ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መከላከያ በአልሻባብ የተቃጣበትን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ማክሸፉን አስታወቀ
የኢትዮጵያ መከላከያ በምዕራብ ሶማሊያ በምትገኘው ሮብ ድሬ ከተማ በአልሻባብ የተቃጣበትን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ማክሸፉን አስታወቀ።
የአልሻባብ ኃይል በሮብ ድሬ ባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቢያስብም “ሙሉ በሙሉ ከሽፎ ተደምስሷል” ሲልም መከላከያ ዛሬ መስከረም 9/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አልሻባብ ለዚህ ጥቃት ሶስት ፈንጂ የጫኑ መኪናዎች፣ 12 ፈንጂ የታጠቁ ታጣቂዎች እንዲሁም ከ450 በላይ አባላቱን ማሳተፉንም መከላከያ የክፍለ ጦር አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ፈይሳ አየለን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል።
ኮሎኔል ፈይሳ ቡድኑ “አሉኝ የሚላቸውን አባላቱን ለጥፋት ቢያሰልፍም በቀጠናው በሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጥፋት ሃሳቡን ሳያሳካ ተደምስሷል” ሲሉም ተናግረዋል።
አልሻባብ በርካታ የሰው ሃይል በማሰለፍ እና በተሽካርካሪ ፈንጂ ጠምዶ ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሷል ያሉት ደግሞ ሻምበል ጥላሁን ደምሴ ናቸው።
ሆኖም የመከላከያ ኃይል ሁለት ክፍሎች ተናበው እና ተቀናጅተው “ለጥፋት የተንቀሳቀሰውን የአልሻባብ ኃይልን በመቅደም ከአፈር ቀላቅለነዋል” ሲሉም ሻምበሉ መናገራቸውን መከላከያ በመግለጫው አትቷል።
መከላከያ አልሻባብ ቃጥቷል ያለው ጥቃት መቼ እንደሆነ ባይገልጽም በምዕራብ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር ከአልሻባብ ጋር እሁድ መስከረም 6/ 2016 ዓ.ም ከፍተኛ ግጭት ውስጥ መግባቱን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል።
ከኢትዮጵያ ድንበር በ20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ባኮል ክልል፣ ራብ ዱሬ ከተማ አቅራቢያ የኢትዮጵያ ጦር ከአልሻባብ ጋር ያደረጉት ውጊያ ከፍተኛ እንደሆነ ለዜና ወኪሉ የተናገሩት ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጦችን ሰምተናል ብለዋል።
በሶማሊያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ላይ የአልሻባብ ቡድን ሁለት አድፍጦ ጥቃቶች ማድረሱን እና በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ባኩል ክልል እሁድ እለት ግጭት እንደነበረም አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል። በጥቃቶቹ እና በነበረው ግጭት ከባድ ጉዳት መድረሱንም አናዶሉ አስነብቧል።
ለሶማሊያ ፖሊስ የአቅም ግንባታ እና ሌሎች ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው እና በአውሮፓውያኑ 2024 ተልዕኮው የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት የሆኑት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ላይ ነው ጥቃቱ የተሰነዘረው።
የሰላም አስከባሪዎቹ ከየድ ወደ ዋጂድ ከተማ ሲመለሱም በአልሻባብ የመጀመሪያው የደፈጣ ጥቃት እሁድ እለት አጋጥሟቸዋል ብሏል። ሁለተኛው ጥቃት ደግሞ ከኤል ባርዴ ወደ ሁዱር በመጓዝ ላይ በነበሩ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ላይ እንደሆነም ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች በባኩል ክልል በሚገኙት ዋጂድ እና ሁዱር የጦር ሰፈር አላቸው።
የኢትዮጵያ መከላከያም ተከታታይ የመልሶ ማጥቃቶችን እንደፈጸመም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በሁዱር የሚገኙ የጸጥታ መኮንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ከሶማሊያ ወታደሮች ጋር በመሆን በመልሶ ማጥቃቱ ከ55 በላይ የአልሻባብ ታጣቂዎችን መግደላቸውን ያስነበበው ዘገባው ነገር ግን በሁለቱ ጥቃቶች ምን ያህል የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደተገደሉ እና እንደቆሰሉ የጸጥታ መኮንኑ ከመግለጽ ተቆጥበዋል ብሏል።
አናዱሉ በዚህ ዘገባው በኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪዎች እና በአልሻባብ አባላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መኮንኑን ዋቢ በማድረግም አስፍሯል። ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው አልሻባብ 167 የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደሉን እና ወታደራዊ ተሽካርካሪዎችን ማውደሙን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከሶማሊያ ጋር በሚያዋስናት የድንበር ከተማ በአልሻባብ የተቃጣባትን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ ማክሸፏን ማስታወቋ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት መጨረሻ በሶማሌ ክልል ዶሎ ከተማ አልሸባብ የቃጣው ጥቃትም ጥፋት ከማድረሱ በፊት በአካባቢው የነበረው የመከላከያ ሰራዊት በተሳካ ሁኔታ አስቁሟቸዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መከላከያ የአጥፍቶ ጠፊዎቹን ታጣቂዎቹን መግደሉን እና “ለአሸባሪ ቡድኑ” ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያዎችን ማውደሙም በወቅቱ ተገልጿል።
በ2014 ሐምሌ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአል ሻባብ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ወደ ሶማሌ ክልል ከገቡ በኋላም ለሳምንታት የዘለቀ ውጊያም ተደርጎ ተመትተው ተመልሰዋል መባሉ ይታወሳል።
ይህን በአልሸባብ የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ መሰማራቱን የሶማሌ ክልል መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።