ከፍተኛ አማካሪዎች በበኩላቸው እስካሁን ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ ሐማስ የሞቱ ታጋቾቸችን አስከሬን ሙሉ በሙሉ ማስረከብ ባለመቻሉ የተኩስ አቁሙን ጥሷል ብላ እንደማታምን አስታውቀዋል።

አማካሪዎቹ ሐማስ በሕይወት ያሉ ታጋቾችን በሙሉ በመልቀቅ ለዕቅዱ ተግባራዊነት ያለውን ተገዢነት ማሳየቱን የተናገሩት አማካሪዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የሞቱ ታጋቾችን አስከሬን የመፈለግ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው "የቀሩት አስከሬኖችን ለመፈለግ እና ለማውጣት የተጠናከረ ጥረት እንዲሁም ዘመናዊ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ። ይህንን ዶሴ ለመዝጋት ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

ቀደም ሲል እስራኤል "ዘመቻው አልተጠናቀቀም" በማለት የቀሩ ታጋቾችን በሚመለከት "ምንም ማመቻመች" እንደማታደርግ አስታውቃ ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ጦርነት ዳግም የሚጀመር ከሆነ ሠራዊቱ በጋዛ ያለውን ሐማስ ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ "ሁሉን አቀፍ ዕቅድ" እንዲያዘጋጅ መታዘዙን አስታውቋል።

ሐማስ የ28ቱን ታጋቾች አስከሬን በሙሉ ካላስረከበ ወደ ጋዛ የሚገባውን ሰብዓዊ እርዳታ እንደምትገድብ እስራኤል አስጠንቅቃለች።