ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መንግሥት መጠለያ ጣቢያዎችን ለቀው የወጡ የሱዳን ስደተኞች ጉዳይ እንዳሳሰበው ገለጸ
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በአማራ ክልል በሚገኙት ኩመር እና አውላላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የደረሰው “አሳዛኝ ሁኔታ አስግቶኛል” አለ።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ከሚገኙት ኩመር እና አውላላ የተባሉት የተባበሩት መንግሥታት መጠለያ ጣቢያዎች የሱዳን ስደተኞች በተደጋጋሚ ጥቃቶች ሳቢያ መውጣታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ፣ ዛሬ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ነው መንግሥት ሁኔታው እንዳሳሰበው የገለጸው።
በደረሱባቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ከመጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሱዳናውያን ስደተኞች እርዳታ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።
ኩመር እና አውላላ ከተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡ ስደተኞች ቁጥር 7 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ቢቢሲ ዛሬ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ. ም. በስልክ ያናገራቸው ሦስት ስደተኞች ተናግረዋል።
ቢቢሲ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።
የኢትዮጵያ መንግሥት “ከአገልግሎትና ደኅንነት ጋር የተያያዙ ችግሮች” ስደተኞች እየገጠሟቸው መሆኑን እንደሚገነዘብ ገልጿል።
ስደተኞቹ በመጠለያ ጣቢያዎቹ የገጠሟቸውን ችግሮች “ከአገር ውስጥ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች ጋር በመሆን ለመፍታት ቁርጠኛ ነኝ” ሲልም በመግለጫው አትቷል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ከክልል አመራሮችና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር በመሆን ስደተኞቹ ያለባቸውን የደኅንነት ስጋት ለመቅረፍ እና “ባለው ውስን አቅርቦትም ቢሆን መሠረታዊ ግልጋሎትን ለማሻሻል” እንደሚሠራም ተጠቁሟል።
የአካባቢው መስተዳድር የስደተኞቹ ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን “ጥረታቸውን ቀጥለዋል” ሲልም መግለጫው ያክላል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን፣ ስደተኞቹ ከመጠለያ ካምፖች ለቀው መውጣታቸው “እጅግ እንዳሳሰበው” ለቢቢሲ ገልጿል።
ከአውላላ ካምፕ “ወደ ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ለቀው መውጣታቸውን” እንዲሁም ከኩመር ካምፕ “ቢያንስ 300 ገደማ ስደተኞች ለቀው መውጣታቸውን” ለቢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
“በተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች ማጋጠማቸው እንዲሁም ወንጀል፣ ዝርፊያ፣ በመሣሪያ የታገተ ዝርፊያ እና እገታ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ የወጡት” ሲልም አክሏል።
ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት “ሁሉንም አማራጮች እየተጠቀመ” እንደሆነም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን፣ ከተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች በኋላ ስጋት የተሰማቸው 1 ሺህ ስደተኞች ከኩመር መጠለያ ጣቢያ ሸሽተው መሄዳቸውን እንደሚያውቅ መናገሩን ሮይተርስ ከቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
ስደተኞቹ በአካባቢው ሚሊሻዎች ጥቃት እና ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው በኋላ በመጠለያው ከነበሩት 8 ሺህ ስደተኞች መካከል 7 ሺህ የሚሆኑት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ማለዳ ካምፑን ለቀው በእግራቸው መሸሻቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ስደተኞቹ ሸሽተው ከለላ ለማግኘት ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጭ በዋና ጎዳና ላይ ላይ እና በአቅራቢያዎቹ በሚገኝ ትንሽ ከተማ ፓሊስ ጣቢያ አጠገብ ለቀናት ማደራቸውን ተናግረዋል።
እርዳታ እንዲደረግላቸው እየተማጸኑ ያሉት ስደተኞች ከመንግሥት እና ከተባበሩት መንግሥታት ምንም ዓይነት ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘታቸውን አንድ ስደተኛ ዛሬ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“እርዳታ እንፈልጋለን። የመጣነው ችግርን ሸሽተን ነው። አሁን ደግሞ ሌላ ችግር እየገጠመን ነው” ሲሉም ተማጽነዋል።
ስደተኞቹ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጦርነት የሸሹ ስደተኞችን ጨምሮ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እንዳስጠለለች በመጥቀስ፣ በአቅርቦት ውስንነት ምክንያት በኩመር እና አውላላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዲሁም በሌሎችም ቦታዎች አገሪቱ ለስደተኞች የምትሰጠው አገልግሎት አሁን ላይ “እክል እንደገጠመው” ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለስደተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያሻሽል ዓለም አቀፍ አጋሮቹ እንዲያግዙትም በመግለጫው ጠይቋል።
በኩመር መኖሪያቸውን ያደረጉ ሱዳናውያን ስደተኞች ገንዘብ ክፈሉ በሚል መታገት፣ ግድያ እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎችን የመሳሰሉ ለወራት የቀጠሉ ችግሮች እንደገጠሟቸው ለተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ሮይተርስ ገልጿል።
“ወንጀሎች፣ በትጥቅ የታገዙ ዝርፊያዎች፣ ተኩስ እና እገታዎችን ጨምሮ በርካታ የፀጥታ ጉዳዮች ሪፖርቶችን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ ጥለው የሸሹት” ብሏል የተባበሩት መንግሥታት።
የኩመር እና አውላላ መጠለያ ጣቢያዎች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ከመተማ በ70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ይገኙበታል።
መተማ ከሱዳን ለሚመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዋና መዳረሻ ከተማ ስትሆን የኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከአቅሙ በላይ ተጨናንቆ እንደሚገኝ ከጥቂት ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና መከላከያ ሠራዊት እያደረጉት ባለው ግጭት የስደተኞቹ ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።
በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በሆኑት የጦሩ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ 1.6 ሚሊዮን ገደማ ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተመድ መረጃ ያሳያል።
ከነዚህም ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ገብተዋል።