ዜሌንስኪ ክሬይሚያን ለሩሲያ አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ 'እንደሚያስቡ' ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ክሬሚያን የሰላም ስምምነት አካል አድርገው ለሩሲያ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው ብለው እንደሚያስቡ ተናገሩ። ኪዬቭ ግን ከዚህ ቀደም ይህን መሰሉን ሃሳብ ውድቅ አድርጋው ነበር።

እአአ በ2014 በሕገ ወጥ መንገድ ሩሲያ የተጠቀለለችውን ግዛት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ ስለመሆናቸው የተጠየቁት ትራምፕ "አንደዚያ ነው የማስበው" ሲሉ መልሰዋል።

ትራምፕ አክለውም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱ እንዲቆም "ተኩስ እንዲያቆሙ፣ ተቀምጠው ስምምነት እንዲፈርሙ" አሳስበዋል። ይህም በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሊሳካ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ትራምፕ ይህን የተናገሩት ከቫቲካን ከተመለሱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየታቸውን ነው። ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቫቲካን ተገኝተው የነበሩት ፕሬዝዳንቱ ከዜዜንስኪ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

ትራምፕ ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን እና ስለክሬይሚያ "በጣም አጭር ውይይት ተደርጓል" ብለዋል።

በየካቲት ወር በዋይት ሐውስ በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መካከል የተደረገውን አለመግባባት ለማመልከት ሊሆን በሚችል መልኩም ዜሌንስኪ አሁን "ረጋ ያለ" ይመስላል ሲሉ ተናግረል።

ዩክሬን ምንም ዓይነት የግዛት ስምምነት መደረጉን ደጋግማ በመቃወም በመሬት ጉዳይ ላይ መነጋገር የሚቻለው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሲደረስ ብቻ መሆኑን አበክራ ስትገልጽ ቆይታለች።

ዜሌንስኪም ሆኑ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በትራምፕ አስተያየት ዙሪያ በይፋ ምላሽ አልሰጡም።

እሁድ ዕለት የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ዩክሬን ለተኩስ አቁም በሚል ግዛቷን የሚያካትት ስምምነት እንዳትደርስ አስጠንቅቀዋል ።

ሚኒስትሩ ለጀርመኑ የዜና ማሰራጫ ኤአርዲ እንደተናገሩት ኪዬቭ "በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሃሳብ መሄድ የለባትም" ብለዋል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት "አብዛኞቹ ዋና ዋና [የስምምነቱ] ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል" ብለዋል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ዩክሬን ክሬሚያን ጨምሮ በሩሲያ የተነጠቀችውን ሰፊ መሬት እንድትሰጥ ልትጠየቅ ትችላለች።

አሜሪካ ቅርቡ ያዘጋጀችውን ዕቅድ ዝርዝር ቢቢሲ አልተመለከተም።