ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ኪየቭ ገቡ
ከፍተኛ የፔንታጎን ባለሥልጣን "ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረግ ጥረት ላይ ለመነጋገር" ዩክሬን መግባታቸውን የአሜሪካ ጦር አስታወቀ።
በአሜሪካ ጦር ዋና ጸሀፊ ዳን ድሪስኮል የተመራው የልዑካን ቡድን ሐሙስ ዕለት በኪየቭ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ያገኛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ረቡዕ ዕለት አሜሪካ እና ሩሲያ ዩክሬን ግዛቶቿን አሳልፋ እንድትሰጥ የሚጠይቅ አዲስ የሰላም ዕቅድ እያዘጋጁ ስለመሆኑ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር።
ሩሲያም ሆኑ ዋሽንግተን የመረጃውን ትክክለኛነት አላረጋገጡም።
ረቡዕ ዕለት ሩሲያ በዩክሬን ምዕራባዊ ግዛት ተርኖፒል በሚሳዔል እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች በፈጸመችው ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ የፈጸመችው እአአ በ2022 የካቲት ወር ላይ ነበር።
የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዴቪድ በትለር በሰጡት መግለጫ "ድሪስኮል እና ልዑካቸው ዛሬ ማለዳ የዩክሬን ባለሥልጣናትን ለማግኘት እና ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ላይ ለመነጋገር ኪየቭ ደርሰዋል" ብለዋል።
ከድሪስኮል ጋር ወደ ስፍራው ያቀኑት የአሜሪካ ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል ራንዲ ጆርጅ፣ በአውሮፓ ከፍተኛ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጄኔራል ክሪስ ዶናሁ እና የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ሚካኤል ዋይመር ናቸው።
ድሪስኮል እና ጄኔራል ጆርጅ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በዩክሬን ውይይት ካደረጉ ከፍተኛ የጦር ጄነራሎች መካከል ናቸው።
ረቡዕ ዕለት የወጡ ምስሎች ድሪስኮል ከዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚያሃል ጋር ተገናኝተው ሲጨባበጡ አሳይተዋል።
ከዚያ በኋላ ሽሚያሃል በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ "በፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ እና በፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስምምነት የተደረሰበትን ታሪካዊ የመከላከያ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለው ቀጣይ ምዕራፍ ላይ እናተኩራለን" ብለዋል።
አክለውም ዋሽንግተን "በግምት 105 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የፓትርዮት የአየር መከላከያ ስርዓት አጋዥ ቁሶችን ለመግዛት" ድጋፍ ስላደረጉ አመስግነዋል።
ቀደም ሲል የዩክሬን ባለሥልጣናት ከልዑካን ቡድኑ ጋር የሚደረገው ንግግር መሬት ላይ ስላለው ወታደራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም የተኩስ አቁም የሚደረግባቸው ዕቅዶች ላይ እንደሚያተኩር በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ባለሥልጣን "ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ እና ትራምፕ አሁን ባለው የውጊያ መስመር ላይ ጦርነቱን ለማስቆም ተስማምተዋል፤ እንዲሁም የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ከስምምነት ላይ ተደርሷል" ብለዋል።
በርካታ መገናኛ ብዙኃን አሜሪካ እና ሩሲያ በግላቸው ጦርቱን ለማስቆም የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ማርቀቃቸውን እየዘገቡ ነው።
አክሲዮስ፣ ፋይናንሻል ታይምስ እና ሮይተርስ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት የቀረቡት ዕቅዶች ኪየቭ የተወሰኑ ግዛቶቿን እና መሣሪያዎቿን እንድትሰጥ እንዲሁም የዩክሬን መከላከያ ኃይል ብዛት በከፍተኛ ቁጥር እንዲቀንስ ይጠይቃል።
የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መልዕክተኛ ኪሪል ዲሚትሪቭ ባለ 28 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ላይ በጋራ መስራታቸውን ይታመናል።
ቢቢሲ ዋይት ሐውስ እና የዊትኮፍ ተወካይ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ ዘገባዎቹን አጣጥለዋል።
ረቡዕ ዕለት ለሩሲያ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ምላሽ በነሐሴ ወር ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ትራምፕ በአላስካ የተገናኙበትን ጉባዔ በመጥቀስ "አሁን ባለው ሁኔታ 'የአንካራጅ መንፈስ' በሚል ምንም የጨመርነው አዲስ ነገር የለም" ብለዋል።
ፕሬዚዳንቶቹ በነበራቸው የአንድ ቀን ስብሰባ ወቅት ስለተደረሰው ስምምነት ምንም ይፋ የሆነ ነገር የለም።
ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ በተደጋጋሚ የዩክሬን ግዛቶችን አሳልፎ መስጠት የማይታሰብ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።