ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አስተዳደር 'በስህተት' ወደ ኤል ሳልቫዶር የላከውን ግለሰብ እንዲመልስ ፍርድ ቤት አዘዘ
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር 'በስህተት' ወደ ኤል ሳልቫዶር የላከውን ግለሰብ ወደ አሜሪካ እንዲመልስ ፍርድ ቤት አዘዘ።
የሜሪላንዱ ነዋሪ ኪልመር አብሬጎ ጋርሲያ በስደት ወደ ኤል ሳልቫዶር እስር ቤት መላኩ ተገልጿል።
ያለፈው ወር ኪልመርና ሌሎችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የወንጀለኛ ቡድን አባላት ናቸው ተብለው ከአሜሪካ መባረራቸው ይታወሳል።
እስከ ሰኞ ድረስ ኪልመር ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ዳኛ ፓውላ ዢኒስ ወስነዋል።
የአሜሪካ የስደትና ከስተምስ ቢሮ አይስ ግለሰቡ ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላከው "በስህተት ነው" ብሏል።
በ2019 ኪልመር ከአሜሪካ መባረር እንደሌለበት በፍርድ ቤት ተወስኖለት ነበር።
ዋይት ሀውስ ግን ግለሰቡ የኤምኤስ-13 ወንጀለኛ ቡድን አባል ነው ብሏል።
ጠበቃው እንዳሉት ይህንን ክስ የሚደግፍ ማስረጃ አልቀረበም።
የትራምፕ አስተዳደር ወደ ኤል ሳልቫዶር የከፋ እስር ቤት የላኩት 238 ቬንዝዌላውያንና 23 የኤል ሳልቫዶር ዜጎችን ነው።
የኪልመር ጠበቃ ሳይመን ሳንዶቫል-ሞሸንበርግ እንዳሉት፣ ደንበኛቸው በምንም ወንጀል ተከስሶ አያውቅም።
"በግዳጅ ከአገር የማስወጣት ያህል ነው" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
አይስ የተፈጠረው ነገር "ስህተት ነው" ቢልም የአገር ውስጥ ደኅንነት ክፍል ግን ፍርድ ቤት ኪልመር በኤል ሳልቫዶር ይዞታ ሥር ስላለ የአሜሪካ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ውሳኔ የመስጠት መብት የለውም ብሎ ተከራክሯል።
ዳኛው ግን ኪልመርን ከአሜሪካ ማስወጣት "ሕገ ወጥ ነው" ብለው ብያኔ ሰጥተዋል።
የዋይት ሀውስ ምክትል ቺፍ ኦፍ ስታፍ ስቴፈን ሚለር ዳኛዋን "የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝደንት ነኝ ብላ የምታስብ ማርክሲስት" ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ኪልመርን መመለስ አይቻልም ማለቱ ጠበቃውን አስቆጥቷል።
"ምንም ጥረት ሳያደርጉ አልተሳካልንም ማለታቸው ነው" ብለዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዐቃቤ ሕግ ኤሬዝ ራቬኒ በፍርድ ቤት ቀርበው ሲከራከሩ ስህተት መፈጠሩን አምነዋል።
ዳኛዋ "የእስር ትዕዛዝ አልወጣበትም። ስለዚህ ከአገር ለማስወጣት ምክንያት አልነበራቸውም" ብለዋል።
ጉዳዩ ከዴሞክራቶች በኩል ትችት አስከትሏል። የትራምፕ የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣኖች ትክክለኛውን አሠራር እየጣሱ ነው ሲሉም ነቅፈዋል።
ዴሞክራቱ የሜሪላንድ አገረ ገዢ ዌስ ሞር "ስህተት መሥራታቸውን አምነዋል። ስለዚህ እንዲያርሙት እጠብቃለሁ" ብለዋል።