ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል የተመድ መጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ተገደሉ
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኘው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ ዛሬ፣ ሐምሌ 10/ 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአብዛኛው ሱዳናዊ ስደተኞችን ባስጠለለው በኩመር የመጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ፖሊሶች መገደላቸውን እንዲሁም በርካቶች መቁሰላቸውን ሁለት ስደተኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሙት በዚህ ጥቃት አንድ ስደተኛ ህጻን መጎዳቱንም ነው እነኚሁ የዐይን እማኞች የተናገሩት።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ስደተኞች ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በታጣቂዎች እየደረሰባቸው ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመሸሽ እና በቂ ድጋፍ እንደሌላቸው በመግለጽ ከመንግሥታቱ ድርጅት የመጠለያ ጣቢያዎች ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት ኩመር እና አውላላ ከተሰኙት የመጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡ ስደተኞች ቁጥር 7 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ቢቢሲ ሚያዝያ 30/ 2016 ዓ.ም. በስልክ ያናገራቸው ስደተኞች ተናግረው ነበር።
ስደተኞቹ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸውን በወቅቱ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ስደተኞቹ ከለላ ለማግኘት ሸሽተው ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጪ በዋና ጎዳና ላይ እና በአቅራቢያ በሚገኝ ትንሽ ከተማ ፓሊስ ጣቢያ አጠገብ እያደሩ መሆኑንም እንዲሁ ገልጸዋል።
የዛሬውን ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ስደተኞቹ ያስረዱ ሲሆን ቢቢሲ ጥቃቱን አስመልክቶ ከተባበሩት መንግሥታት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት አውላላ እና ኩመር የተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ከሱዳን፣ ከኤርትራ እና ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን ይቀበላሉ።
ካለፈው ወር ጀምሮ ኩመር 6 ሺህ ስደተኞችን እያስተናገደ ያለ ሲሆን፣ አውላላ ደግሞ በአብዛኛው ሱዳናውያን እና ደቡብ ሱዳናውያን ያሉበት 2 ሺህ ስደተኞችን ይዟል።
በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ሠራዊት እያደረጉት ባለው ግጭት የስደተኞቹ ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።
በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በጦሩ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄኔራል መሃመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ1.6 ሚሊዮን ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ገብተዋል።
ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቱ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያንን ከቤት ንበረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን ሕይወታቸውን ከጦርነቱ ለማትረፍ ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትም ዜጎች ለተፋላሚ ወገኖች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሰለባ ከመሆናቸው ባሻገር ለከባድ ረሃብ መጋለጣቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት እና ግብረ ሰናይ ተቋማት እያሳወቁ ነው።