ሐማስ በሕይወት ያሉ 20 እስራኤላውያን ታጋቾችን በሙሉ ለቀቀ

የእስራኤል መከላከያ በሕይወት ያሉትን 20 ታጋቾች በሙሉ መለቀቃቸውን አስታወቀ።

ለሁለት ዓመት ያህል የዘለቀውን ጦርነት ያስቆማል የተባለው እና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት የቀረበው የሰላም ዕቅድ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ነው ታጋቾቹ ሰኞ ጠዋት የተለቀቁት።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታጋቾቹን መለቀቅ "አዲስ ጅማሮ" ሲሉ ገልጸውታል።

የእስራኤል መከላከያ የተለቀቁትን 20 ታጋቾች ከቀይ መስቀል የተረከበ ሲሆን የተወሰኑት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።

በስምምነቱ መሠረት ከእስራኤል እስር ቤቶች የተለቀቁ ፍልስጤማውያንን የጫኑ አውቶብሶችም በእስራኤል ወረራ ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ፣ ራማላህ መድረሳቸው ተገልጿል።

"ይህ ታላቅ ቀን ነው። ይህ አዲስ ጅምር ነው" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ግብጽ ከማምራታቸው በፊት በእስራኤል ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

ሐማስ በበኩሉ በሕይወት ያሉ ሁሉንም ታጋቾች ማስረከቡን የገለፀ ሲሆን፣ የ28 ታጋቾች አስከሬንን በዛሬው ዕለት እንደሚያስረክብ አስታውቋል።

የእስራኤላውያኑ ታጋቾች ቤተሰቦች ደስታቸውን በተለያየ መንገድ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የታጋቾች እና የጠፉ ቤተሰቦች የተሰባሰቡበት 'ሆስቴስ ኤንድ ሚሲንግ ፋሚሊስ ፎረም' በማኅበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ "ወደ አገራችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ" ሲል ለጥፏል።

ፎረሙ "ከ738 አስጨናቂ ቀናት በኋላ" ወደ ቤተሰባቸው የተቀላቀሉትን ሰባት ታጋቾች በስም ዘርዝሮ ". . . ከእስር እንዲፈቱ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ወደ ለፉት ቤተሰቦቻችሁ፣ ጓደኞቻችሁ እና ይህች ቀን እንደምትመጣ አምኖ ወደ ተፋለመ ሕዝብ፣ ወደ እኛ እቅፍ እየተመለሳችሁ ነው" ሲል ጽፏል።

ፎረሙ አክሎም "ትግላችን አላበቃም። የመጨረሻው ታጋች እስኪመጣ እና ተገቢውን ቀብር እስኪፈጸምለት ድረስ አያበቃም። ይህ የእኛ የሞራል ግዴታ ነው። ያኔ ብቻ ነው የእስራኤል ሕዝብ ሙሉ የሚሆነው" ብሏል።

ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ከተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች ለቅቆ የወጣ ሲሆን ሐማስ ደግሞ ታጋቾቹን መልቀቅ ጀምሯል።

የእስራኤል ወታደሮች ስምምነት ወደተደረሰባቸው አካባቢዎች ቢመለሱም በአጠቃላይ ከጋዛ ሰርጥ ለቀው አልወጡም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ የእስራኤል መንግሥት እና የሐማስን ይሁንታ ካገኘ በኋላ ፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሰው መኖሪያቸው መመለስ ጀምረዋል።

በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት ሐማስ በሕይወት ያሉትን ሁሉንም ታጋቾች የለቀቀ ሲሆን፣ የ28 ታጋቾችን አስክሬንም ያስረክባል።

እስራኤል 250 ፍልስጤማውያን እስረኞች፣ ከጋዛ የታገቱ 1,700 ፍልስጤማውያንም ትለቅቃለች።