ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋዛ ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል እና ሐማስ 20 ነጥቦችን በያዘው የጋዛ ተቁስ አቁም ዕቅዳቸው የመጀመርያ ዙር ላይ መስማማታቸውን ተናግረዋል።
መስማማታቸው የተገለፀው ሐሙስ ዕለት ሲሆን ያንንም ተከትሎ የቀሩ እስራኤላውያን ታጋቾችን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ይለቀቃሉ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ለቅቆ በመውጣት እርዳታ እንዲገባ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች እንዲሁም በምን ያህል ጊዜ ተፈጸሚ እንደሚሆኑ እስካሁን ድረስ በግልጽ የቀረበ መረጃ የለም።
ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን የገደለበት እና 251 አግቶ የወሰደበት ሁለተኛ ዓመት ማክሰኞ ዕለት ታስቦ ውሏል።
ይህ ስምምነት የመጀመርያው ደረጃ ሲሆን በጋዛ በቀጣይ ምን ይሆናል የሚለው ላይ በርካታ ስምምነቶች ይኖራሉ።
በትራምፕ የሰላም ዕቅድ ጋዛን ማን ያስተዳድራል?
በትራምፕ ዕቅድ መሠረት ጋዛ ከፍልስጤማውያን ምሑራን በሚውጣጣ ጊዜያዊ የሽግግር ኮሚቴ ትመራለች።
ኮሚቴው "የሰላም ቦርድ" ተብሎ በሚጠራው በዶናልድ ትራምፕ እና በቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ሊቀመንበር እና መሪነት ቁጥጥር የሚደረግበት ይሆናል።
የትራምፕ ቡድን ይፋ ባደረገው ዕቅድ መሠረት ጋዛ ሰርጥን "የሪፎርም ፕሮግራሙ ከተጠናቀቀ" ለፍልስጤማውያን አስተዳደር የሚያስረክቡ ይሆናል።
ሐማስ ጋዛን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማስተዳደር ውስጥ ድርሻ አይኖረውም።
በዕቅዱ ላይ የሐማስ አባላት በሰላም አብሮ ለመኖር ፈቃደኛ የሚሆኑ ከሆነ ወይም ወደ ሌላ አገር ሄደው ለመኖር ከፈቀዱ ምህረት እንደሚደረግላቸው ተቀምጧል።
በጋዛ ለሚኖሩ ዜጎች ምን ለውጥ ያመጣል?
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ሐሙስ ዕለት እንደተናገሩት ከሆነ የእስራኤል ካቢኔ ስምምነቱን ባፀደቀው በ24 ሰዓታት ውስጥ የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።
በአውሮፓ ምክር ቤት በውጭ ግንኙነት ከፍተኛ የፖሊሲ ፌሎው የሆኑት ሂው ሎቫት በአጭሩ የተኩስ አቄም ስምምነት ማለት የጋዛ ነዋሪዎች "ለሕይወታቸው መስጋት ያቆማሉ ማለት ነው" ይላሉ።
"ሦስት ነገር፤ አይገደሉም፣ አይፈናቀሉም፣ አይራቡም። እነዚህ ሦስት ነጥቦች ለጋዛ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ጠቃሚ መስፈርቶች ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከግል ደህንነታቸው ባሻገር አንዴ ሰዎች ወደ መኖሪያቸው ከተመለሱ በኋላ ሕይወታቸውን መልሰው እንዴት መገንባት እንዳለባቸው ያስባሉ" ሲሉ ሎቫት አክለዋል።
በጋዛ የሚኖሩ ሰዎች በዜናው ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል።
በጋዛ የሚኖረው ጁማ ረመዳን አቡ አሞ ለቢቢሲ አረብኛ "መጀመርያ የማደርገው ከቤታችን ላይ የተከመረውን እና ወንድ እና ሴት አያቴን የተጫናቸውን ፍርስራራሽ ማንሳት ነው።ከዚያ በኋላ ቤቱን ዳግም መስራት እንቀጥላለን። በፈጣሪ ፈቃድ ጋዛን መልሰን እንገነባታለን፤ እናም ከበፊቱ የተሻለች ትሆናለች" ብሏል።
ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ለፈጸመው ጥቃት ምላሽ የሰጠው የእስራኤል ጦር የጋዛን ሕንጻዎች እና መሠረተ ልማቶች አውድሞታል።
ጦርነቱ ከ67,000 በላይ አብዛኞቹ ሰላማዊ ዜጎች የሆኑ ፍልስጤማውያንን የገደለ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 18,000ዎቹ ሕጻናት መሆናቸውን የሐማስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ መረጃ በመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ በሌሎች ዓለማቀፍ አካላት ተዓማኒ ተደርጎ ይቆጠራል።
እርዳታን በተመለከተ ስምምነቱ ምን ይላል?
20 ነጥቦችን የያዘው የትራምፕ ዕቅድ ወደ ጋዛ ሰርጥ ወድያውኑ "የተሟላ እርዳታ" መግባት እንደሚጀምር ያስቀምጣል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በነሐሴ ወር በጋዛ ሰርጥ ድርቅ መከሰቱን አውጇል።
ዕቅዱ በተጨማሪም የሚገባው እርዳታ መጠን "ጥር 19 የሰብዓዊ እርዳታን በሚመለከት በተደረሰው ስምምነት ላይ ከተጠቀሰው ጋር የተጣጣመ" መሆን እንዳለበት ይገልጻል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የእስራኤል ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ በየቀኑ 600 የጭነት መኪና እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ ይገባል።
ሮይተርስ የፍልስጤም ምንጮቹን ጠቅሶ መጀመርያ ላይ በትንሹ 400 መኪኖች መግባት የሚጀመሩ ሲሆን ቀስ በቀስ ቁጥሩ ይጨምራል ብሏል።
ሎቫት ግን የተመሰከረላቸው ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በጋዛ ለሞኖሩ እርዳታ ለማድረስ ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መስራት መቻላቸው መረጋጋጥ አለበት ይላሉ።
የትራምፕ ዕቅድ በመንግጅታቱ ድርጅት ሲመራ የነበረወንእ የምግብ ስርጭት የተካው አወዛጋቢው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን እጣ ፈንታ ምን አንደሚሆን ያለው ነገር የለም።
ሎቫት ለቢቢሲ ሲናገሩ "የመጨረሻው የተኩስ አቁም ከፈረሰ በኋላ በእርዳታ ጣቢያዎች አካባቢ ያለው የደህንነት ሁኑታ ማሽቆልቆሉን ግልጽ መሆን ይኖርብናል" ብለዋል።
ስምምነቱ ፀንቶ ይቆያል?
የዛሬ ሁለት ዓመት በሁለቱም ወገኖች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንስቶ ካለው አንጻር ሲሰላ ይህ ስምምነት እጅጉን መግባባት የታየበት ነው ማለት ይቻላል።
ነገር ግን በኢየሩሳሌም የቢቢሲ ጋዜጠኛ የሆነው ቶም ቤኔት የትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ጥቂት ገጾችን የያዘ የሰላም ማዕቀፍ ነው ይላል።
አክሎም ሁለቱም ወገኖች ሊፈቱት የሚገባቸው ዋና የማያግባቧቸው ነጥቦች አሉ ብሏል።
ከእነዚህም መካከል እስራኤል ሐማስ ትጥቁን መፍታት አለበት የምትለው አንዱ ነው።
ከዚያ ባሻገር ደግሞ እስራኤል ጋዛን ሙሉ በሙሉ ለቅቃ መውጣት አለባት የሚለው እንዲሁም ጋዛን ማን ያስተዳድራል የሚሉት ነጥቦች የማያግባቧቸው ናቸው።
ሎቫት በበኩላቸው የመጀመርያው ዕቅድ ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ አላቸው፤ ነገር ግን ቀጥሎ የሚሆነው ላይ እርግጠኛ ለመሆን ይቸገራሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው እስራኤል መታለፍ የሌለባቸው "ቀይ መስመር" ስትል ያስቀመጠችው ነው።
"ኔታንያሁ በዋይት ሐውስ ከነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ ወድያውኑ እስራኤል ሙሉ በሙሉ ጋዛን ለቅቃ አትወጣም እንዲሁም ፍልስጤም ብሎ አገር አይኖርም ብለዋል" ይላሉ።
"ዕቅዱን ተግባራዊ በማድረግ ውስጥ ሁለት ትልቅ እንቅፋቶች አሉ። ምንያቱም እስራኤል ለዕቅዱ ተገዢ የማትሆን ከሆነ ፍልስጤማውያን ተገዢነታቸውን መጠበቅ ያስቸግራቸዋል። በአስቸኳይ ከሆነው ለመጀመር ከጋዛ ለቅቆ መውጣት" ሲሉ አክለዋል።
ትራምፕ እንዴት እዚህ ውስጥ ሊሳተፉ ቻሉ?
የዚህ የሰላም ጥረት ዋነኛው መለያው የፕሬዚዳንት ትራምፕ የግል ተሳትፎ መኖር ነው።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ስምምነት አንዲመጡ በሐማስ ላይ ብቻ ሳይሆን በእስራኤል ላይም ጨዓና ማድረጋቸውን በኢየሩሳሌም የቢቢሲ ዘጋቢ የሆነው ሁጎ ባቼጋ ይናገራል።
የዚህ ስምምነት ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቅ ፕሬዚዳንት ትራምፐ እስካሁን ድረስ ካከናወኑት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት ሁሉ ትልቁ ነው።
ፕሬዚዳንቱ ለጥረታቸው መስከረም 30 የሚሰጠው የኖቤል ሰላም ሽልማት እንደሚገባቸው በግልጽ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ሎቫት " አሜሪካ ምን ጊዜም በእስራኤል ወይንም በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማሲ ውስጥ ወሳኝ ሚናን ትጫወታለች። አሜሪካ ከማንኛውም አገር በበለጠ እስራኤል ላይ የተሻለ ተጽዕኖ አላት። ትራምፕ ያንን ተጽዕኖ ለመጠቀም በአገር ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነሳ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል።"
ትራምፕ በሚቀጥሉት ቀናት አደራዳሪዎች በስምምነቱ ዙሪያ እየሰሩ ወደ ሚኙበት ግብጽ ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዋይት ሐውስ አርብ ወደ ስፍራው ለመጓዝ ዕቅድ መኖሩን ጠቁሟል።