ኡሁሩ ኬንያታ በሰላም ንግግሩ ውስጥ እንደማይሳተፉ አሳወቁ

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ለማብቃት ለሚደረገው ጥረት በአፍሪካ ኅብረት ከተሰየሙት አሸማጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በንግግሩ ውስጥ እንደማይሳተፉ አሳወቁ።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ንግግር እንዲጀመር የአፍሪካ ኅብረት ባቀረበው ጥሪ መሠረት በሳምንቱ ማብቂያ ላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነበር።

ከአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ናግኩካ ጋር በአሸማጋይነት በንግግሩ ይሳተፋሉ ተብለው የነበሩት ኬንያታ በመጨረሻው ሰዓት ነው እራሳቸውን ያገለሉት።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ አመራሮች ባለፈው ሳምንት መስከረም 21/2015 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐማት በተጻፈ ደብዳቤ የቀረበላቸውን ንግግር የመጀመር ግብዣ መቀበላቸውን በይፋ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

ቀደም ሲል አርብ ከሰዓት በኋላ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ እሁድ ዕለት ሊጀመር የታሰበው የሰላም ንግግር በሎጂስቲክ ችግር ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋሸጉን ዘግቦ ነበር። ነገር ግን ይህ የሎጂስቲክ ችግር ምን እንደሆነ ዲፕሎማቶቹ የገለጹትም ሆነ ዘገባው ያለው ነገር የለም።

ሁለቱም ወገኖች ደም አፋሳሹን ጦርነት በንግግር ለማስቆም ፈቃደኝነት ካሳዩ በኋላ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውሳኔው አውንታዊ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ፣ በቶሎ ከተጨባጭ ውጤት ላይ እንዲደረስ ተስፋ ሰንቀው ነበር።

ከአሸማጋዮቹ አንዱ የሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ ንግግሩ አንድ ቀን ሲቀረው ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በጻፉት ደብዳቤ በታቀደው ንግግር ላይ እንደማይገኙ ማሳወቃቸው በሂደቱ ላይ መጓተትን እንዳይፈጥር ስጋት ፈጥሯል።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት በሰላም ንግግሩ ላይ ላለመገኘታቸው እንደ ምክንያት ያቀረቡት የንግግሩ ጊዜ እሳቸው ከያዙት ሌላ መረሃ ግብር ጋር በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑን በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኡሁሩ ከዚህ ባሻገርም በሌላ ጊዜ የሚካሄድ ከሆነና እሳቸውም በአሸማጋይነት የሚሳተፉ ከሆነ፣ ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ዝግጅት እንዲረዳቸው ያሉትን “ንግግሩ ስለሚካሄድበት ሂደት አወቃቀር እና አፈጻጸም፣ የተጋበዙ አሸማጋዮች መመሪያ ላይ ማብራሪያ” ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ማድረግ ከንግግሩ ከአጀንዳዎች ሁሉ ቀዳሚው እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸው፤ ይህም የሰዎችን ስቃይ በማስቆም ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ከማስቻሉ ባሻገር ለንግግሩ ትክክለኛውን ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል ኡሁሩ በደብዳቤያቸው።

ኡሁሩ ኬንያታ ለሁለት የሥልጣን ዘመን ለ10 ዓመታት የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነ ካገለገሉ በኋላ ባለፈው ነሐሴ ወር ማብቂያ ላይ ሥልጣናቸውን በምርጫ ላሸነፉት ዊሊያም ሩቶ መስረከባቸው ይታወሳል።

ኡሁሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሰላም ለማውረድ ጥረት ካደረጉ መሪዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶም ሥልጣን በተረከቡበት ዕለት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኬንያታ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በታላላቅ ሐይቆች አገራት አካባቢ ያሉ ግጭቶችን ለማስቆም የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀጥሉ አሳውቀው ነበር።

እሁድ መስከረም 29/2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ይጀመራል ተብሎ ስለታቀደው ንግግር ወደ ሌላ ጊዜ ስለመተላለፉም ሆነ ስለ ኡሁሩ ኬንያታ አለመገኘት ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከትግራይ ኃይሎች የተባለ ነገር የለም።

በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ በመቶሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን ማስከተሉ ሲዘገብ ቆይቷል።

የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ተፋላሚዎቹን በማቀራረብ ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም አስካሁን ተጨባጭ ውጤት ያስገኘ ድርድር ሳይካሄድ ቆይቷል።