ሳዑዲ አረቢያን ስለሚያሽከረክሩት ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ያልተሰሙ እውነታዎች

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2015 መጀመሪያ ላይ የዚያን ጊዜው የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ የ90 ዓመቱ አብዱላህ በጠና ታምመው በሆስፒታል አልጋ ላይ እያጣጣሩ ነበር።

የንጉሡን በጠና መታመም ተከትሎ ታናሽ ወንድማቸው ሰልማን ንግሥናውን ለመረከብ ሲሰናዱ፤ የሰልማን ተመራጭ ልጅ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ደግሞ ለሥልጣን እየተዘጋጁ ነበር።

ስማቸው በአጭሩ ሲጠራ ኤምቢኤስ የሚባሉት ሞሐመድ ቢን ሰልማን አባታቸው ንጉሥ እርሳቸው ደግሞ ልዑል አልጋ ወራሽ የሆኑት ገና በ29 ዓመታቸው ነው።

በወቅቱ ኤምቢኤስ ዕድሜያቸው ለጋ ቢሆንም ለአገራቸው ሳዑዲ ትልቅ ሕልም ሰንቀዋል። ይሁን እንጂ ኤምቢኤስ በሳዑዲ ንጉሣውያን ቤተሰብ ውስጥ እርሳቸው ሥልጣን እንዳይዙ የሚገዳደር ኃይል እንደሚኖር ያውቁ ነበር።

ንጉሥ አብዱላህ በሞቱበት የአውሮፓውያኑ 2015 የመጀመሪያ ወር ላይ በአንድ ውድቅት ሌሊት ኤምቢኤስ የአገሪቱን የደኅንነት ሹም በቤተ-መንግሥታቸው ድረስ አስጠሩ።

ይህ የደኅንነት ኃላፊ ሳዓድ ቢን ካህሊድ አል ጃብሪ ነበሩ። አል ጃብሪ በር ላይ ሞባይል ስልካቸውን አስቀምጠው እንዲገቡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው።

ቢን ሰልማንም በተመሳሳይ ስልካቸውን ከውጭ ትተው በአንድ ክፍል ውስጥ ከደኅንነት ሹሙ ጋር ብቻቸው ተገናኙ።

ኤምቢኤስ በቤተ-መንግሥቱ ያሉ ሰላዮችን እጅግ ከመጠርጠራቸው የተነሳ በክፍሉ የነበረውን መደበኛ የስልክ መስመር ሶኬትን በመንቀል አቋርጠውት ነበር።

በዚያ ውድቅት ሌሊት ኤምቢኤስ ሳዑዲ ለዘመናት ካንቀላፋችበት ነቅታ በዓለም መድረክ የሚገባትን ቦታ እንድትይዝ ምን መሆን እንዳለበት ሲያወሩ ነበር ይላሉ የወቅቱ የደኅንነት ሹም አል ጃብሪ።

በዓለም ደረጃ ትርፋማ የሆነውን አርማኮ የተባለ የሳዑዲ መንግሥት የነዳጅ ኩባንያ ድርሻን በመሸጥ፣ በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነው የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት የማነቃቃት ዕቅዳቸውንም ነገሯቸው።

ኤምቢኤስ በዓለም ዙሪያ የሜትር ታክሲ አገልግሎት በሚሰጠው ኡበር እና በአሜሪካው ሲሊከን ቫሊ የአዳዲስ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያላቸውን ፍላጎት፣ እንዲሁም ለሳዑዲ ሴቶች ነጻነትን በመስጠት ለ6 ሚሊዮን ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠርን የተመለከቱ ዕቅዶችን ለደኅንነት ሹሙ ገለጹላቸው።

በኤምቢኤስ የሚጨበጥ የማይመስል ህልም የተደነቁት አል ጃብሪ፤ በአጭር የሥልጠን ዘመኑ በታሪክ ትልቁን ግዛተ መንግሥት ስለገነባው፤ “ስለታላቁ አሌክሳንደር ሰምተው ያውቃሉ?” ሲሉ ኤምቢኤስን መጠየቃቸውን ያስታውሳሉ።

ኤምቢኤስ ከደኅንነት ሹሙ ጋር ለማድረግ አቅደውት የነበረው የግማሽ ሰዓት ውይይት ለሦስት ሰዓታት ዘለቀ።

አል ጃብሪ ክፍሉን ለቅቀው ሲወጡ ያሉበትን ሳያሳውቁ በመጥፋታቸው ስጋት በገባቸው ሰዎች የስልክ ጥሪ ሞባይላቸው ተጨናንቆ አገኙት።

ለዚህ ዘገባ የልዑል አልጋ ወራሹ ወዳጆች እና ነቃፊዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። የምዕራባውያን አገራት ዲፕሎማቶች እና ሰላዮች እንዲሁ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ለሚነሱበት ትችቶች ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ሳድ አል-ጃብሪ በሳዑዲ ደኅንነት ውስጥ በነበራቸው ትልቅ ስፍራ ለአሜሪካው ሲአይኤ እና ለዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ኤምአይ6 ኃላፊዎች የቅርብ ወዳጅ ነበሩ።

ዛሬ አል-ጃብሪ ከኤምቢኤስ ጋር ሆድ እና ጀርባ ናቸው። እአአ 2017 ላይ ከሳዑዲ ወጥተው በስደት በካናዳ ይኖራሉ። የቀድሞ የደኅንነት ሹም ኤምቢኤስ ሊያስገድሉኝ ይፈልጋሉ ሲሉ መገናኛ ብዙኃን ላይ ወጥተው አቤቱታ አቅርበዋል።

ምንም እንኳ ሳዑዲ አል-ጃብሪን ተፈላጊነት የሌለው የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣን ናቸው ብላ ብታጣጥላቸውም፤ ግለሰቡ በስደት ያሉ ስለ አገሪቱ ብዙ ምሥጢር የሚያውቁ ስለመሆናቸው ለቢቢሲ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ይመሰክራል።

አል-ጃብሪ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ አገሪቱን እንዴት እንደሚመሩ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ምንም እንኳ በአገሪቱ ትልቁ ሥልጣን የንጉሡ ቢሆንም አገሪቱን እየዘወሩ ያሉት አሁን ላይ 38 ዓመት የሆናቸው ጎልማሳው ኤምቢኤስ ናቸው።

ቢን ሰልማን የሳዑዲ አረቢያን ምጣኔ ሃብት ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ይተቻሉ።

የመብት ተሟጋቾች በኤምቢኤስ አስተዳዳር ስር በነጻነት የመናገር መብት ተሸርሽሯል፣ በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር እና የሴቶች መብት ተከራካሪዎች እስር ጨምሯል በማለት ይወቀሳሉ።

ያልተጠበቁተ ቢን ሰልማን

የመጀመሪያው የሳዑዲ አረቢያ ንጉሥ አብዱላህ (የኤምቢኤስ አያት) 42 ወንድ ልጆችን ወልደዋል።

የሳዑዲ ንግሥና ለወንድ ልጆች ሲተላለፍ መጥቷል። እአአ 2011 እና 2012 ላይ ከንጉሥ አብዱላህ ልጆች መካከል ሁለቱ ድንገት ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የኤምቢኤስ አባት ሰልማን ለሥልጣን ተመቻቹ።

የሳዑዲ ጉዳይን የራሳቸው ጉዳይ አድርገው የሚከታተሉ የምዕራባውያን አገራት ሰላዮች በዚህ ወቅት ቀጣዩ የሳዑዲ ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ማን ሊሆን ይችላል የሚለውን ይተነብዩ ነበር።

በዚህ ጊዜ ታዲያ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ልጅ በመሆናቸው ጨርሶ በዝርዝር ውስጥ አልነበሩም ብቻ ሳይሆን ጨርሶ አይታወቁም ነበር ማለት ይቻላል።

እአአ 2014 የዩኬ መንግሥት የደኅንነት ተቋም የሆነው የኤምአይ6 ኃላፊ የነበሩት ሰር ጆን ሳዌርስ “በአንጻራዊነት አስተዳደጉ ከሕዝብ ተሸፍኖ ነው። ሥልጣን እንዲይዝ ተደርጎ አይደለም ያደገው” ይላሉ።

ኤምቢኤስ ያደጉት በቤተ-መንግሥት ውስጥ ነው። በቤተ-መንግሥት ያደገ ልጅ ቢያጠፋም አይቀጣም። ተቀማጥሎ ነው የሚያድገው። ለዚያም ይሆናል ኤምቢኤስ የሚያስተላልፉት ውሳኔ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ ቀድመው የማያሰላስሉት።

ኤምቢኤስ በመጥፎ ባሕሪያቸው በሪያድ ስማቸው ገናና መሆን የጀመረው ገና በጉርምስና ዕድሜያቸው ነበር።

በወቅቱ “አቡ ራሳሳ” ወይም “የጥይት አባት” የሚል ቅጽል ስም ነበራቸው። ይህን ስም ያገኙት በንብረት ይገባኛል ጥያቄያቸውን ውድቅ ወዳረጉባቸው የፍርድ ቤት ዳኛ በፖስታ ጥይት ከላኩ በኋላ ነው።

“ጭካኔ የተሞላበት የራሱ የሆነ መርህ አለው። ማንም ሰው እንዲጋፈጠው አይፈቅድም። ይህም ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የሳዑዲ መሪ ላይ ያልታየ ለውጥ አምጥቷል” ይላሉ የቀድሞ የኤምአይ6 ኃላፊ።

እኚህ የቀድሞ የኤምአይ6 ኃላፊ እንደሚሉት ኤምቢኤስ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሳዑዲ የእስላማዊ ጂሃዲሰቶች መፍለቂያ ለሆኑ፣ ከአገር ውጪ ለሚገኙ መስጂዶች እና የእስልምና ትምህርት ቤቶች ታደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ማስቆማቸው ለምዕራባውያኑ መልካም እርምጃ ነበር ይላሉ።

ንጉሥ ሰልማን ለረዥም ዓመታት በመርሳት በሽታ ሲሰቃዩ የቆዩ ሲሆን፣ ለድጋፍ ፊታቸውን ያዞሩ የነበሩትም ወደ ኤምቢኤስ ነበር።

ንጉሥ ሰልማን ቁልፍ በሚባሉ ስብሰባዎች ላይ ልጃቸውን ኤምቢኤስን ይዘው ነበር የሚገኙት።

በስብሰባዎች ላይ ብዙ ጊዜ ኤምቢኤስ በአይፓዳቸው ላይ ማስታወሻዎችን ይጽፉ እና ማስታወሻዎቹን ወደ አባታቸው አይፓድ ያሰተላልፉታል።

“ንጉሡ የሚናገሩትን ነገር የሚጽፍላቸው ኤምቢኤስ ስለመሆኑ አስብ ነበር” ይላሉ የወቅቱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት ሎርድ ኪም ዳሮክ።

ኤምቢኤስ አባቱ ንጉሥ እስኪሆኑ ድረስ እጅግ ከመቸኮላቸው የተነሳ በወቅቱ አጎቱ የነበሩት ንጉሥ አብዱላህን ከሩሲያ በመጣ የቀለበት በመርዝ ስለመግደል ሰዎችን እስከማማከር ደርሰው ነበር።

“ይህ መረጃ በሃሳብ ደረጃ የተጋነነ ይሁን በትክክል የተወጠነ እርግጠኛ ባልሆንም እኛ ግን ሁኔታውን በአንክሮ ስንከታተል ነበር” የሚሉት ደግሞ የቀድሞው የሳዑዲ የደኅንነት ሹሙ አል ጃብሪ ናቸው።

አል ጃብሪ እንደሚሉት ከሆነ ኤምቢኤስ ይህን ሃሳቡን ሲያስረዳ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል መመልከታቸውን ይናገራሉ።

“ለረዥም ጊዜ ንጉሡን እንዳይጨብጥ እና በንጉሡ እልፍኝ እንዳይገኝ ተከልክሎ ነበር” ይላሉ የቀድሞ የደኅንነት ሹም።

እአአ 2015 ላይ ንጉሥ አብዱላህ በሕመም ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ የኤምቢኤስ አባላት ሰልማን ንጉሥ ሆኑ። ኤምቢኤስም የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።

ታዲያ ኤምቢኤስ ሥልጣን ላይ እንደወጡ አቅማቸውን ለማሳየት ጊዜ አልፈጁም። ጦራቸውን ወደ የመን አዘመቱ።

የየመን ጦርነት

ኤምቢኤስ ሥልጣን በተቆናጠጡ ገና በሁለተኛ ወራቸው የሁቲ አማጺያንን ለመውጋት የአካባቢው አገራትን አስተባብረው ጦርነት ጀመሩ።

ኤምቢኤስ በየመን የኢራን አጋር ናቸው የሚሏቸው የሁቲ አማጺያን አብዛኛውን የየመን ምዕራባዊ አካባቢዎች ተቆጣጥረው ይዘው ነበር።

ልዑል አልጋ ወራሹ የቀሰቀሱት ጦርነት በየመን ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።

ይህ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በሳዑዲ የዩኬ አምባሳደር የነበሩት ሰር ጆን ጄንኪንስ፤ ጦርነቱን መጀመር “ብልህነት የተሞላበት ውሳኔ ነው ብዬ አላስብም” ይላሉ።

“የአገሪቱ ሠራዊት ጦርነቱ እንዲጀምሩ የተሰጣቸው ጊዜ 12 ሰዓታት ብቻ ነበር። ይህ ተሰምቶ የሚያወቅ አይደለም” ይላሉ የቀድሞ አምባሳደር።

እውነት ነው ይህ ጦርነት ኤምቢኤስን በሳዑዲ ጀግና አድርጓቸው ነበር። ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት የየመኑ ጦርነት የኤምቢኤስ የመጀመሪያው ስህተት ተደርጎ ይወሰዳል።

በሳዑዲ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሚታወቁት ዘገምተኛ የሆነ ውሳኔዎችን በመስጠት ነው። ኤምቢኤስ ግን ቅጽበታዊ በሆነ ሁኔታ አጋር ለሚባሉ አገራት እንኳ ሳያሳውቁ በሚሰጡት ውሳኔ መለየት ጀመሩ።

አል ጃብሪ፤ ልዑል አልጋ ወራሹ የየመን ጦርነትን ለመጀመር ሲሰናዱ ከአሜሪካ የሚያገኙት እርዳታ የአየር ጥቃት ድጋፍ ብቻ ስለመሆኑ በወቅቱ የፕሬዝዳንት ኦባማ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በሆኑ ኮንዶሊዛ ራይስ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር።

“የምድር ላይ ዘመቻ ለማካሄድ ብሔራዊ የክተት ጥሪ መደረጉ አስደንቆን ነበር። የአባቱን ፊርማ አስመስሎ በመፈረም ነው ይህን የክተት ጥሪ ያወጀው” ይላሉ አል ጃብሪ።

የወቅቱ የኤምአይ6 ኃላፊ ሰር ጆን ምንም እንኳ ኤምቢኤስ የአባቱን ፊርማ አስመስሎ ክተት ስለማወጁ እርግጠኛ ባልሆንም ንጉሡ ግን የየመን ጦርነትን አይደግፉም ይላሉ።

በራሳቸው መንገድ የሚጓዙት

ኤምቢኤስ በአውሮፓውያኑ 2017 የገዙት በጣም ታዋቂ ሥዕል ስለሰውየው ብዙ የሚናገር ነው።

ምንም እንኳ የሚያስተዳድሩት ማኅበረሰብ ወግ አጥባቂ እና ሃይማኖታዊ ቢሆንም፣ እሳቸው ወጣ ያለ ነገር ከማድረግ እንደማይቆጠቡ የሚያሳይም ነው።

ይህ ብቻ አይደለም አልጋ ወራሹ ጉልበታቸውን ለምዕራባውያኑ ለማሳየት ወደኋላ እንደማይሉም የተስተዋለበት እርምጃም ወስደዋል።

በ2017 አንድ የኤምቢኤስ ወኪል ናቸው የተባሉ ግለሰብ ንጉሥ ሳልቫቶር ሙንዲ የተባለውን ሥዕልን በ450 ሚሊዮን ዶላር ሸምተዋል። ሥዕሉ በዓለማችን እጅግ ውዱ የጥበብ ሥራ ነው።

በሌዎናርዶ ዳ ቪንቺ ነው የተሳለው የሚባልለት ይህንን ሥዕል ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ገነት እና ምድር ፈጣሪ እንዲሁም እንደ ዓለም መድኃኒት የሚያቀርብ ነው።

ሥዕሉ ለጨረታ ወጥቶ ከተገዛ በኋላ ለሰባት ዓመታት የት እንዳለ አይታወቅም ነበር።

አንዳንድ ዘገባዎች ሥዕሉ በልዑል አልጋ ወራሹ ቤተ-መንግሥት አሊያም በግል መርከባቸው ውስጥ ይገኛል ይላሉ።

ነገር ግን በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እንዲሁም የአልጋ ወራሹ ጓደኛ የሆኑት በርናርድ ሀይከል እንደሚሉት ሥዕሉ ጄኔቫ የሚገኝ አንድ መጋዘን ውስጥ ነው የሚገኘው፤ ልዑሉ ወደፊት ሳዑዲ ውስጥ በሚገነባ ሙዚየም ውስጥ ሊሰቅሉት ይሻሉ።

ኤምቢኤስ “ሪያድ ውስጥ በጣም ትልቅ ሙዚየም መገንባት እፈልጋለሁ” ብለዋል ሲሉ ሀይከል ይናገራሉ። “ልክ እንደ ሞናሊዛ ያለ የሰዎችን ቀልብ የሚገዛ ነገር እፈልጋለሁም” ብለዋል ሲሉ ያክላሉ።

ልዑሉ ለስፖርት ያላቸው አተያይም ምን ያክል የተለጠጠ ዕቅድ እንዳላቸው እና ከተለመደው አሠራር ለመውጣት እንደማይፈሩ የሚያሳይ ነው።

ሳዑዲ አረቢያ ዓለም አቀፍ በሚባሉ ስፖርቶች ላይ ብሯን እያፈሰሰች ነው። ሳዑዲ በአውሮፓውያኑ 2034 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ብቻዋን ለማሰናዳት ሐሳብ አላት። እንደ ቴኒስ እና ጎልፍ ያሉ ስፖርቶች በሜዳዋ እንዲካሄዱ ሚሊዮን ዶላሮችን እያፈሰሰች ትገኛለች።

አንዳንዶች ይህ “ስፖርት ዋሺንግ” አሊያም ሳዑዲ በስፖርቱ አማካይነት ስሟን ለማደስ የምታደርገው ጥረት ነው ሲሉ ይተቻሉ።

ነገር ግን የሳዑዲው መሪ አውሮፓውያኑ ስለሳቸው ያላቸው አስተሳሰብ የሚደንቃቸው አይደሉም፤ ሳዑዲንም ሆነ ራሳቸውን ታላቅ ለማድረግ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ከማድረግ የሚመለሱ አይመስሉም።

“ኤምቢኤስ የሚፈልጉት እንደ አንድ መሪ የራሳቸውን ጉልበት ማሳየት ነው” የዩናየትድ ኪንግደም የስለላ ተቋም የሆነው ኤምአይ6 የቀድሞው ኃላፊ ሰር ጆን ሳወርስ።

ልዑሉን በአካል አግኝተው የሚያውቁት ሳወርስ እንደሚሉት “ልዑሉ ይህን ለማድረግ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ የአገራቸውን ጉልበት ማጠናከር ነው። ለዚህ ነው ይህን ሁሉ የሚያደርጉት።”

አል-ጃብሪ ለ40 ዓመታት በሳዑዲ የነበራቸው ሥልጣን የኤምቢኤስን የለውጥ ሰይፍ መቋቋም አልቻለም።

የቀድሞው ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ናይፍ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት አል-ጃብሪ ኤምቢኤስ ሥልጣን መቆጣጠር ሲጀምሩ ነው ሳዑዲ አረቢያን ጥለው የሸሹት። አል-ጃብሪ የሸሹት ከውጭ የስለላ ድርጅቶች የደረሳቸው መልዕክት አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ የሚጠቁም መሆኑን ተከትሎ ነው።

ነገር ግን አል-ጃብሪ እንደሚሉት አንድ ቀን ድንገት ሳያስቡት ኤምቢኤስ የጽሑፍ መልዕክት ልከው ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ እንደጠየቋቸው ይናገራሉ።

“ነገሩ ወጥመድ ነበር - እኔ ደግሞ አልቀበልም አልኩኝ” የሚሉት አል ጃብሪ ቢመለሱ ዕጣ ፈንታቸው ታስሮ መሰቃየት፣ እንደሆነ ይናገራሉ።

የአል-ጃብሪ ታዳጊ ልጆች የሆኑት ኦማር እና ሳራህ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ለማምለጥ በመሞከር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው እስር ተፈርዶባቸዋል። ታዳጊዎቹ ድርጊቱን አልፈጸምንም ይላሉ። የተባበሩት መንግሥታት አካል የሆነው የሕገ ወጥ እስሮችን የሚመለከተው ክፍል ሁለቱ ወጣቶች እንዲለቀቁ ጠይቋል።

“ሊገድለኝ ነበር ያሰበው” ይላሉ አል-ጃብሪ። “ካልሞትኩኝ በቀር ሰላም አያገኝም። ስለዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም።”

የሳዑዲ ባለሥልጣናት ዓለም አቀፉ ፖሊስ ኢንተርፖል ጃብሪን ከካናዳ ይዞ እንዲያመጣላቸው ቢጠይቁም አልተሳካላቸውም። ሰውዬው የአገር ውስጥ ሚኒስቴር አባል ሳሉ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሙስና ሠርተዋል ሲሉ ነው የሚከሷቸው።

ነገር ግን ሰውዬው የሜጀር ጄኔራል ማዕረግ ያላቸው ሲሆን፣ የአል-ቃኢዳን የሽብር ጥቃት በመከላከል ብዙ ሠርተዋል ተብለው በአሜሪካው ሲአይኤ እና በዩኬው ኤምአይ6 ይመሰገናሉ።

የኻሾግጂ ግድያ

በአውሮፓውያኑ 2018 ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የተፈፀመው የጀማል ኻሾግጂ ግድያ ለኤምቢኤስ መከራከርን አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጓል።

ለኻሾግጂ ግድያ የዲፕሎማት ፓስፖርት ተሰጥቷቸው ከተጓዙ 15 ገዳዮች መካከል የኤምቢኤስ የግል ጥበቃዎች ይገኙበታል። የኻሾግጂ አስከሬን እስካሁን ያልተገኘ ሲሆን፣ በመጋዝ ተቆራርጦ እንደተጣለ ይገመታል።

ከግድያው በኋላ ከኤምቢኤስ ጋር በዋትስአፕ ያወሩት ሀይከል “እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል? ስል ጠይቄው ነበር” ይላሉ። “ሲመስለኝ እሱም በጣም ደንግጦ ነበር። ጉዳዩ ይህን ያህል አነጋጋሪ ይሆናል ብሎ የጠበቀ አይመስለኝም።”

ዴኒስ ሮስ ከግድያው በኋላ ነው ኤምቢኤስን ያገኙት። “ግድያውን እሳቸው እንዳልፈፀሙት ነው የነገሩኝ፤ ይልቁንስ ሳይታሰብ የተፈፀመ ግድያ ነው” ይላሉ። “ላምነው እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ይሄ ግድያ እንዲፈጸም ትዕዛዝ ይሰጣሉ ብዬ አልገምትም።”

ኤምቢኤስ እስከ ዛሬ ድረስ ስለግድያው ምንም እውቀት እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት። ነገር ግን በ2019 በሰጡት ቃል ግድያው የተፈፀመው በእሳቸው አገዛዝ ዘመን ስለሆነ “ኃላፊነት እወስዳለሁ” ማለታቸው አይዘነጋም።

በ2021 ይፋ የሆነ የአሜሪካ የደኅንነት ዘገባ እንደሚጠቁመው ኤምቢኤስ በጀማል ኻሾግጂ ግድያ እጃቸው እንዳለበት ነው።

ፕሮፌሰር ሀይከል ልዑል አልጋ ወራሹ “መከራ አስተምሯቸውም ቢሆን ከስህተታቸው ተምረዋል” ይላሉ። ግድያው እሳቸውን እና አገራቸውን እንደ ጨካኝ አድርጎ የሚያስወስድ መሆኑ ያስቆጫቸዋል ሲሉ የሚናገሩት ምሑሩ እንደ ኻሾግጂ ዓይነት ግድያ ድጋሚ አናይም ይላሉ።

ሰር ጆን ሳወርስም እንዲሁ የጋዜጠኛው ግድያ ሁኔታዎችን የቀየረ ነው ባይ ናቸው። “እኔ እንደሚመስለኝ ከስህተቱ ተምሯል። ነገር ግን ማንነቱን የሚቀይር አይመስለኝም።”

የልዑል አልጋ ወራሹ አባት ንጉሥ ሰልማን አሁን 88 ዓመታቸው ነው። ንጉሥ ሰልማን ሲሞቱ ኤምቢኤስ ሳዑዲ አረቢያን ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት ሊመሩ ይችላሉ።

ቢሆንም በቅርቡ ልዑሉ ሲናገሩ እንደተሰሙት በሳዑዲ እና በእስራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት ለማረጋጋት በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት ግድያ ሊፈፀምባቸው እንደሚችል ስጋት አላቸው።

“እኔ እንደሚመስለኝ በጣም ብዙ ሰዎች ሊገድሉት ይፈልጋሉ” ይላሉ ፕሮፌሰር ሀይከል። “ይህንን ደግሞ እሱም ያውቃል።”

እንደ ኤምቢኤስ ያሉ ሰዎችን ከአደጋ የሚጠብቃቸው ነገር ሁሌም ንቁ ሆነው እራሳቸውን መጠበቃቸው ነው። ልዑል አልጋ-ወራሹ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አል-ጃብሪ ይህን አስተውለዋል። ቤተ-መንግሥት ጠርተው ሲያናግሯቸው የቴሌፎኑን ገመድ ከግድግዳው አላቀው ነበር።

ኤምቢኤስ አሁንም አገራቸውን ለማዘመን እየጣሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ይህን ለማድረግ የሚጠቀሙት መንገድ ከእሳቸው ቀድሞ ከነበሩ መሪዎች የተለየ ነው።

እንዲያም ሆኖ ግን ምንም ምህረት የሌላቸው፤ በአቅራቢያቸው ያሉ ሰዎች አንዲት ቅንጣት ስህተት እንኳ መፈፀም የማይፈቅዳላቸው እንደሆኑም ይነገርላቸዋል።