ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ በአልሻባብ የተቃጣባትን ጥቃት ማክሸፏን አስታወቀች
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በሚያዋስናት የድንበር ከተማ በአልሻባብ የተቃጣባትን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ ማክሸፏን አስታወቀች።
ጥቃቱ በሶማሌ ክልል ዶሎ ከተማ በኩል ትላንት ግንቦት 30/ 2015 ዓ.ም መቃጣቱንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
በአካባቢው የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ቡድኑ ጥፋት ከማድረሱ በፊትም በተሳካ ሁኔታ እንዳስቆማቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የትናንት መግለጫ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መከላከያ የአጥፍቶ ጠፊዎቹን ታጣቂዎቹን መግደሉን እና “ለአሸባሪ ቡድኑ” ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያዎችን ማውደሙም ተገልጿል።
መግለጫው በደፈናው የሽብር ጥቃቱ መክሸፉን እንዲሁም ታጣቂዎች መገደላቸውን ቢገልጽም የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
አል ሻባብ ረቡዕ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር ሰፈር ላይ በሰነዘረው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት አራት ወታደሮች መቁሰላቸውን ባለስልጣናት ማስታወቃቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ -ሶማሊያ ድንበር ዶሎ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የጦር ሰፈር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሁለት ተሽከርካሪዎች ተሳትፈውበት የነበረ ሲሆን ወዲያውኑ “ታጣቂዎቹ በጦር ሰፈሩ በነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት እንደተገደሉ” የሶማሊያ መንግሥት በሚያስተዳድረው የዜና ወኪል ሶና ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የመጀመርያው ተሽከርካሪ በጦር ሰፈሩ መግቢያ ላይ ፈንድቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ አራት ወታደሮች ቆስለዋል ተብሏል።
ሁለተኛው ተሽከርካሪ ወደ ጦር ሰፈሩ ከመድረሱ በፊት ከጥቅም ውጭ የተደረገ ሲሆን ይህም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረጉም ተገልጿል።
ታጣቂው ቡድን በበኩሉ በሶማሊያ ድንበር ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ሰፈር ላይ ሁለት የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች መፈጸሙን በኮሚዩኒኬሽን ቻናሉ በኩል አስታውቋል ሲል አልጀዚራ የአሜሪካ የቁጥጥር ቡድን ሳይትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የመጀመሪያው ጥቃት በአካባቢው ወታደራዊ ዕዝ ዋና መስሪያ ቤት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘን ኢላማ ማድረጉን ማተቱንም ዘገባው አስነብቧል።
በአልሻባብ ጥቃት የተሰነዘረበት የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በመሆን ታጣቂ ቡድኑን ለመዋጋት እና ወደ ኢትዮጵያ የሚሻገሩ አባላትንም በመከላከል ድንበሩን ለመጠበቅ የተሰማራ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ የጦር ሰፈር የሚገኘው ኃይል ከአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ዕዝ ስር አይደለም።
ባለፈው ሐምሌ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአል ሻባብ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ወደ ሶማሌ ክልል ከገቡ በኋላም ለሳምንታት የዘለቀ ውጊያም ተደርጎ ተመትተው ተመልሰዋል መባሉ ይታወሳል።
ይህን በአልሸባብ የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ መሰማራቱን የሶማሌ ክልል መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።
ረቡዕ የደረሰው ጥቃት በሶማሊያ በሰፈሩ የውጭ ወታደሮች ላይ ሲሰነዘር ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሶስተኛው ነው።
ቡድኑ በቅርቡ በሶማሊያ የታችኛው የሸበሌ ግዛት በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
የኡጋንዳ ሠራዊት በሶማሊያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ስር ለሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ተሰማርቶ ቆይቷል።
በዓመታት ውስጥ አል ሻባብ በኡጋንዳ ሠራዊት ላይ በቅርቡ የፈጸመውን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት በአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች ላይ ፈጽሞ አያውቅም ተብሏል።
አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን ሲሆን፣ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። ቡድኑ በሶማሊያ ውስጥ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ በርካታ የቦምብ እና የደፈጣ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።
አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በኬንያ ውስጥ ተደጋጋሚ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ ጥቃቱ እስከ ኡጋንዳ ድረስ የዘለቀ ነው።
አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም በተደጋጋሚ ሲዝት የቆየ ቢሆንም ከሙከራ ያለፈ ጥቃት አድርሶ አያውቅም። አሁን ታጣቂዎቹ እየፈጸሙት ያለው ጥቃት ያልተጠበቀ ነው።
አልሻባብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አስርጎ ያስገባቸው ታጣቂዎቹ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በወሰደው እርምጃ ወደ 200 የሚጠጉ የቡድኑ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።