የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰላም ኮሚቴ ሰየመች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ

የፎቶው ባለመብት, EOTC/FB

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በመላው አገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ኮሚቴ መሰየሙን አስታወቀ።

ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየውን የቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤ መጠናቀቅን ተከትሎ በወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ በአገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ “ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ” ኮሚቴ መዋቀሩ ተገልጿል።

ይህ የሰላም ኮሚቴም በአገር ውስጥ እና በውጭ ካሉ ተቋማት ጋራ የሚሠራ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚኖረው እንደሚሆንም ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ችግር ምክንያት የአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት መቋረጡን፣ በርካታ ምእመናን እና ካህናት በእስር እና በእንግልት ላይ እንደሚገኙ የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ አመልክቷል።

እነዚህም ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ እና በመደበኛ መዋቅራቸው ወደ አገልግሎታቸው እንዲመለስ ለማድረግ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን ተሰይመው ከፌዴራል እና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመነጋገር ችግሮቹ እንዲፈቱ እንዲደረግ መወሰኑም ተገልጿል።

ቤተ ክርስቲያኗ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች፣ የዜጐች መፈናቀል እና ስደት ተወግዶ ሁሉም ዜጋ በአገሩ በእኩልነት፣ በሰላም እና በፍቅር ተከባብሮ በአንድነት እንዲኖር ለማድረግ ግጭቶች እና አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከግንቦት 01 ጀምሮ 16/2015 ዓ.ም. ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ በቤተ ክርስቲያኗ እና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

በተለይ ባለፈው የካቲት ወር ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ዋነኛው ጊዜ የፈለገ አነጋጋሪ አጀንዳ እንደነበር እና በመጨረሻም በስምምነት መጠናቀቁን የቤተክርስቲያኗ አባቶች ሰኞ ዕለት መግለጻቸው ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም መሠረት በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች ባሉ አገረ ስብከቶች የሚያገለግሎ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት በዕጩነት እንዲቀርቡና በመጪው ሐምሌ እንዲሾሙ እና ለሌሎች ክልሎች ደግሞ በመጪው ዓመት እንዲሾሙ ከስምምነት ተደርሷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ከማዕከላዊው ሲኖዶስ በመለየት የራሳቸውን ቤተ ክህነት የመሠረቱት የትግራይ ጳጳሳት ማክሰኞ ዕለት ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መወሰናቸውን ቢያሳውቁም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ግን በክልሉ ካሉ አባቶች ጋር የተቋረጠውን ግንኙነት ለማስተካከል አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

“በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ተሰይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ልዑክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል” የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ተልዕኮውን እንዲፈጽም መመሪያ መሰጠቱ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ለአስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ የሚሆን ሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ፣ በመላው አገሪቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳትም የተለያዩ ተግባራት እንዲከናወኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ መወሰኑን መግለጫው አመልክቷል።

ከወራት በፊት ሕገ ወጥ ነው ከተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጋር በተያያዘ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጉዳይም ምላሽ እንደተሰጠው መግለጫው ጠቅሷል።

በዚህም በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ የመቱ ፈለገ ሕይወት የነገረ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲከፈት፣ በሌሎች አህጉረ ስብከቶች ሊከፈቱ የታሰቡ ኮሌጆችን እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን በተመለከተም ጥናት ተደርጎ በቀጣይ ዓመት ጥቅምት ወር ለሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል።

ባለፈው የካቲት ወር ከቤተ ክርስቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት ውጪ በሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ተሰጥቷል የተባለውን ሲመት ተከትሎ ከተፈጠረው ቀውስ በኋላ የተካሄደው ይህ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ፣ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ እና ውጥረት የተሞላበት እንደነበር ተነግሯል።

በተለይ ውዝግብ ካስነሳው ሹመት ጋር በተያያዘ ይሰጣል የተባለው ውሳኔ ዋነኛው እና ሰፊ ጊዜ የፈለገ እንደነበር የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ገልጸዋል።

በመጨሻም የኤጲስ ቆጶሳትን ሹመት በተመለከተ “ክፍት በሆኑ እና በተደራቢነት በተያዙ፣ ጉልህ እና አንገብጋቢ ችግር ላለባቸው” በኦሮምያ እና በደቡብ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከቶች ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ በስምምነት በመሰየም መቋጫ እንደተበጀለት ተነግሯል።