ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ወደ ኤል ሳልቫዶር አባራ የመለሰችውን ግለሰብ በድጋሚ ለማባረር ያቀረበችው ዕቅድ በጊዜያዊነት ታገደ
አሜሪካ በስህተት ወደ ኤል ሳልቫዶር አባራው የነበረውና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደገና የመለሰችውን ግለሰብ በድጋሚ ወደ ሶስተኛ አገር ለማባረር ያቀረበችው ዕቅድ በፌደራሉ ዳኛ በጊዜያዊነት ታገደ።
የፌደራሉ ዳኛ ኪልማር አብሬጎ ጋርሺያ የተባለው ግለሰብ ወደ ሶስተኛ አገር ምናልባትም ወደ ኡጋንዳ መባረሩን በጊዜያዊነት አግደዋል።
ይህንንም እገዳ ተከትሎ በአውሮፕላን ሊሳፈር የነበረው ኪልማር በኢሚግሬሽን ባለስልጣናት አማካኝነት በእስር ወደሚቆይበት ስፍራ ተወስዷል።
የአሜሪካ መንግሥት ጋርሺያን በስህተት ኤል ሳልቫዶር ወደሚገኝ ነውጠኛ እስር ቤት አስገብቶት የነበረ ሲሆን በመጨረሻም መጋቢት ወር ላይ ወደ አሜሪካ መልሶ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ መስርቶበታል።
ጋርሺያ የቀረበለትን የጥፋተኝነት ውል ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የአሜሪካ ባለስልጣናት ወደ ኡጋንዳ እንደሚያባርሩት መንገራቸውን ጠበቆቹ ተናግረዋል።
ጋርሺያ የታሰረበትን አኳኋን እንዲሁም እንዲሁም ወደ "ኡጋንዳም ሆነ ሌላ አገር" መባረሩን በመቃወም አዲስ የፌደራል ክስ አቅርቧል።
ማክሰኞ በነበረው ችሎት ፓውላ ሺንስ የተሰኙት ዳኛ ጉዳዩ እስኪሰማ ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ጋርሺያን ከአገር እንዳያባርር እግድ መጣላቸውን አስታውቀዋል።
ዳኛዋ መንግሥት ጋርሺያን ወደ ኡጋንዳ ለማባረር የተነሳበትን አላማ ጥያቄ ውስጥ ከተዋል።
ጋርሺያ ወደ ኡጋንዳ ቢባረር ጉዳት እንደማይገጥመው የአሜሪካ ባለስልጣናት ማሳየት እንደተሳናቸው ዳኛዋ ጠቅሰዋል።
ጋርሺያ የቀረበበትን ወንጀል ጥፋተኛ ነኝ ብሎ ባለማመኑ ምንም አይነት ትስስር ወደሌለው ሃገር መንግሥት ለመላክ ማቀዱ ዳኛዋ ስጋት እንዳሳደረባቸው በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
"በእኔ ዕይታ ይህንን ማድረግ እንደማትችሉ ግልጽ ነው፤ ህገ መንግሥታዊ መብትን ለመግፈፍ እንዲህ አይነት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አትችሉም" ሲሉ ዳኛ ሺኒስ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሁለት ከዚህ ቀደም የተሰጡ የፍርድ ትዕዛዞች መንግሥት ጋርሺያን እስከ መጪው ረቡዕ ከሰዓት ድረስ ከአገር እንዳያባርረው ይከለክላሉ።
የመንግሥት ጠበቃ ድሩ ኤንሲንግን በበኩላቸው "ጋርሺያ ከአገር መባረሩ የማይቀር ነው" ሲሉ ለዳኛዋ አስረድተው ወደ ሶስተኛ አገር ማባረር "ጊዜን የሚወስድ ነው" ብለዋል።
ዳኛዋ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ የትራምፕ አስተዳደር ጋርሺያን "ከአገር ፍጹም ማባረር አይችልም" የሚል ብያኔ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ የኢሚግሬሸን ባለስልጣን (አይስ) ጋርሺያን ቨርጂኒያ በሚገኘው ተቋሙ ውስጥ አስሮት እንደሚገኝ ጠበቃው ሲሞን ሳንዶናል ሞሸንበርግ ለዳኛዋ አስረድተዋል።
ግለሰቡ፣ አሜሪካ ከአገር አባራቸው በኤል ሳልቫዶር አደገኛ እስር ቤት እንዲገቡ ከተደረጉ 250 ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኪልማር ከአገር የተባረረበት ሁኔታ ሕጋዊ አይደለም በማለት ዋይት ሐውስ እንዲመልሰው በሚያዝያ ወር ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ፤ ዋይት ሃውስም ይህንን ብያኔ ሲቃወም ቆይቷል።
አሜሪካ በስህተት ወደ ኤል ሳልቫዶር ያባረረችውን ይህንን ግለሰብ ወደ አገር መልሳ በሁለት የፌደራል ወንጀሎች ክስ እንደመሰረተችበት መግለጿ ይታወሳል።
ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት ሲሞን ሳንዶቫል ሞሼንበርግ ክሱን "አሳፋሪ" እንዲሁም አጠቃላይ ሁነቱን "ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም" ሲሉ ፈርጀውታል።
"መንግሥት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመተላለፍ ኪልማርን በውጭ አገር እስር ቤት አጥፍተውት ነበር። አሁን ከወራት መዘግየት እና ሚስጥራዊ አካሄድ በኋላ ስህተታቸውን ለማረም ሳይሆን ለፍርድ ለማቅረብ እየመለሱት ነው" ብለዋል።
ኪልማር ገና በታዳጊነቱ ነው ከኤል ሳልቫዶር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ የገባው።
በአውሮፓውያኑ 2019 በሜሪላንድ ውስጥ ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር በፌደራል የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ተይዞ ነበር።
ሆኖም የኢሚግሬሽን ዳኛ በትውልድ አገሩ ባሉ የወሮበላ ቡድኖች ጥቃት ሊደርስበት ይችላል በሚል ምክንያት ከአገር እንዳይባረር ጥበቃ አድርጎለታል።
ከዚያ በኋላ በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር በትራምፕ አስተዳደር ከአገር የተባረረ ሲሆን የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጋዊ አይደለም በሚል ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ብያኔ አስተላልፏል።