ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊዝ ትረስ፡ ስልጣን እንዲለቁ ያስገደዷቸው 3 መሠረታዊ ጉዳዮች
ሊዝ ትረስ ወደ ዶውኒንግ ስትሪት ከመጡ በ6ኛው ሳምንታቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።
ገና በ45ኛ ቀናቸው ስልጣን መልቀቃቸው በዩኬ ታሪክ ለአጭር ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩ ሰው ያደርጋቸዋል።
ሊዝ ትረስ የወግ አጥባቂ መሪነት ቦታን ከቦሪስ ጆንሰን ተረክበው ለ6 ሳምንታት የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዋል። ከዚህ ቀደም ዩኬን ለአጭር ጊዜ በጠቅላይ ሚንስትርነት የመሩት ጆርጅ ካኒንግ ነበሩ። ጆርጅ ካኒንግ ሞት ሳይቀድማቸው እአአ 1872 ላይ ዩኬን ለ119 ቀናት መርተው ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትሯን ስልጣን እንዲለቁ ያስገደዷቸውን ሦስት ምክንያቶች እንመልከት።
የታክስ ቅነሳ እቅድ
ሊዝ ገና ወደ ስልጣን እንደመጡ ነበር ፈተና የበዛባቸው። ሊዝ ስልጣን በያዙ ሦስተኛ ሳምንታቸው ከፋይናንስ ሚንስትሩ ጋር በመሆን የ45 ቢሊዮን ፓዎንድ የታክስ ቅነሳ እቅድ አስተዋወቁ።
ይህ ግን ብዙ ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን ይዞ በመምጣቱ ትችት አስከተለባቸው። ይህ እቅድ ሙሉ በሙሉ የተተወ ሲሆን የፋይንስ ሚንስትሩም ከስልጣናቸው ተባረዋል።
የፓርቲ አባላት ትችት
ሊዝ ከበርካታ ቁጥር ካላቸው የፓርቲ አጋሮቻቸው ትችት በዝቶባቸው ነበር። አንዳንዶች ስልጣን እንዲለቁ ጭምር በአደባባይ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሴኡላ ብሬቨርማን ስልጣናቸውን ለቀቁ። ሊዝ የተፈጠረባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት የቀድሞ ተቀናቃኞቻቸውን ግራንት ሻፕስ እና ጄረሚ ሃንትን መሾም ነበረባቸው።
ቃል የገቡትን መፈጸም አልቻሉም
ትረስ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪነትን ቦታ ሲይዙ ቀጥሎ ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆኑ ፈጽማቸዋለሁ ያሏቸውን ማድረግ አልቻሉም።
በጽሐፍት ቤታቸው በር ላይ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ባስታወቁበት አጭሩ መግለጫቸው፤ “ወግ አጥባቂ ፓርቲ ለመረጠኝ ኃላፊነት መወጣት እንደማልችል ተረድቻለሁ” ብለዋል።
ማን ሊተካቸው እንደሚችል አልታወቀም
ሊዝ ትረስን ለመተካት በቀጣይ ሳምንት የመሪነት ውድድር ይካሄዳል ይባል እንጂ ተሰናባቿን ጠቅላይ ሚንስትር ማን ሊተካ እንደሚችል እስካሁን አልታወቀም።
አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። ጀረሚ ሃንት የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል።
ሊዝ ትረስም እርሳቸውን የሚተካ መሪ እስኪገኝ ድረስ በስልጣን ላይ እንደሚቆዩ በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል።
ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ከሕልፈታቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሹመትን ያጸደቁት የሊዝ ትረስን ነበር።
ንግሥት ኤልዛቤጥ በ70 ዓመት የንግሥና ዘመናቸው ሊዝ ትረስ 15ኛ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ነበር።