ዩክሬን ከሩሲያ ጋር አዲስ ዙር ውይይት እንዲደረግ ትፈልጋለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን ባለፈው ወር የተቋረጠውን ድርድር እንደገና ለመጀመር በማቀድ ከሩሲያ ጋር አዲስ የሰላም ድርድር እንዲካሄድ ሀሳብ ማቅረቧን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ተናገሩ።
ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን የሆኑት ሩስቴም ኡሜሮቭ በሚቀጥለው ሳምንት ከሩሲያ አቻቸው ጋር ለመገናኘት ጥያቄ አቅርበዋል።
ዜሌንስኪ ትናንት ምሽት ባደረጉት ንግግር በዚህ ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁሉም ነገር መደረግ ይኖርበታል።
ዜሌንክሲ ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት ያላቸውን ዝግጁነትም በድጋሚ አረጋግጠዋል።
"በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ ስብሰባ ሰላምን በትክክል ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ይህ ምክረ ሃሳብ የመጣው ሩሲያ ሌላ ሰፊ የአየር ድብደባ ጥቃት ከፈፀመች እና የሦስት ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ነው ።
ከአርብ ምሽት እስከ ቅዳሜ ድረስ ባሉት ጊዜያት አስር የዩክሬን ክልሎች እና በርካታ ከተሞች በሩሲያ የአየር ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር ከ340 በላይ ፈንጂዎች እና አነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዲሁም 35 ክሩዝ እና ባለስቲክ ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆንም አብዛኞቹን መክተናቸዋል ብሏል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ በኔቶ አገራት በኩል ወደ ዩክሬን "ከፍተኛ የጦር መሳሪያ" እንደምትልክ ገልጸው፣ ጦርነቱን በ50 ቀናት ውስጥ ለማቆም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ሩሲያ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስፈራርተዋል።
ትራምፕ ባስቀመጡት ቀነ ገደብ ውስጥ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሰች በቀሪዎቹ የሩሲያ የንግድ አጋሮች ላይ 100 ፐርሰንት ሁለተኛ ደረጃ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።
በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል በኢስታንቡል የተካሄደው ሁለት ዙር ውይይት አገራቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ አልቻለም።
ነገር ግን በጦርነቱ የተገደሉትን ወታደሮች አስከሬን ለመመለስ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ምርኮኞችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።
በሰኔ መጀመሪያ ላይ ከተጠናቀቀው የመጨረሻው ዙር ንግግር በኋላ የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩሲያ ዳግም "ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም" እንዲደረግ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ማድረጓን ተናግረዋል።
ኪየቭ እና የአውሮፓ አጋሮቿ እንዲሁም አሜሪካ የሚፈልጉት ያለምንም የቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ነው።
ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛት እንድትሰጣት እና ሁሉንም የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍን መቀበል እንድታቆም ጠይቃለች።
በወቅቱ ዜሌንስኪ ሞስኮን "ቀጣዩ ስብሰባ ውጤት አልባ እንዲሆን የተቻለውን ሁሉ እያደረገች ነው" ሲሉ ወንጅለዋታል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን የወረሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 2022 ነበር።
ሩሲያ አሁን እአአ በ2014 በኃይል የያዘችውን ደቡባዊ ክሬሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።















