ትራምፕ እንደምን ጆ ባይደን ያልተሳካላቸውን የጋዛ ስምምነት አሳኩ?

እስራኤል በኳታር የተሰበሰቡትን የሐማስ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ላይ የወሰደችው የአየር ጥቃት የአካባቢው የሠላም ተስፋ የበለጠ ያራቀ መስሎ ነበር።

ጷጉሜ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአሜሪካን አጋር ሉዓላዊነት የጣሰ ነበር። ግጭቱን ወደ ክልል አቀፍ ጦርነት የማስፋፋት አደጋም ፈጥሯል።

ዲፕሎማሲው ያበቃለት መሰለ።

በተቃራኒው ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተቀሩት ታጋቾችን በሙሉ ለመልቀቅ ስምምነት ላይ መደረሱን እንዲያበስሩ ምክንያት ለመሆን በቃ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሁለት ዓመታት ይህንን ለማሳካት ሲጥሩ ቆይተዋል።

ይህ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ የጋዛ አስተዳደር እና የእስራኤል ሙሉ ለሙሉ ከአካባቢው መውጣቷን የሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ድርድሩ ይቀጥላል።

ይህ ስምምነት ከተሳካ የትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ትልቁ ስኬት ሊሆን ይችላል። በተቃራኒው ባይደን እና ዲፕሎማቶቻቸው ያመለጣቸው ዕድል ተብሎ ይታወሳል።

የትራምፕ ልዩ መንገድ እና ከእስራኤል እና ከአረብ አገራት ጋር ያላቸው ግንኙነት ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ይመስላል።

እንደ አብዛኞቹ የዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ሁሉ ከሁለቱም ፕሬዝዳንቶች ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ምክንያቶችም ነበሩ

ባይደን ያልነበራቸው የቀረበ ግንኙነት

በአደባባይ ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሁሌም የሞቀ ግንኙነት አላቸው።

ትራምፕ እስራኤል ከእኛ የተሻለ ወዳጅ የላትም ማለት ይወዳሉ።

ኔታንያሁ ደግሞ እስራኤል "በዋይት ሐውስ ያላት ታላቅ አጋር" ሲሉ ትራምፕን ይገልጿቸዋል። እነዚህ ሞቅ ያሉ ቃላት በድርጊቶችም ተመስክረዋል።

ትራምፕ በመጀመርያ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በእስራኤል የሚገኘውን የአሜሪካን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም አዛወሩ። በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት በዌስት ባንክ ያለውን የእስራኤል ሰፈራ ሕገወጥ ነው የሚለውን የአሜሪካ አቋም ቀየሩ።

እስራኤል በሰኔ ወር በኢራን ላይ የአየር ጥቃትን ጀመረች። ትራምፕ የአሜሪካን ቦምብ ጣይ ጄቶች በማሰማራት የአገሪቱን የኒውክሌር ማበልፀጊያ ተቋሞች እንዲደበደብ አዘዙ።

እነዚህ የአደባባይ ድጋፎች ትራምፕ ከመጋረጃ ጀርባ በእስራኤል ላይ የበለጠ ጫና እንዲያሳድሩ ዕድል ሳይሰጣቸው አልቀረም።

የትራምፕ ተደራዳሪ ስቲቭ ዊትኮፍ በፈረንጆቹ 2024 መጨረሻ ላይ ኔታንያሁ አንዳንድ ታጋቾችን ለማስፈታት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲቀበሉ ጫና አድርገውባቸው ነበር የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

በሐምሌ ወር እስራኤል በሶሪያ ጦር ላይ ጥቃት ስትሰነዝር የክርስቲያኖች ቤተክርስትያን በመጠቃቱ ምክንያት ኔታንያሁ አካሄዳቸውን እንዲቀይሩ ትራምፕ ግፊት ያደርጉ ነበር።

ትራምፕ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ፍላጎት እና ጫና አሳይተዋል ሲሉ የካርኒጌ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ ባልደረባ የሆኑት አሮን ዴቪድ ሚለር ተናግረዋል።

"አንድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ይህን ማድረግ አለባችሁ ካልሆነ ግን ሲሉ ቃል በቃል በመናገር ምሳሌ የሚሆኑ የሉም።"

ባይደን ከኔታንያሁ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሁል ጊዜ ቀለል የሚል ነበር።

የባይደን አስተዳደር ስትራቴጂ እስራኤልን በአደባባይ በማወደስ ውስጥ ለውስጥ ጫና መፍጠርን የሚከተል ነበር።

ባይደን ለእስራኤል ግማሽ ምዕተ-ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ድጋፍ አድርገዋል።

የጋዛው ጦርነት ግን በዲሞክራቶች ዘንድ ከፍተኛ ክፍፍል ፈጥሯል።

ባይደን የሚወስዷቸው ሁሉም እርምጃዎች የፓርቲያቸው የመከፋፈል አደጋ ነበረው። ጠንካራ የሆነው የትራምፕ ሪፐብሊካን መሠረት ግን ለፕሬዝዳንቱ የመንቀሳቀስ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

ከአገር ውስጥ ፖለቲካ ወይም ከግል ግንኙነቶች ባሻገር በባይደን አስተዳደር ዘመን እስራኤል ሠላም ለመፍጠር ዝግጁ አለመሆኗን የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን በመጡ በስምንት ወራት ውስጥ ግን ኢራን ቀዝቅዛለች፣ በሰሜን በኩል ሂዝቦላህ በጣም መፍረክረኩ እና ጋዛ መፈራረሷ ሁሉም ዋና ዋና የስትራቴጂ ዓላማዎች ተሳክተዋል በሚባልበት ደረጃ አድርሶታል።

የንግድ ታሪክ የባህረ ሰላጤውን ድጋፍ ለማረጋገጥ አግዟል

የኳታር ዜጋን የገደለው የእስራኤሉ የዶሃ ሚሳኤል ጥቃት የሐማስ ባለስልጣናትን ነፍስ አልቀጠፈም።

አጋጣሚው ትራምፕ ለኔታንያሁ ቀጭን ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፤ጦርነቱ መቆም ነበረበት።

እስራኤል በጋዛ በአንጻራዊ በነጻነት እንድትንቀሳቀስ ትራምፕ ፈቅደው ነበር። እስራኤል በኢራን ለምታደርገው ዘመቻ የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይል ተጠቅመዋል።

በኳታር መሬት ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ግን ከእነዚህ የተለየ ነው። ጦርነቱን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማብቃት እንዳለበት እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

በርካታ የትራምፕ ባለስልጣናት ለቢቢሲው የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት ከሆነ ይህ አጋጣሚ ፕሬዝዳንቱ የሠላም ስምምነት እንዲደረግ ከፍተኛ ጫና እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከባህረ ሰላጤው አገራት ጋር ያላቸው የቅርብ ግኑኝነት በመረጃ ጭምር የተደገፈ ነው።

ከኳታር እና ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጋር የንግድ ግንኙነት አላቸው።

ሁለቱንም የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን የጀመሩት በሳዑዲ አረቢያ ኦፊሴላዊ ጉብኝቶችን በማከናወን ነው። በሁለተኛው አጋጣሚ ዶሃን እና አቡ ዳቢን ጎብኝተዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ በእስራኤል እና በተለያዩ የሙስሊም መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት መደበኛ ያደረገው የአብርሃም ስምምነት የመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ትልቁ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአረብ አገራቱ ያደረጓቸው ጉብኝቶች አስተሳሰባቸው ለውጦታል ሲሉ የካውንስል ኦን ፎሬን ሪሌሽንስ ባልደረባው ኤድ ሁሴን ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጉዟቸው ወቅት እስራኤልን ባይጎበኙም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታርን ጎብኝተዋል። ጦርነቱን እንዲያቆሙም ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቀርቦላቸዋል።

እስራኤል በዶሃ ላይ የሰነዘረችው ጥቃት አንድ ወር እንኳ ሳይሞላው ኔታንያሁ ይቅርታ ለመጠየቅ ወደ ኳታር ሲደውሉ ትራምፕ በስፍራው ነበሩ።

በተመሳሳይ ቀን የእስራኤሉ መሪ የትራምፕን ባለ 20 ነጥብ የጋዛን የሠላም ዕቅድ ፈረሙ።

ዕቅዱን በአካባቢው ያሉ ቁልፍ የሙስሊም አገራት ድጋፍ ሰጥተውታል።

ትራምፕ ከኔታንያሁ ጋር ያላቸው ግንኙነት እስራኤል ስምምነት ላይ እንድትደርስ ጫና እንዲያሳድሩ ካስቻላቸው፤ ከሙስሊም አገራት መሪዎች ጋር ያላቸው ቅርበት ሐማስ ስምምነቱን እንዲፈጽም እንዲያግዙ ያስችላቸዋል።

"በግልጽ ከተከሰቱት ነገሮች አንዱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከእስራኤላውያን እንዲሁም ደግሞ በተዘዋዋሪ ከሐማስ ጋር መሥራትን ማዳበራቸው ነው" ሲሉ የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል (ሲኤስአይኤስ) ባልደረባ የሆኑት ጆን አልተርማን ተናግረዋል።

"ይህ ለውጥ አምጥቷል። ይህን በጊዜው ለማድረግ መቻሉ እና በታጣቂዎቹ ፍላጎት አለመሸነፍ ብዙ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ሲታገሉበት የነበረው ችግር ነበር። ይህም በአንጻራዊነት በተሳካ ሁኔታ የሠራ ይመስላል።"

ትራምፕ በእስራኤል ከኔታንያሁ የበለጠ ተወዳጅ መሆናቸውንም ተጠቅመውበታል ሲሉም አክለዋል።

እስራኤል ከአንድ ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ከእስራኤል እስር ቤቶች ለመልቀቅ ወስናለች። ከጋዛም በከፊል ለመውጣት ተስማምታለች።

ሐማስ ከአንድ ሺህ 200 በላይ እስራኤላውያንን ለሞት ከዳረገው የመስከረም 26/2016 ዓ.ም.ጥቃት በኋላ የተወሰዱትን በሕይወት ያሉ እና የሞቱትን ቀሪ ታጋቾችን በሙሉ ይለቃል።

ለጋዛ ውድመት እና ከ67 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት ማብቂያውን አሁን መገመት ይቻላል።

አውሮፓውያን የራሳቸውን ተጽዕኖ ያሳድራሉ

እስራኤል በጋዛ ባደረገችው የሚደርስባት ዓለም አቀፍ ውግዘት መጨመሩ የትራምፕን አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

በፍልስጤማውያን ላይ ከሚደርሰው ውድመት እና ሰብዓዊ ውድመት አንጻር በመሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች ታይተው የማይታወቁ ናቸው።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የኔታንያሁ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተገለለ መጥቷል።

እስራኤል ለፍልስጤማውያን የሚሰጠውን የምግብ አቅርቦት ስትቆጣጠር እና በጋዛ ከተማ ላይ ያቀደችውን ጥቃት ስታስታውቅ፣ በፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የተመሩ በርካታ የአውሮፓ አገራት ዋሽንግተን ለእስራኤል ካላት ድጋፍ ጋር አብረው መጓዝ እንደማይችሉ ወሰኑ።

የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት የወደፊት ዕጣን በተመለከተ በአሜሪካውያን እና በአውሮፓ አጋሮች መካከል የነበረውን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኝኑት መለያየት ጀመረ።

ፈረንሳይን ለፍልስጤም መንግሥት ዕውቅና እሰጣለሁ ስትል የትራምፕ አስተዳደር ወቀሳ አቀረበ።

እውቅናውን እንደምትሰጥ ዩናይትድ ኪንግደምም ገለጸች። የሁለት-ግዛት መፍትሄን ሃሳብ ለማቆየት እየሞከሩ ሲሆን በሁለቱም በኩል ያሉትን ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦችን በማግለል የእስራኤል እና የፍልስጤም የወደፊት የዲፕሎማሲያዊ መንገድን ለማደስ እየሞከሩ ነበር።

ማክሮን ለሠላም ዕቅዱ ሳዑዲዎችን ማሳመን ችለው ነበር።

ትራምፕ በበኩላቸው የጋዛን የረዥም ጊዜ የወደፊት እጣ ፈንታ በተመለከተ ከእስራኤል ብሔርተኞች እና ከአውሮፓ እና አረብ ጥምረት ጋር ፊት ለፊት ተፋጠው ነበር። በመጨረሻም የባህረ ሰላጤው ወዳጆቻቸው መረጡ።

በፈረንሣይ-ሳዑዲ የሠላም ዕቅድ መሠረት የአረብ አገራት ሐማስ ያደረሰውን ጥቃት በማውገዝ ቡድኑ በጋዛ ላይ ያለውን አገዛዝ እንዲያበቃ እና መሳሪያውን በገለልተኛ መንግሥት ስር ለፍልስጤም አስተዳደር እንዲያስረክብ ጠይቋል።

ይህ ለአረቦች እና ለአውሮፓውያን ዲፕሎማሲያዊ ድል ነበር።

የትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሠላም ዕቅድ ከፈረንሳይ እና ከሳዑዲ እቅድ ቁልፍ የሆኑ ሃሳቦችን ወስዷል። ይህም ግልጽ ያልሆነ እና ቅድመ ሁኔታ ያለው ቢሆንም የፍልስጤም "መንግሥትነትን" መጠቅሰን የጨመረ ነው።

ትራምፕ ቱርክን፣ ኳታርን እና ግብጽን በሐማስ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኔታንያሁ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ደግሞ በግላቸው ጫና ፈጥረዋል።

ትራምፕን እምቢ ለማለት ማንም ወገን አይሞክርም።

የትራምፕ ልዩ አካሄድ አለመግባባቱን ፈታው

የትራምፕ ያልተለመደ አካሄድ አሁንም የማስደንገጥ አቅም አለው። በከባድ ነገር ይጀምር እና ወደ ተለመደው አካሄድ ያድጋል።

በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው "ትንሹ የሮኬት ባለቤት" የሚለው ዘለፋ እና "እሳት እና ቁጣ" የሚሉት ማስጠንቀቂያዎች አሜሪካን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወደ ጦርነት አፋፍ እየወሰዷት መስሎ ነበር። ይልቁንም በቀጥታ ንግግር ወደማድረግ ገቡ።

ትራምፕ ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት ፍልስጤማውያን ከጋዛ መልቀቅ ይጠበቅባቸዋል በሚል ሃሳብ ነበር።

ፍልስጤማውያን ሲለቁ ጋዛን ወደ ዓለም አቀፍ ሪዞርትነት ለመቀየር በማለም እንደሆነ ገልጸዋል።

የሙስሊም መሪዎች ተናደዱ። የመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማቶች ደነገጡ።

የትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሠላም እቅድ ባይደን ሊፈጽሙት ከነበረው እና የአሜሪካ አጋሮች ለረዥም ጊዜ ካጸደቁት የተለየ አይደለም።

ትራምፕ ወደ ተለመደው ውጤት ለመድረስ በጣም ያልተለመደ መንገድን ተጠቅመዋል።

ውጥንቅጡ የወጣ ነበር። በዩኒቨርሲቲዎች ዲፕሎማሲን የሚያስተምሩበት መንገድ ላይሆን ይችላል። ቢያንስ ለአሁኑ ውጤታማነቱ ተረጋግጧል።

የኖቤል ኮሚቴ የዘንድሮውን የሠላም ሽልማት አሸናፊ አሳውቋል።

ትራምፕ አሸናፊ ይሆናሉ ተብሎ የማይታሰብ ቢሆንም፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከነበረው አንጻር ግን ተስፋቸው የለመለመ መስሎ ነበር።

ቬኔዙዌላዊቷ ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።