ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል ከሚገኘው መጠለያ ጣቢያ ወጥተው መንገድ ዳር ያሉ የሱዳን ስደተኞች ጉዳይ እንዳሳሰበው ተመድ ገለጸ
በአማራ ከልል ምዕራብ ጎንደር ከሚገኘው የተመድ መጠለያ ጣቢያ ወጥተው ለሳምንታት ያህል መንገድ ዳር የዋሉ የሱዳን ስደተኞች ጉዳይ እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ገለጸ።
ስደተኞቹ አውላላ ከተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት ጣቢያ ለቀው የወጡት በተደጋጋሚ በታጣቂዎች የሚደርስባቸውን ጥቃቶች በመሸሽ እንደሆነ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ከጥቃቶች በተጨማሪ በመጠለያው ያለው አገልግሎት እጥረት ጋር በተያያዘ አንድ ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ሚያዝያ 23 2016 ዓ.ም ለቀው የወጡ ሲሆን አንዳንዶቹም የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው እጅግ እንዳሳሰበው ኮሚሽኑ ትናንት ግንቦት 20/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ስደተኞቹ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ኩመር እና አውላላ ከተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡ ስደተኞች ቁጥር 7 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ቢቢሲ ሚያዝያ 30/ 2016 ዓ.ም በስልክ ያናገራቸው ሶስት ስደተኞች ተናግረው ነበር።
ስደተኞቹ ሸሽተው ከለላ ለማግኘት ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጭ በዋና ጎዳና ላይ ላይ እና በአቅራቢያዎቹ በሚገኝ ትንሽ ከተማ ፓሊስ ጣቢያ አጠገብ እያደሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ጋር በመሆን ከስደተኞቹ ጋር በመገናኘት ያሏቸውን ስጋቶች ለመስማት እና ለችግሩ መፍትሄዎችን ለማግኘት እየሞከረ መሆኑን ገልጿል።
ስደተኞቹ በመንገድ ላይ መሆናቸውን ተጋላጭነታቸውን የበለጠ እንደሚጨምረው የገለጸው ኮሚሽኑ በተጨማሪም ያሉበት ሁኔታ ንጽህና የጎደለው እና የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው የበለጠ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ ስደተኞቹ ወደ አውላላ ጣቢያው እንዲመለሱ ጠይቆም ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም ከባለስልጣናቱ ጋር ውይይት እንደሚቀጥልም ጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞችን ጨምሮ ፈታኝ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ ባለፈው አርብ የረድዔት ሰራተኞችን የያዘ መኪና በጥይት መኪና መመታቱን ተከትሎ አንድ ሰራተኛ ተገድሏል ብሏል።
ሆኖም ባለፉት ሶስት ሳምንታት የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ መጠለያ ጣቢያ በሆኑት ኩመር እና አውላላ አካባቢ የፌደራል ፖሊሶችን ጨምሮ ተጨማሪ የጸጥታ ጥበቃ ስራዎችን ማሰማራቱን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት አውላላ እና ኩመር የተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ከሱዳን፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን ይቀበላሉ።
ከባለፈው ወር ጀምሮ የኩመር ጣቢያ 6 ሺህ ስደተኞችን እያስተናገደ ያለ ሲሆን የአውላላ ጣቢያ ደግሞ በአብዛኛው ሱዳናውያን እና ደቡብ ሱዳናውያን ያሉበት 2 ሺህ ስደተኞችን ይዟል።
በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና መከላከያ እያደረጉት ባለው ግጭት የስደተኞቹ ህይወት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።
በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በጦሩ መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ1.6 ሚሊዮን ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ከነዚህም ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ገብተዋል።