የትራምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም ኃላፊን አባረረ

ዋይት ሀውስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም ኃላፊና የበይነ መረብ ደኅንነት ኃላፊን አባረረ።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው በአሜሪካ ከፍተኛ የደኅንነት ተቋሞች እየተባረሩ ነው።

ጀነራል ቲሞቲ ሀው ለምን እንደተባረሩ ግልጽ ባይሆንም ትራምፕ ከደጋፊያቸው ሎራ ሉመር ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው መባረራቸው የተገለጸው።

ዴሞክራቶች የደኅንነት ኃላፊዎቹ መባረር "በጣም አስጊ ነው" ያሉ ሲሆን በብሔራዊ ደኅንነት ክፍተት እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

የትራምፕ ደጋፊ የሆነችው አክቲቪስት ሎራ፤ ትራምፕ የተወሰኑ ሠራተኞችን እንዲያባርሩ ጠይቃለች።

ለትራምፕ ድጋፍ አላሳዩም የተባሉ አመራሮች እንዲባረሩ ጠይቃ ውሳኔው መተላለፉ ተገልጿል።

በኤክስ ገጿ ጄነራል ሀው እና ምክትላቸው ዌንዲ ኖብል "ለፕሬዝደንት ትራምፕ ታማኝ ስላልሆኑ ነው የተባረሩት" ስትል ጽፋለች።

ትራምፕ ለሳቸው ታማኝ ያልሆኑ ሰዎችን እንደሚያባርሩ ሲዝቱ ነበር።

"ሰዎች ሁሌም እናባርራለን። የማንወዳቸውን፣ ሊጠቀሙብን የሚሞክሩትንና ወገንተኝነታቸው ለሌሎች የሆነውን እናባርራለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ብሔራዊ ደኅንት ተቋም ከቢቢሲ ምላሽ ተጠይቆ ወደ መከላከያ ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል መርቷል።

ከዚህ ቀደም ግን በግለሰቦች ጉዳይ አስተያየት እንደማይሰጥ ገልጿል።

ዴሞክራቱ ቲም ሀይምስና ሌሎችም ዴሞክራቶች ጄነራል ሀው መባረራቸውን ለሲቢኤስ አረጋግጠዋል።

ሀይምስ "በጣም አስደንጋጭ" ሲሉ ውሳኔውን ገልጸዋል።

"ታማኝና ቀጥተኛ መሪ መሆኑን አውቃለሁ። ሕግ ያከብራል፤ ለብሔራዊ ደኅንነት ቅድሚያ ይሰጣል። በዚህ አስተዳደር ግን እንዲህ ያለ ሰው መሆን ለመባረር ያበቃል" ሲሉም አክለዋል።

የስለላ ኃላፊ ብራየን ዋልሽ፣ የቴክኖሎጂና ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ዴቪድ ፌት እና ሌሎችም የተቋሙ አመራሮች ተባርረዋል።

ብሔራዊ የደኅንነት ተቋሙ በሲግናል ቡድን ውስጥ ጋዜጠኛን በስህተት ከማካተቱ ጋር በተያያዘ ስሙ ሲነሳ ነበር።

የሲግናል ቡድኑ በየመን የሁቲ አማጺያን ላይ ስለሚሰነዘር ጥቃት መረጃ የተለዋወጡበት ነበር።

ጄነራል ሀው በሲግናል ቡድኑ ውስጥ ባይኖሩበትም በኮንግረስ ፊት ቀርበው ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የተባሉትን የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልዝ አሁንም ድረስ ትራምፕ እየደገፉ ነው።

የአትላንቲክ መጽሔት ጋዜጠኛውን ወደ ሲግናል ቡድኑ የቀላቀሉት ዋልዝ መሆናቸው ተገልጿል።

ምንጮች እንደሚሉት፣ ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ ለትራምፕ አስተዳደር ታማኝ አይደሉም የተባሉ ባለሥልጣኖች ላይ እርምጃ እየተወሰደነ ነው።

የመከላከያ ጸሐፊው ፒት ሄግስ መረጃውን በሲግናል ከመልቀቅ ጋር በተያያዘ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።

ትራምፕ ከደጋፊያቸው ሎራ ጋር ስላደረጉት ውይይት ሎራ በግልጽ ባትናገርም ትራምፕ "አገር ወዳድ" ሲሉ ጠርተዋት፤ ከሷ አንዳንዴ ምክር እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።