በኬንያ የግብር ጭማሬን ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኬንያ የኑሮ ውድነት በከፋበት ወቅት መንግሥት የጣለውን የግብር ጭማሬ ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው ተገደለ።
በዛሬው ዕለት በመላው አገሪቷ የተካሄደው የአደባባይ ተቃውሞ የነዳጅ ግብሩን በእጥፍ ያሳደገውና ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ቀረጥ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ፖሊሲን ያስተዋወቀ አዲስ የፋይናንስ ህግ መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ተቃውሞው በፍርድ ቤት እገዳ ተጥሎበታል።
ከዋና መዲናዋ ናይሮቢ በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኢማሊ በነበረው ተቃውሞ አንድ ግለሰብ በጥይት ተመትቶ መሞቱንም የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የፖሊስ መኪና ባቃጠሉና በአካባቢው በሚገኝ ባንክ ላይ ድንጋይ በወረወሩ ተቃዋሚዎች ላይ ፖሊስ ተኩስ መክፈቱን ደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
ኢማሊ ከናይሮቢ ወደ ባህርዳርቻው ሞምባሳ በሚወስደው መንገድ ላይ የምትገኝ ሲሆን ዛሬ ማለዳ ላይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መንገዱን በመዝጋታቸውን መኪኖች ለመተላለፍ መቸጋራቸውን ኬ24 ሚዲያ በድረገጹ ባወጣው ዘገባ አትቷል።
ተቃውሞዎቹን ፖሊስ ህገወጥ ናቸው ብሎ ቢያውጅም ሰልፈኞቹን ከመውጣት አላገዳቸውም።
ፖሊስም ሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት በተቃዋሚው ሞት ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።
ፖሊስ በናይሮቢ የካሙኩንጂ ግቢ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ አስለቃሽ ጭስ የተኮሰ ሲሆን የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደርጋሉ ተብለው እየተጠበቁ ነበር።
ከስፍራው በቀጥታ የተለቀቀው ቪዲዮ እንዳሳየው የመድረክ ቴክኒሻኖች እቃቸውን ለመሰብሰብ ሲሯሯጡ ታይተዋል።
ሚሊዮን ዶላሮችን ፈጅቶ የተገነባው የናይሮቢ ፈጣኑ ጎዳና (ኤክስፕረስ ዌይ) በተቃዋሚዎቹ ምክንያት መዘጋቱን አስተዳደሩ ገልጿል።
የተወሰኑ ተቃዋሚዎችን መንገዱን ሲያበላሹ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጋርተዋል።
ፖሊስ ማስጠንቀቂያ ያስተላፈበትንና ህገወጥ ብሎ የጠራው ይህ ሰልፍ በዕቅድ የተካሄደ ነው።
በተለያዩ ከተሞች የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ የረጨ ሲሆን የፖሊስ አዛዡም ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስፈላጊው እርምጃ ሁሉ ይወሰዳል ብለዋል።












