የቴክሳስ ግዛት ትራምፕ ለሚያባርሯቸው ስደተኞች ማቆያ ሰፊ መሬት ለመስጠት ቃል ገባች

የቴክሳስ ግዛት ባለሥልጣናት ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሚያባርሯቸው ስደተኞች ማቆያ የሚሆን 567 ሄክታር መሬት ለመስጠት ቃል ገቡ።

መሬቱ በሜክሲኮ እና አሜሪካን ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን፣ ሕጋዊ ሰነድ ለሌላቸው ስደተኞች ማቆያ የሚውል ነው።

የቴክሳስ መሬት አስተዳደር ቢሮ በፃፈው ደብዳቤ “በሀገራችን ታሪክ አመፀኛ እና ወንጀለኛ ስደተኞችን የምናባርርበት ወቅት ላይ ስለሆንን ለዚህ ማሳለጫ እና ማቆያ እንዲሆን ነው” መሬቱን የሰጠነው ብሏል።

ትራምፕ በተደጋጋሚ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች ከሀገራቸው ጠራርገው እንደሚያስወጡ እና ለዚህ ደግሞ ብሔራዊውን ዘብ እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህ ዕቅዳቸው የገንዘብ እና የሎጂስቲክ እክል ሊገጥመው ይችላል። የመብት ተሟጋች ቡድኖችም የፕሬዝደንቱን ዕቅድ ለማስቀልበስ በሕጋዊ መንገድ ይታገላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢንተርኔት ላይ የተለቀቀው ደብዳቤ ፍሎሪዳ ወደሚገኘው ማራላጎ የተሰኘው የትራምፕ ቅንጡ ሪዞርትም መላኩ ተሰምቷል።

“መሬቱ የእርሻ መሬት ነው። ለጥ ያለ ስለሆነ ለግንባታ ቀላል ነው። ማቆያ ካምፖች በቀላሉ ልንገነባበት እንችላለን” ሲሉ የቴክሳስ የመሬት ኮሚሽነር ዶውን ባኪንግሃም ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

የቴክሳስ ግዛት አስተዳዳሪዎች ትራምፕ ከሥልጣን ከወረዱም በኋላ በራሳቸው ድንበር ላይ አጥር ለመገንባት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር። የግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች ትራምፕ በሜክሲኮ ድንበር አካባቢ ጥበቃው ሊጠናከር ይገባል ማለታቸውን ይደግፋሉ።

ኮሚሽነሯ “የትራምፕ አስተዳደር እነዚህን ወንጀለኞች ከሀገራችን ለማስወጣት ለሚያደርገው ጥረት መቶ በመቶ ተባባሪ ነኝ” ብለዋል።

ነገር ግን ዲሞክራት ሀገረ-ገዢዎች ያሏቸው ካሊፎርኒያ፣ አሪዞና እና ኒው ሜክሲኮ በጅምላ ስደተኞችን ማባረር የሚባለውን ሐሳብ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ድንበር ላይ የሚገኙት ጥበቃዎች እና የግብር እና ገቢ ባለሥልጣናት ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለአጭር ጊዜ ለማቆየት የሚጠቀሙት የጨርቅ እና የፕላስቲክ ዳሶችን ነው። ከዚህ በተጨማሪ በጡብ የተሠሩ ቤቶችም ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ስለስደተኞች ጉዳይ ትራምፕን የሚያማክሯቸው ስቴፈን ሚለር የትራምፕ አስተዳዳር ስደተኞችን ለማባረር የሚሆኑ እጅግ ሰፊ ማቆያዎችን ይገነባል ሲሉ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

አማካሪው በቴክሳስ ግዛት በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ ሰፊ እና አውላላ ሜዳ ላይ የስደተኞች ማቆያ ይገነባል ሲሉ ነው የተናገሩት።

ከኢሚግሬሽን ኤንድ ከስተምስ ኢንፎርስመንት አሊያም በቅፅል ስሙ አይስ እየተባለ ከሚጠራው ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት 38,863 ስደተኞች ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።

12 ሺህ ገደማ የሚሆኑት ስደተኞች ቴክሳስ ግዛት በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ነው ያሉት።

ምንም እንኳ የቴክሳስ ግዛት ለትራምፕ ስደተኞችን የማባረር ዕቅድ ሰፊ መሬት ለመስጠት ቃል ቢገባም የሎስ አንጀለስ ከተማ ምክር ቤት “የስደተኞች መጠለያ” እንሆናለን ሲል የአዲሱን ፕሬዝደንት ሐሳብ አጣጥሏል።