ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢሎን መስክ አባት፡ "ልጄ ዐይን አፋር ነው፤ ለፖለቲካ አልተፈጠረም"
ኢሎን መስክ የዓለም ቁጥር አንድ ቱጃር ነው። ከከፍተኛ ፖለቲከኞች ጋር ወዳጅነትም አለው። 'ይፋዊ ያልሆነው የአሜሪካ ፕሬዝደንት' እስከመባልም ደርሷል።
የኢሎንን ልጅነት ለማወቅና የበለጠ ስለ ኢሎን ለማወቅ ቢቢሲ ከአባቱ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኢሎን መስክ አባት ኤሮል መስክ ይባላል።
ለመጨረሻ ጊዜ አባትና ልጅ ያወሩት ከቃለ ምልልሱ አንድ ቀን በፊት ነው።
አባትየው ባለሁለት ሞተር አውሮፕላን ለመግዛት ገንዘብ አንሶት ልጁን እንደጠየቀ ያስታውሳል።
"ትንሽ ገንዘብ አጥሮኝ ነው ሙላልኝ አልኩትና ሰጠኝ። አመሰግናለሁ አልኩት" ሲል አባትየው ያስታውሳል።
ኤሮል መስክ የሚኖረው ኬፕ ታውን አቅራቢያ ባለ ቪላ ቤት ነው። ዘና ያለና በራስ መተማመን ያለው ሰው ነው።
ልጁ ኢሎን የተወለደው በ1971 በፕሪቶርያ ነው። አባቱ መኃንዲስ፣ እናቱ ሞዴል ናቸው።
እናትና አባቱ ከተለያዩ በኋላ ኢሎን ከአባቱ ጋር ይኖር ነበር። ከዚያም በ1989 ወደ ካናዳ አቀና።
ኤሮል "ኢሎን በጣም ጥሩና እንከን የሌለበት ልጅ" ነበር ይላል። የሚፈልገውን ነገር ሁሌም ያገኛል።
"ቁጥር አንድ እስካልሆነ ድረስ እንደማያቆም አውቃለሁ" ይላል አባትየው።
ኢሎን አሁን ተስላ፣ ስፔስ ኤክስና ኤክስን ያስተዳድራል። 419.4 ቢሊዮን ዶላር እንዳለው ዋል ስትሪት ጆርናል ይገልጻል።
በአሜሪካ ፖለቲካ በጉልህ ይታያል። የፌደራል መንግሥትን አሠራር የሚቆጣጠረው ዶጅ ኃላፊ ነው።
በልጅና አባት መካከል ያለው ግንኙነት ውስብስብ ነው። ኢሎን ልጅነቱ በስቃይ የተሞላ እንደነበር ይናገራል።
ግለ ታሪኩን የጻፈው አሽሌ ቫንስ እንደሚገልጸው "ትምህርት ቤት በሽጉጥ ሲባረር ውሎ ቤት መጥቶም ስቃይ ይጠብቀው ነበር"።
ወንድሙ ኪምብል እንደሚለው አባታቸው የቃላት ጥቃት ያደርስባቸው ነበር።
"ይጮህብናል። ለሰዓታት ይመክረናል። እርባና ቢስ ይለናል። አስፈሪና አስቀያሚ ነገሮችን ይለናል" ይላል።
ኢሎን በ2017 ቃለ ምልልስ ሲሰጥ "አባቴ ክፉ ሰው ነው" ብሎ ነበር።
ኤሮል ግን ለምን ልጁ እንደዛ እንዳለ አያውቅም።
"አሁን እናወራለን። የሆነ ጊዜ ላይ ይቅርታ እንደሚጠይቀኝ እርግጠኛ ነኝ። ወንድ ልጆች በሆነ መንገድ ከአባቶቻቸው ጋር እንደሚፎካከሩ መዘንጋት የለብንም" ይላል።
ኤሮል ወታደር መሆኑ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት አይክድም።
"ከትል በታች እንደሆንንና ወደላይ ከፍ ለማለመት መሥራት እንደሚጠበቅብን ይነገረናል። በዚህ ሒደት ውስጥ ጠንካራ ወንድ ይወጣናል" ሲል ይገልጻል።
ኤሮል እና ኢሎን ብዙ ተመሳሳይ ነገር አላቸው። ሁለቱም ነጋዴ ናቸው። ሁለቱም አወዛጋቢ ናቸው። ሁለቱም ብዙ ልጆች አሏቸው።
ኤሮል ሰባት ልጆች ሲወልድ ኢሎን 14 ልጆች እንዳሉት ይታመናል።
ኤሮል ልጁ በሥራ ጫና ምክንያት ልጆቹን ችላ በማለቱ ይወቅሰዋል። እሱ ግን ለልጆቹ እኩል ትኩረት ለመስጠት መሞከሩን ይናገራል።
ኤሮል ቃለ ምልልስ ላይ ሳለ አራተኛ ልጁን ረስቷት ነበር። የአራተኛ ልጁ እናት የቀድሞ የእንጀራ ልጁ ጃና በዙዳንሁት ናት።
ኤሮል የጃናን እናት ሄይዲ ያገባው ጃና አራት ዓመቷ ሳለ ነበር።
ኤሮል ሦስት ሴት ልጆች አሉኝ ካለ በኋላ መልሶ መሳሳቱን አምኖ ሴት ልጆቹ አራት መሆናቸውን ይናገራል።
የመጀመሪያ ልጅ ሲወልዱ ጃና 30 ዓመት ሲሆናት ኤሮል 70 ዓመቱ ነበር። ሁለት ልጆች ወልደው ተለያይተዋል።
የጃና እና ኤሮል ግንኙነት በኤሮልና ኢሎን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል።
ኢሎን የፖላንድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ትንሽ ሰው" ብሎ መሳደቡ ይታወሳል። ሰዎችን በአደባባይ ሲዘልፍ አባትየው ይሸማቀቅ ይሆን? በሚል ተጠይቋል።
አባትየው "ኢሎንም ይሁን ሌሎቹ ልጆቼ የሚናገሩት እያንዳዱ ቃል ያሳስበኛል። ራሳቸውን ችግር ውስጥ እንዳይከቱ ስለምሰጋ ነው የሚያሳስበኝ" ሲል መልሷል።
"ልጅ ሳለ ጀምሮ ትልልቅ ሰዎችን ደደብ ማለት እንደሌለበት እነግረው ነበር። እሱም 'ለምን? ደደብ ናቸውኮ' ሲል ይመልሳል። እኔም ደደብ ቢሆኑም ልትነግራቸው አይገባም እለዋለሁ" ሲልም አባትየው አክሏል።
ኤሮል እንደሚለው ፖለቲካ ውስጥ በነጻነት መናገር እንደሚስተዋል ጠቅሶ "አንድ ቀን ተሰዳድበው በሌላ ቀን ወዳጅ ይሆናሉ" ይላል።
ኢሎን በፖለቲካው ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቢሆንም አባቱ ኤሮል ግን ለፖለቲካ የሚሆን ሰው እንዳልሆነ ይናገራል።
"የቴክኖሎጂ ሰው ነው። የቴክኖሎጂ ሰዎች ነገሮች ትርጉም እንዲሰጧቸው ይፈልጋሉ" ይላል።
ልጁ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ለመሥራት እንደሚቸገር ይገልጻል።
"ሰዎቹ ታዋቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ደደብ ሆነው ይገኛሉ" ይላል ኤሮል።
ኤሮል እሱና ቤተሰቡ በተለየ ሁኔታ የሚያደንቁት ፖለቲከኛ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መሆኑን ይናገራል።
"ፑቲንን በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሳይሆን እንደ ሰው ስናየው አለማከበር አይቻልም። የሚናገረው ነገር ትርጉም ይሰጣል። በፑቲን አለመደነቅ ከባድ ነው" ይላል።
ልጁም በዚህ ሐሳብ እንደሚስማማ ኤሮል ያምናል።
ሩስያ ዩክሬንን ስለመውረሯ ሲጠየቅ "ማን በትክክል እንደጀመረው ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው" ሲል ይመልሳል።
ለዩክሬን በጦርነቱ መጀመሪያ ስታርሊንክ ሳተላይት ኢንተርኔት ማቅረብ ትክክል እንደነበር ኤሮል ያምናል።
ኢሎን ለገንዘብ ሲል አቋሙን ለውጧል የሚለውን አይቀበለውም።
"ቤተሰባችን ሁሉም ነገር አለው። ከዚህ በላይ ገንዘብ አንፈልግም" ሲልም መልሷል።
ስለ ኢሎን ሰዎች የማያውቁት ነገር ምንድን ነው? በሚል የተጠየቀው ኤሮል "ያፍራል።
አሁንም ድረስ ሰው በተሰበሰበበት መድረክ ላይ እንዴት ማውራት እንዳለበት እየተለማመደ ነው።
ማለት ያለበትን ነገር በፍጥነት ነው የሚለው" በሚል ምላሽ ሰጥቷል።