ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
911 ደውሎ እርዳታ የጠየቀው የላስ ቬጋስ ነዋሪ በመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ተገደለ
የላስ ቬጋስ ነዋሪ የሆነው የ43 ዓመቱ ብራንደን ዱራም ወደ ቤቱ ያለፈቃድ ከገባ ግለሰብ ጋር እየታገለ እርዳታ እንዲሰጠው ወደ 911 ቢደውልም በፖሊስ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።
በወቅቱ አንድ ክፍል ውስጥ ለመደበቅ የተገደደችው የ15 ዓመቷ ሴት ልጁን ጨምሮ የዱራም ቤተሰቦች የፖሊስ መኮንኑ ከሥራ እንዲባረር ጠይቀዋል።
የዱራም ታዳጊ ልጅ እንደገለጸችው ከሆነ የላስ ቬጋስ ፖሊሶች አባቷን እንደ “ተበዳይ” ሳይሆን እንደ “ጥቃት አድራሽ” አድርገው ስለቆጠሩት “ውስጧ ተሰብሯል።”
ዱራምን በጥይት የገደለው አሌክሳንደር ቡክማን የተባለው ፖሊስ ጠበቃ ግን ደንበኛው ምንም አይነት ወንጀል እንዳልሠራ ተናግሯል።
የላስ ቬጋስ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ በበኩሉ የተከሰተውን ክስተት እስኪመረመር ድረስ የ26 ዓመቱ ቡክማን ደመወዝ እየተከፈለው ሥራውን አቁሞ እንዲቆይ መደረጉን ተናግሯል።
ዱራም ወደ 911 ደውሎ ሁለት ሰዎች ከቤት ውጭ እየተታኮሱ እንደሆነ እና ቤቱን ሰብረው ለመግባት እየሞከሩ እንደሆነ ሪፖርት አድርጓል ሲል ፖሊስ ገልጿል።
ለጥሪው ምላሽ የሰጡ ፖሊሶች መስኮቶቻቸው የተሰበሩ መኪኖችን አግኝተዋል።
በተጨማሪም በቤቱ ላይ ጉዳት መድረሱን ከማየት ባለፈ እና ከውስጥ ጩኸት በመስማታቸው ቡክማን ወደ ውስጥ ለመግባት በሩን በኃይል ሰብሮታል ሲል ፖሊስ ተናግሯል።
በፖሊስ የተለቀቀው ቪዲዮ ላይ ቡክማን ሽጉጡን መዝዞ በቤቱ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ከቪዲዮው ዕይታ ውጭ ጩኸት እና ድብድብ ይሰማል።
አንድ መተላለፊያ ላይ ከወገቡ በላይ ራቁቱን የነበረው ዱራም ጭምብል ከለበሰች ሴት ጋር በቢላዋ ሲታገሉ ፖሊሱ ይመለከታል። ግለሰቧ አሌሀንድራ ቡድሮ እንደምትባል ፖሊስ አስታውቋል።
ቡክማን “ቢላዋውን ጣል፣ ቢላዋውን ጣል” ብሎ ጮኸ። ከሰከንዶች በኋላ ሽጉጡን ሲተኩስ ዱራምን ይመታዋል። ቀጥሎም እሱን እና ቡድሬን መሬት ይወድቃሉ።
ቡክማን አምስት ተጨማሪ ጥይቶችን ወደ ዱራም በመተኮስ "እጃችሁን ወደ ላይ አንሱ" ማለቱን በፖሊስ የተለቀቀው የፖሊስ የካሜራ ቀረጻ አሳይቷል።
ዱራም እዚያው ህይወቱ ማለፉ ተነግሯል። አሌሀንድራ ተይዛ የጦር መሣሪያ በመያዝ እና ያለፈቃድ ሰው ቤት መግባትን ጨምሮ አራት ክሶች ቀርበውባታል።
"የሜትሮፖሊታን ፖሊስ አባቴ ከገደለው በኋላ እንዲተኛ መንገሩ በጣም አስከፍቶኛል። የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ቀሪውን ህይወቴን ያለ አባት እንድኖር በማድረጉ ተጎድቻለሁ” ስትል የዱራም ልጅ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግራለች።
የቤተሰቡ ጠበቃ በበኩላቸው ለቡክማን አፋጣኝ የእስር ማዘዣ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የፖሊስ ዘገባን በመጥቀስ የአገር ውስጥ የዜና ማሰራጫዎች እንደዘገቡት ከሆነ ዱራም እና አሌሀንድራ ቀደም ሲል የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው።
ረዳት ሸሪፍ ዶሪ ኮረን በበኩላቸው በርካታ ተኩስ እንደነበረ ቢገለጽም ፖሊስ በቦታው ላይ ሽጉጥ አላገኘም ብለዋል።
ክስተቱ የፖሊስን ግድያዎች በድጋሚ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል። ይህ የሆነውም የፍትህ ሚንስትር በሐምሌ ወር በኢሊኖይ በሚገኘው ቤቷ በአንድ ፖሊስ መኮንን በጥይት ተመትታ በሞተችው በሶኒያ ማሴ ዙሪያ ምርመራ ከመክፈቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።