ሐማስ የታጋቾችን አስከሬን ለመለየት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል አለ

ሐማስ ረቡዕ ዕለት የተጨማሪ ሁለት ታጋቾችን አስከሬን ማስረከቡን ገልጾ፣ ነገር ግን የሌሎችን አስከሬን ከጋዛ ፍርስራሾች ውስጥ ለማውጣት ተጨማሪ ጊዜ እና የዘመኑ መሳሪያዎች ያስፈልጉኛል አለ።

የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ባወጣው መግለጫ ላይ ለሰላም ስምምነቱ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቆ እስካሁን ማስረከብ የቻለው የታጋቾች አስከሬን ሊደርስባቸው የቻላቸውን ብቻ መሆኑን ገልጿል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ለስምምነቱ ተገዥ ካልሆነ እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ልትቀጥል ትችላለች ብለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በበኩሉ በቀይ መስቀል በኩሉ የታጋቾችን አስከሬን መቀበሉን ገልጾ ማንነታቸውን የመለየት ሥራ ይቀራል ብሏል።

የእስራኤል ጦር ሕዝቡ በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቦ "የታጋቾቹን ማንነት የማረጋገጥ ሥራ ተሰርቶ በመጀመርያ ለቤተሰቦቻቸው እንደሚያሳውቅ" ገልጿል።

20 ነጥቦች የያዘው የሰላም ዕቅድ ያለበትን ደረጃ ላይ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ከፍተኛ አማካሪዎች በበኩላቸው እስካሁን ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ ሐማስ የሞቱ ታጋቾቸችን አስከሬን ሙሉ በሙሉ ማስረከብ ባለመቻሉ የተኩስ አቁሙን ጥሷል ብላ እንደማታምን አስታውቀዋል።

አማካሪዎቹ ሐማስ በሕይወት ያሉ ታጋቾችን በሙሉ በመልቀቅ ለዕቅዱ ተግባራዊነት ያለውን ተገዢነት ማሳየቱን የተናገሩት አማካሪዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የሞቱ ታጋቾችን አስከሬን የመፈለግ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ረቡዕ ማታ ሐማስ ያስረከባቸው አስከሬኖች ከታጋቾቹ መካከል መሆናቸው ከተረጋገጠ 19 አስክሬኖች ብቻ በጋዛ ይቀራሉ ማለት ነው።

በመጀመርያው የጋዛ ሰላም ዕቅድ መሰረት ሐማስ 28 በሕይወት የሌሉ ተጋቾችን አስከሬን ማስረከብ ይጠበቅበታል።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው "የቀሩት አስከሬኖችን ለመፈለግ እና ለማውጣት የተጠናከረ ጥረት እንዲሁም ዘመናዊ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ። ይህንን ዶሴ ለመዝጋት ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

ቀደም ሲል እስራኤል "ዘመቻው አልተጠናቀቀም" በማለት የቀሩ ታጋቾችን በሚመለከት "ምንም ማመቻመች" እንደማታደርግ አስታውቃ ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ጦርነት ዳግም የሚጀመር ከሆነ ሠራዊቱ በጋዛ ያለውን ሐማስ ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ "ሁሉን አቀፍ ዕቅድ" እንዲያዘጋጅ መታዘዙን አስታውቋል።

ረቡዕ ዕለት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ከተገናኙ በኋላ ሚኒስቴሩ እስራኤል ካትዝ፣ ሐማስ የሰላም ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያመነታ ከሆነ ጦሩ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል።

ማክሰኞ ዕለት ሐማስ ካስረከባቸው የታጋቾች አስከሬን መካከከል አንዱ የታጋቾች አይደለም በሚል መመለሱ ይታወሳል።

ሐማስ የ28ቱን ታጋቾች አስከሬን በሙሉ ካላስረከበ ወደ ጋዛ የሚገባውን ሰብዓዊ እርዳታ እንደምትገድብ እስራኤል አስጠንቅቃለች።

እስራኤል እስካሁን የ45 ፍልስጤማውያንን አስከሬን አስረክባለች።

የእስራኤል ታጋቾች አስከሬን ካልተለቀቀ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንቅፋት ሊገጥመው ይችላልም ተብሏል።

የእስራኤል መከላከያ "ሐማስ ስምምነቱን ማክበር አለበት። የታጋቾችን አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ይመልስ" ብሏል።

"ይህ ሳይሆን ከቀረ ወይም ሒደቱ ከዘገየ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል" ሲልም አስጠንቅቋል።

ሐማስ ስምምነቱን አላከበረም በሚል እስራኤል ሰብአዊ እርዳታ ለመገደብ እና የራፋሕን ድንበር ላለመክፈት ወስናለች።