ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉግል በተሳሳተ የአቅጣጫ ጥቆማ የሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል በሚል ተከሰሰ
ጉግል ማፕ ፊሊፕ ፓክሰን የተባለ ግለሰብን በፈረሰ ድልድይ ላይ እንዲያሽከረክር በማመላከቱ ህይወቱን አጥቷል ያሉ ቤተሰቦች ጉግል ላይ ክስ መሰረቱ።
ጉግል ወቅታዊው የስፍራውን ሁኔታ ባለመጠቆሙ የቤተሰባቸውን አባል ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኗል በሚል ነው ወደ ፍርድ ቤት ያመሩት።
የፊሊፕ ፓክሶንስ ቤተሰቦች ጉግል በቸልተኝነት ከ9 ዓመት በፊት ከአግልግሎት ውጪ የሆነ ድልድይን ማመላከት ባለመቻሉ ህይወቱን እንዳጣ ተናግረዋል።
ፓክሰን ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ በአሜሪካ ሰሜን ካሊፎርኒያ ግዛት ከጥቅም ውጪ የሆነ ድልድይ ላይ ለማሽከርከር ሲሞክር ነበር ሕይወቱ ያለፈው።
የጉግል ቃል አቀባይ የቀረበውን ክስ ኩባንያው እየተመለከተው እንደሆነ ተናግረዋል።
ትላንት ረቡዕ ክሱ ተመስርቷል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ፓክሰን ሴት ልጇቹን የጓደኛቸውን ልደት እንዲያከብሩ ወደ ቤቷ ወስዷቸው እየተመለሰ ሳለ ነበር አደጋው ያጋጠመው።
ቤተሰቦቹ እንደመሰረቱት ክስ ከሆነ ፓክሰን ለአካባቢው አዲስ ነበር።
ባለቤቱ ቀደም ብላ ልጇቿን ይዛ ስታሽከርክር እሱ ወደኋላ ቀርቶ ነበር።
“ሚስቱን ልጆቹንና ራሱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንደሚመራ ሰለሚጠብቅ የማያውቀው መንገድ ከሆነ ጉግል ማፕን ይጠቀማል” ሲሉ የቤተሰቡ ጠበቆች ባሰፈሩት መግለጫ ጠቅሰዋል።
“በሚያሳዝን ሁኔታ ያለምንም ጥርጣሬ በዝናብና ጨለማ ውስጥ የጉግልን ጊዜ ያለፈበት አቅጣጫ እየተከተለ ሲያሽከረክር” ከ9 ዓመት በፊት በከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት የፈረሰ ድልድይ ላይ ለማሽከርከር ሲሞክር ባጋጠመው አደጋ ህይወቱን እንዳጣም ገልጿል።
የአከባቢው ነዋሪዎች እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 የፈረሰውን ድልድይ በተመለከተ ያለውን መረጃ እንዲያስተካክል ጉግልን በተደጋጋሚ መጠየቃቸውንንም ክሱ ያመላክታል።
ወደ ድልድዩ የሚወስደውን መንገድ የሚዘጉ ብረቶች መጥፋታቸውም ተገልጿል።
ጠበቃዎቹ ድልድዩን የመጠገን ኃላፊነት አለባቸው ያላቸውን ሶሰት ተቋማትንም ከሷል።
“ልጆቻችን አባታቸው እንዴት እና ለምን እንደሞተ እየጠየቁ ነው። እኔም እንደአዋቂ ምን እንደተፈጠረ ስላልገባኝ እንሱን ማስረዳት አልቻልኩም” ስትል የፓክሰን ባለቤት በሰጠችው መግለጫ ተናግራለች።
ጉግል በበኩሉ ለፓክሰን ቤተሰቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን እንገጻለን ማለቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።